ስድስተኛዉ አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ተካሂዷል። እስከ ዛሬ ድረስ የምርጫዉ አጠቃላይ ውጤት እና አሸናፊዉ ፓርቲ አልታወቀም። ለዚህ ምርጫ በርካታ ፓርቲዎች እና የግል ዕጩ ተመራጮች ተወዳድረዋል። የፓርቲ ፖለቲካ አውዱን በተቆጣጠረበት መድረክ የግል ዕጩዎች ተመራጭ ሆነዉ የተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ቢያገኙ፣ የፓርቲዎችን በተለይም የገዢዉን ፓርቲ ተጽእኖ ተቋቁመዉ አገርና ማኅበረሰብ የሚፈልጉትን ዉጤታማ ለዉጥ ማምጣት ይችላሉ ወይስ በፓርቲዎች ተውጠው የይስሙላ ተወካዮች ሆነዉ ይወጣሉ የሚለዉ የብዙዎች ስጋት ነዉ። በዘንደሮዉ ምርጫ በግል ዕጩ ሆነዉ ከቀረቡት መካከል ሙሓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አንዱ ነው ። ዲ/ን ዳንኤል በዚህ ምርጫ ካሸነፈ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ከባቢ የጠፋዉን በመፈለግ፣ የአማካይነት ሚና ወይም ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ ወርቃማዉ እኩሌታ “the golden mean” እያለ የሚጠራዉን እዉነት ወደ ፖለቲካዉ ክበብ ማስገባትን ያለመ መሆኑን ይናገራል። የአማካይ ፖለቲካ አራማጆች ከጡንቻ ይልቅ አዕምሮና ሐሳብን ይጠቀማሉ ፤ለሐሳብ ልዕልና ይሟገታሉ፤ ሰይፍን በሰይፍ የሚለዉን ብሂል ይጠየፋሉ፤ ከደረቅ ፖለቲካ ይልቅ ለሕግ ልዕልና ይተጋሉ፤ ከጨፍላቂነት አስተሳሰብ ወደ አካታችነት ያደላሉ። ዲ/ን ዳንኤልም የዚህ ሐሳብ አራማጅ ሆኖ ወደ ፖለቲካዉ ብቅ ማለቱን በተደጋጋሚ በሰጣቸው ቃለ ምልልሶች አሳዉቋል።
የግል ዕጩዎች በኢትዮጵያ
የግል ዕጩ ተወዳዳሪ ኾኖ ወደ ፓርላማ የመግባት ታሪክ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ ዛሬ የደረሰ የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳያ ነዉ። የሩቁን ትተን ባለፈዉ ሩብ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ የተደረጉት ምርጫዎች ይነስም ይብዛም የግል ዕጩዎች ቀርበዉባቸዋል።
የመጀመሪያ በሆነዉ የ1987 ምርጫ 960 የሚኾኑ የግል ዕጩዎች ተወዳዳሪ የነበሩ ሲሆን፣ 10 ያህሉ የምክር ቤት ወንበር ለማሸነፍ ችለዋል ። በ1992 ዓ.ም. በተካሄደዉ ኹለተኛዉ ምርጫ በግል ከተወዳደሩ 490 ዕጩዎች 13 ዕጩዎች አሸንፈዉ ፓርላማ ገብተዋል። በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ልዩ ቦታ በሚሰጠዉ በምርጫ 97 የግል ተወዳዳሪ ዕጩዎች ቁጥር እየቀነሰ ወደ 353 ወርዶ ነበር። ከ ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) በስተቀር ለምክር ቤት አባልነት ያሸነፈ ዕጩ አልተገኘም። በ 2002 ዓ.ም. በተካሄደዉ አራተኛዉ ምርጫ የግል ዕጩዎች ብዛት ከ 34 አልዘለለም። በዉጤቱም ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ብቸኛዉ የግል ተመራጭ ኾነዉ ተጠናቋል።
