በ2014 ለአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ 3 ቢሊዮን ብር ብድር እንደሚቀርብ ተገለጸ

የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን በ2014 በጀት ዓመት ለኹለት ሺሕ 973 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች 3.17 ቢሊዮን ብር የሥራ ማስኬጃና የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ብድር እንደሚያቀርብ አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ በ2014 በጀት ዓመት 1.6 ቢሊዮን ብር ለ1553 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስሪዎች የሥራ ማስኬጃ ብድር ለማቅረብ ማቀዱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ለ1420 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ 1.5 ቢሊዮን ብር የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ብድር እንደሚያቀርብ ገልጿል።

ባለሥልጣኑ በ2013 በጀት ዓመት ከ962 ሚሊዮን ብር በላይ ለ716 ኢንዱስትሪዎች የሥራ ማስኬጃ ብድር ያቀረበ ሲሆን፣ ለ907 የካፒታል ዕቃ ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች 867 ሚሊዮን ብር ብድር ማቅረቡን አስታውሷል።
የአነስተኛ እና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አሸናፊ መለሰ እንደገለጹት፣ ተቋሙ በዋናነት ሦስት ተግባራትን ለማከናወን እየሠራ ሲሆን፣ እነዚህም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን መፍጠር የሚያስችሉ ተግባራትን መከወን፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉትን ማጠናከር እና በዘረፉ የተሻለ የገበያ ትስስር፣ በተለይ በዋናነት ከውጭ አገራት ጋር፣ እንዲኖራቸው መጣር እና በሽያጭ እና ግዢ ላይ ያለውን ሥራ የተሻለ ማድረግ እንደሆነ ጠቁመዋል።

አሸናፊ አያይዘውም በበጀት ዓመቱ ወደ 1.6 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ሥራ ለማስጀመር፣ የተለያዩ ጥሬ ዕቃዎችን ለመግዛት እና የሠራተኞች ደሞዝ ለመክፈልም ጭምር የሚውል ሲሆን፣ 1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ደግሞ የተለያዩ ማሽነሪዎችን ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገር ለመግዛት እና አዳዲስ ዕቃዎችን ለማስገባት እንደሚውል ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ክሬቲቭ ሃብ (Creative Hub) የተሰኘ አዳዲስ ሐሳብ ያላቸውን ሥራ ፈጣሪዎች በዲጅታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም ወደ ምርት እንዲገቡ የሚያስችል ክህሎት እንዲጨብጡ የሚያደርግ አዲስ ወርክ ሾፕ ተከፍቶ ሥራ ላይ መዋሉን ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ይህ አዲሱ ወርክ ሾፕ በተለያዩ የግል እና የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች፣ ሐሳብና ሥራ ፈጣሪዎች፣ እንዲሁም በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ በዘርፉ ሐሳብ ያላቸው ግለሰቦች ዕቅዳቸውን ወደ ተግባር መቀየር የሚያስችላቸው ነውም ተብሏል።

ባለሥልጣኑ በ2013 በጀት ዓመት 907 የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች ጋር እንደሠራ የተገለጸ ሲሆን፣ በአዲሱ በጀት ዓመት ዕቅድ እነዚህን የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ተጠቃሚ ኢንደስትሪዎች ወደ አንድ ሺሕ 420 በማድረስ በአራት ሺሕ 25 ሔክታር መሬት ላይ ተጨማሪ ኢንዱስትሪዎችን ለመፍጠር መታቀዱ ነው በሪፖርቱ ላይ የተጠቀሰው።

በ2013 በጀት ዓመት ከነበረው የሥራ አፈጻጸም በተሻለ ለመሥራት የታቀደ መሆኑ እና ባለፈው ዓመት 436 ከነበረው የማምረቻ ቦታ ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች፣ በ2014 ወደ አንድ ሺሕ 717 ለማድረስ እንደሚሠራም ባለሥልጣኑ ባወጣው ሪፖርት ተጠቅሷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here