በምሥራቅ ወለጋ ዞን የጸጥታ ኹኔታ እየተባባሰ በመምጣቱ መቸገራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ

ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ዜጎች መገደላቸው እና መፈናቀላቸዉም ተገልጿል

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣዉ የጸጥታ ችግር አሳሳቢ እንደሆነባቸዉ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአካባቢው ኗሪዎች ተናገሩ።
በተለያየ ጊዜ በታጠቁ ቡድኖች በሚደርስ ጥቃት ቤት ንብረታቸዉን ጥለዉ እየተፈናቀሉና እየተሰደዱ እንደሚገኙ የተናገሩት የጊዳ አያና እና ሀሮ ሊሙ ወረዳ ኗሪዎች፣ በተለይ ባሳለፍነዉ ሳምንት ችግሩ በጣም እየተባባሰ መምጣቱን ይናገራሉ። በዚህ አካባቢ በታጠቁ ቡድኖች በሚደርስ ጥቃት በርካታ የሰዉ ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ ሰዎች ቤት ንብረታቸዉን ጥለዉ ተፈናቅለዋል ሲሉ ኗሪዎቹ ገልጸዋል።

በቅርቡም ሀሮ ሊሙ ወራዳ አጋምሳ በሚባል አካባቢ ቁጥራቸዉ ከመቶ የሚበልጥ ዜጎች በከባድ መሣሪያ መገደላቸውን አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ አረጋግጣለች። በጥቃቱ ሕይወታቸውን ካጡ ዜጎች በተጨማሪ ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መፈናቀላቸውን በአካባቢዉ የነበሩ የዐይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

በደህንነት ስጋት ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአካባቢዉ ኗሪዎች እንደገለፁት፣ በተለይ ልዩ ስሙ አንገር ጉትን ጊዳ አያና ወረዳ መንደር ስድስት በተሰኘ አካባቢ ባሳለፍነዉ ሳምንት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል። “15 ሰዎች በታጣቂዎች ከታገቱ በኋላ በድምጽ አልባ መሳሪያ ሊገድሏቸው መሆኑን በማወቃቸው በአቅራቢያቸዉ በሚገኝ ወንዝ ውስጥ በመግባት ሕይወታቸዉ አልፏል” ከሟቾች መካከልም ለማምለጥ ባደረጉት ሙከራ ኹለቱ ሰዎች በጥይት ተመተዉ የሞቱ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ወንዝ ዉስጥ ወድቀዉ መሞታቸዉን በአካባቢዉ የነበሩ የዐይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በአካባቢው ታጥቆ የሚነቀሳቀሰው “ኦነግ ሸኔ” በተደጋጋሚ በንጹሐን ሰዎች ላይ የሚፈጽመው ጥቃት ከሰዉ ሕይወት መጥፋት አስከ ንብረት ዘረፋ እንደሚደርስ የተናገሩት ኗሪዎቹ፣ ታጣቂ ቡድኑ ይህን ያህል በሰዉ ልጅ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ሲፈጽም እና ንብረት ሲዘረፍ የፌደራል መንግሥትም ሆነ የክልሉ የጸጥታ አካላት ምንም አይነት እርዳታ አለማድረጋቸው ችግሩን እንዳባባሰዉ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በአካባቢዉ ካሉ የመረጃ ምንጮች እንዳረጋገጠችው ችግሩ በመባባሱ እና ታጣቂዎችም ተደጋጋሚ ጥቃት እያደረሱ በመሆኑ፣ አርሶ አደሮች የዘሩትን አዝመራ እንኳን መሰብሰብ ሳይችሉ አካባቢዉን ለቀዉ ወደ ተለያየ ቦታ መፈናቀላቸዉን እና በአሁኑ ሰዓትም ሕይወታቸዉ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ችላለች።

ኗሪዎቹ በተለይም በአካባቢዉ ምንም አይነት የጸጥታ አካላት አለመኖሩን ገልጸዉ፣ የተገደሉ ሰዎችን መቅበር የሚቻልበት ኹኔታ እንኳን ከባድ እንደሆነባቸዉ እና የጥቃቱ ተባብሶ መቀጠልና እልባት አለማግኘት አሳሳቢ ነው ብለዋል።
በጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉትን በተባለ ቦታ የታጣቂ ኃይሉ አባላት የአርሶ አደሮችን ከብቶች በመዝረፍ እና አርቁምቢ መንደር ሦስት በሚባል ቦታም በተመሳሳይ ከብቶችን ዘርፈዉ እና የራሳቸዉን እረኛ ቀጥረዉ እያስጠበቁ እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአካባቢዉ ኗሪዎች መስክረዋል።

የጉትን ከተማ አስተዳደር ችግሩ ከአቅሜ በላይ ነው በማለት ኗሪዎች እራሳቸዉን እንዲጠብቁ መናገሩን የገለጹት አስተያት ሰጭዎቹ፣ ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች እና ባለሥልጣናትም ከተማዉን ለቀዉ እየወጡ መሆናቸዉን ነዉ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ጌታቸው ባልቻ በተደጋጋሚ የስልክ ጥሪና መልዕክት ብትልክም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here