በ 2007 ዓ.ም የፓርላማ መቀመጫ ለማግኘት ራሳቸዉን ዕጩ ያደረጉ የግል ተወዳዳሪዎች ብዛት እያሽቆለቆለ መጥቶ 5 ብቻ ቢቀርቡም፣ አንዳቸዉም ተመራጭ ሆነዉ ወደ ፓርላማ መግባት አልቻሉም። በዘንድሮ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ 125 የግል ዕጩዎች ተወዳድረዋል ። ከነዚህ የግል ተወዳዳሪዎች መካከል በቅስቀሳም ሆነ በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ያህል ትኩረት የሳበ፣ ዝርዝር ህልም እና ትልሙን በመድረክና በሰነድ በማስረዳት ወደ ውድድር ሜዳው የገባ ግለሰብ አልታየም።
በአዲስ አበባ ከተማ በምርጫ ክልል 28 የካ ክፍለ ከተማ ስድስት ወረዳዎች፣ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አምስት ወረዳዎች ላይ፣ በድምሩ ዘጠኝ ወረዳዎች ላይ በሚገኙ ከ 133 በላይ ንዑሳን የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደረው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የምርጫ ቦርድ ውጤቱን እስከሚያሳወቅ ድረስ ማሸነፍና አለማሸነፉ ለጊዜው መገለጽ አንደሌለበት የእርሱም ሆነ የምርጫ ቅስቀሳ አስተባባሪዎቹ እምነት ነው። የብዙዎች ግምት እንደሚያሳየው ዲያቆን ዳንኤል አዎንታዊ የሆነ ውጤት አግኝቶ አገራዊ አስተዋጽኦውን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል ከመናገር ግን አልተቀጠቡም።
የግል ዕጩ (Non-partisan politician)
የግል ዕጩ የሚባለዉ የምርጫ ፉክክር በግለሰቦች ብቃት ላይ የተመሰረተ ነዉ። ይህ የምርጫ ፉክክር በመንግሥት ስርአት ዉስጥ የነበረና አሁንም በበርካታ አገሮች የሚታይ ነዉ። ግለሰቦች በፓርቲ ከመሰባበሰብ ይልቅ በግላቸዉ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነዉ ይቀርባሉ።
በስድስተኛዉ አገራዊ ምርጫ የግል ዕጩ ተወዳዳሪ ሆኖ የቀረበዉ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ከፓርቲ ፖለቲካ ይልቅ ወደዚህ አይነቱ የፖለቲካ ፉክክር አማራጭ ያስገባውን ምክንያት ያስረዳል።
የመጀመሪያዉ የአገር ልዕልና ከምንም በላይ በሐሳቦች ልዕልና የሚመጣ እና እነዚህ ሐሳቦች ከአንድ ፓርቲ ፕሮግራም መዋቅርና አሠራር ስለሚሰፉ ምቹ አይሆኑም የሚል እምነት ነዉ።
ሙሓዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ኹለተኛዉ በምክንያትነት የሚያስቀምጠው፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፉክክርን ብቻ ሳይሆን መተባበበር መፈለጉንም ነዉ። የፓርቲ ተመራጮች ከሚበዙበት ፓርላማ ከፓርቲ ዉግንና የወጣ (የራቀ) ነጻ የሆነ አቀራራቢ አካል ሊኖር ይገባል የሚል የጠነከረ እምነት እንዳለው ይናገራል። ፖለቲከኛነት የንቁ ዜጋ ስልጡን እንቅስቃሴ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲናገር የሚደመጠው ሙሓዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣ አገራዊ ምርጫዉ መካሄዱ ሲታወቅ የግል ዕጩ ሆኖ መወዳደር እንደሚፈልግ አሳውቆ ነበር።
“የተለየ የፖለቲካ ፕሮግራምና ስትራቴጂ የለኝም” የሚለው ዲ/ን ዳንኤል፣ ድምጽ ለሌላቸዉ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ድምጽ ለሌላቸዉ ኢትዮጵያዊ ሐሳቦችም ድምጽ መኾንን አልሞ ወደ ስድስተኛዉ አገራዊ የምርጫ ፉክክር መግባቱን ይናገራል።
የትኛዉም ፓርቲ ሐሳብ ያቅርብ፣ የትኛዉም ሕግ ይርቀቅ፣ ርቱዓዊነቱን መጠበቁን መከታተል፣ ለዚያም ያለመታከት መሟገት ዋና ኋላፊነቱ እንደሚሆን ባደረጋቸው የቅስቀሳ መርሃ-ግብሮች ላይ አንጸባርቋል። ከነባር አገራዊ እሳቤዎች የተቀዱ ኢትዮጵያዊ ሐሳቦች በፖሊሲዎቻችን፣ በሕጎቻችን፣ በአሰራሮቻችን ቦታ ሊያገኙ ይገባል የሚለው ዳንኤል፣ በፓርቲ ፖለቲካ ዉስጥ እንዲህ ያሉት እሳቤዎች ቦታ በማጣታቸዉ የእርሱን የግል ዕጩ ኾኖ መወዳደር አስፈላጊ እንዳደረገዉ ይገልጻል። በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሚባል የፖለቲካ ሥርዓት ከተዋቀረ በኋላ የፓርቲ ፖለቲካ(የቡድን ፖለቲካ) መፋፋሙ የግለሰቦችን ሚና ቢያደበዝዘዉም፣ በበርካታ አገራት ግለሰቦች የላቀ ሚና ተጫዉተው በፖለቲካው ግንባር ደማቅ ታሪክ አሳርፈዋል። በኢጣሊያ፣በክሮሺያ፣በቡልጋሪያ በፊንላንድ በግል የተወዳደሩ ዕጩዎች ፕሬዝዳንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር ኾነዉ አገራቸዉን በማስተዳደር የተረጋጋ አገረ-መንግሥት ፈጥረዋል።
በዓለማችን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዉስጥ የግል ዕጩዎች ተመራጭ እንዲሆኑ የሚፈቅዱ የተለያዩ አገራት ቁጥር በርካታ ነዉ። በዚያዉም መጠን ከፓርቲ ፖለቲካ ዉጭ ግለሰቦች የሕዝብን አደራ ለመሸከም የሚያስችል ትካሻ የላቸዉም፣ ግለሰባዊ አቅማቸዉ ለዚህ ደረጃ አያደርሳቸዉም ብለዉ የከለከሉ አንዳንድ አገራት አሉ። ብራዚል በ 1988 ከሕገ-መንግስት ዉስጥ የግል ዕጩ ተወዳዳሪ ኾኖ መቅረብን ስትከለክል፣ አዉስትራያ (ኦሰተርያ/አወሰትራሊያ) እስከ አምስት የሚደርሱ የግል ተወዳዳሪዎችን በአገሪቱ ፓርላማ እንዲካተቱ ትፈቅዳለች።
የግል ተወዳዳሪነት የት ያደርሳል?
ኢትዮጵያ ፓርላሜንታዊ የአሥተዳደር ሥርዓት የምትከተል በመሆኗ ሕዝብ መሪውን የመምረጥ ሥልጣኑን “በአንድ አሸናፊ” የፖለቲካ ፓርቲ እንዲነጠቅ አድርጓል። ፕሬዝዳንታዊ የመንግሥት ሥርዓት በሕግ አውጪው፣ በአስፈጻሚው እና በፍትህ አካላት መካከል ሥልጣንን በመለየት እና በመጋራት ላይ ተመስርቶ የሚዋቀር ነው። ለዚህ ዓይነቱ አሥተዳደር መነሻና ቀዳሚ ምሳሌ የምትሆነው አሜሪካ ናት፤ ብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ ፊሊፒንስ የመሳሰሉ መንግሥታትም ይህን ሞዴል ይከተላሉ።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ፖለቲካው ከጥቅመኝነት እና ከመንደርተኝነት ተላቆ በላቁ አገራዊ ሐሳቦች ልዕለና ላይ እንዲመሠረት፣ እየዳበረ ከዘለቀም ልኂቃኑን ለከፍተኛ ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማነሳሳት የተለያዩ የምርጫ ሥርዓት (ፕሬዝዳንታዊ) በአማራጭነት በማቅረብ ረገድ ሊያግዝ የሚችልበት ዕድል እንዳለው በተለያየ ጊዜ በሰጠው ቃለ ምልልሶች አስረድቷል። ፕሬዝዳንቱ በቀጥታ ተመራጭነቱ በዜጎች በመሆኑም ተጠያቂነቱ እንደ ፓርላሜንታዊው ሥርዓት ለሕግ አውጪው አካል አይሆንም። ከዚህ መርህ በመነሳት ግለሰቦች ከፓርቲ አጥር ወጥተው በግል ተወዳዳሪ ለመሆን መታተራቸው በሂደት የግል ዕጩዎችን ሚና ያሳድገዋል የሚሉ ወገኖች በርክተዋል።
ለአገራቸውና ለወገናቸው በጎና ቀናኢ ርዕይ ያላቸው ግለሰቦች፣ ራሳቸውን ወክለው ወደ ፖለቲካው ጎራ መምጣታቸው በበርካቶች ዘንድ ተመራጭ በመኾን አገር መምራት የሚችሉበት አጋጣሚ ለመፍጠርም በእጅጉ እንደሚያግዝ የሚጠቁሙ አልታጡም።
እርግጥ ነው አሁን ባለው የኢትዮጵያ የመንግስት ሥርዓት ከፓርቲዎች (ቡድኖች) ውጪ ሆኖ የአገረ መንግሥቱን ሥልጣን ጨብጦ ማስተዳደር ለግል ዕጩዎች የተፈቀደ አይደለም። ቀጥተኛ ዲሞክራሲን ለመተግበር የሚያስችል መደላድልም የለም።
እዚህ ላይ ዲ/ን ዳንኤል የሚያነሳው አንድ ሐቅ አለ፣ “የአገራችን ችግሮች የሚመነጩት ከፖለቲካዊና ማሕበራዊ አወቃቀራችን የተነሳ እንደመሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር የሚጣጣም ፖለቲካዊ ባህልንና ሥርዓትን የተሻለ በሚያስቡ፣ የተሻለ በሚናገሩ፣ እና የተሻለ በሚሰሩ ልኂቃን ድርድር (Elite Bargain) ለማነጽ ያስችላል’’ በማለት የግለሰቦችን ሚና ወሳኝነት ያስቀምጣል። ዜጋ (ግለሰብ) ተኮር ፖለቲካዊ ሥርዓትና ባህል፣ አገርን በረጅሙ ጎዳና ለመምራት ጠቃሚ ነዉ ብሎ ያምናል:: ቡድንን ሳይሆን ሐሳብን ወክለዉ በሚንቀሳቀሱ ልኂቃን ድርድርና ንግግር አስፈላጊነት የሚያምነውም ከዚህ በመነሳት ነዉ።
ግለሰቦች ከየትኛዉም ድርጅታዊ ጥርነፋ ነጻ ሆነዉ ባላቸዉ አቅምና ችሎታ ልክ ለአገር አስተዋጽኦ ለማበርከት ቢንቀሳቀሱ፣ እንደ ክፉ ልማድ አልናጠብ ላለዉ ለቡድንተኝነትና የቡድንተኝነት ዕሳቤ በጎ መፍትሄ መሆን ከመቻሉም በላይ ተዋጽኦውን ዜጋ ተኮር በሆነ ዉይይት ቅርጽ አስይዞ ኢትዮጵያን “ፕሬዝዳንታዊ” የማድረግ ተስፋን ለማለምለም ይቻላል በማለት፣ ለዜጋ ፖለቲካ ቦታ ሰጥቶ በግል እንዲወዳደር ሊነሳሳ የቻለበትን መግፍኤ ያስቀምጣል።
ዲ/ን ዳንኤል ይህን ይበል እንጂ በግል ተወዳድሮ ወደ ፓርላማ መግባት እሱ የሚለውን ያህል ድርጅታዊ መዋቅርን ተገዳድሮ ልቆ መዉጣት እንደማያስችል የሚናገሩ የፖለቲካ ምሁራን አልታጡም። ከነዚህ መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆነው ዮናስ አዴዬ (ዶ/ር) አንዱ ነው።
ፓርቲ የግለሰቦች ጥርቅም ሲሆን፣ በዋነኝነት አፈጣጥሩም የፖለቲካ ሥልጣን ጨብጦ ሕዝብን ማስተዳደር ነዉ የሚለው ዮናስ፣ በግል ዕጩ ሆነዉ ወደ ፓርላማ የሚገቡ ተመራጮች የሕዝብ ወኪል መሆናቸዉ አያጠያይቅም። የሕዝብን ድምጽ ያሠማሉ፤የሐሳብ ሙግት መፍጠር ይችላሉ። ከዚህ ባለፈ ግን በገዢው ፓርቲ ላይ እዚህ ግባ የሚባል መሠረታዊ የሆነ የፖሊሲ እና የአቅጣጫ ለዉጥ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያህል ሊያመጡ አይችሉም፤ በማለት የግለሰቦችን የፓርላማ ተመራጭነት ፋይዳን ይሞግታል።
በሽግግሩ ዘመን በግል ተወዳድረዉ የሕዝብ ተመራጭ የነበሩት ሻለቃ አድማሴ ዘለቀን የሚጠቅሰው ዮናስ፣ በጊዜው የርሳቸዉን ያህል ሙግትና ክርክር በፓርላማዉ የሚያነሳ ግለሰብ እንዳላየ ያስታዉሳል።
የሚያነሷቸዉ ሐሳቦች ዉኃ የሚቋጥሩ ቢሆኑም እንኳን፣ ሕግ አስፈጻሚዉ ከቁብ ሳይቆጥራቸዉ እንደዋዛ ያልፉቸው ነበር በማለት የግለሰቦች ሚና የሚፈለገዉን ያህል ዉጤት ሊያመጣ እንደማይችል ያስረዳል። የዲ/ን ዳንኤልም ቢሆን ብዙም ከዚህ የተለየ ይሆናል ብሎ እንደማይጠብቅ የሚናገረው ዮናስ፣ የብልጽግና አባል ባይሆንም ( De facto party candidate) የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና የቅርብ ሰዉ በመሆኑ ከዚህ አንጻር የተሻለ ነገር ሊያመጣ ይችል ይሆናል በማለት ምልከታውን ያስቀምጣል። አክሎም የፓርላማ ወንበሩ ለብዙዎች የምርጫ ግለ ታሪካቸዉን ከማጉላት የዘለለ ትርጉም አይኖረዉም በማለት ይተቻል። ከግል ተመራጮች ይልቅ ፓርቲዎች ተጠናክረዉ መንግሥትን መሞገት እንዲችሉ የፓርላማ ወንበሮች የመንግሥት ተፎካካሪ በሆኑ ፓርቲዎች ቢሞሉ ምርጫው መሆኑን ይጠቁማል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አባል የሆነው ብዙአየሁ ወንድሙ ስለግል ዕጩ ተመራጮች ከዮናስ የተለየ ሐሳብ አለዉ። ፓርቲዎች በዉስጠ ዲሲፕሊን ሰበብ የታጠሩ በመሆናቸዉ ከፓርቲዉ ሐሳብ በተጻራሪ ያለን ዕሳቤ ማስተናገድ ይቸግራቸዋል። ለህሊናቸዉ፣ ለመረጣቸዉ ሕዝብ እና ለሕገ መንግሥቱ ከመገዛት ይልቅ የፓርቲዉን ፕሮግራም ለማስፈጸም መሽቀዳደም ዉስጥ ይገባሉ በማለት የፓርቲዎችን ከምንም በላይ “ቅድሚያ ለፓርቲዬ” አካሄድን ይሞግታል። በአንጻሩ የግል ተመራጮች የሕዝብን የልብ ትርታ በማዳመጥ የሕዝብን ቁስል ለመፈወስና መፍትሔ ለመስጠት የሚችሉትን ያህል ይታገላሉ። ሐሳባቸዉ ምላሽ ማግኘት አለማግኘቱ እንዳለ ሆኖ እነሱ ግን በዚህ መንገድ ሊጓዙ ይችላሉ። ለዚህም 1992 ዓ.ም. ከጂማ ተመርጠዉ ወደ ፓርላማ የገቡትን በድሩ አደምን ያነሳሉ። በድሩ በወቅቱ ለነበረዉ ህወሓት መራሹ ፓርላማ የወገብ ቅማል ሆነዉበት እንደነበር ወንድሙ ወደኋላ ተጉዞ ሁኔታዉን ያስታዉሳል። ሻለቃ አድማሴ ዘለቀንም አይዘነጋም። እነዚህ ግለሰቦች ከአንዳንድ ፓርቲ ተብዬዎች በላቀ ደረጃ ሕዝብን አንቅተዋል፤ ስለሕዝብ ተሟግተዋል፤ በማለት የነጠረ ሚና እና የላቀ ሰብዕና ነበራቸው ይላል።
ሲጠቀለል፣ የአገር ልዕልና በሐሳብ ልዕልና የሚመጣ ነው የሚለውን ዕሳቤ በማንገት ሙሓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዘንድሮው ምርጫ ቀዳሚ ሆኖ ወጥቷል። በኃይማኖት፣ በታሪክ፣ በቅርስ፣ በባህል፣ በትውፊትና በማሕበረሰብ ዕሴቶች ላይ የጻፋቸው በርካታ መጻሕፍትና መጣጥፎች ከፍ ወዳለ እርከን መሸጋገር እንዲችሉ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የግል ዕጩ ሆነው ምርጫውን ተወዳድረዋል። ውጤቱን የምርጫ ቦርድ በቅርቡ ያሳውቀናል።
ቅጽ 3 ቁጥር 139 ሠኔ 26 2013



