‹ሬይስ ማይክሮ ፋይናንስ› የ ‹ዲጂታል› ብድር መስጠት ሊጀምር መሆኑን አስታውቀ

0
549

ሬይስ ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ. በ‹ሳሃይ ፔይ› አማካይነት የዲጂታል ብድር እና የኢንተርኔት መገበያያ መተግበሪያን በጣምራ ከሰሞኑ ሥራ ላይ እንደሚያውል ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
በሬይስ ማይክሮ ፋይናንስ የበልጸገው ‹ሳሃይ ፔይ› በመባል የሚታወቀው የተንቀሳቃሽ ገንዘብ መላላኪያ መተግበሪያ በሱማሌ እና አጎረባች ክልሎችን ጨምሮ በጎረቤት ኬንያ ድንበር አካባቢ በፍጥነት በማደግ ላይ ይገኛል ።

አዲሱ የመገበያያ እና ዲጂታል ብድር አቅርቦት ዘዴ ከጎረቤት አገራት በተለይም በኬንያ ልምድ ተወስዶ የበለጸገ መሆኑን የሰሃይ ፔይ ሥራ አስፈጻሚ እና የሬየስ ማይክሮ ፋይናንስ መሥራች አባል አብዲአዚዝ ሐሰን ገልጸዋል ።
ሰሃይ ፔይ በቅርቡም ኢስላማዊ መርህን እና የሸርዒያ ህግጋትን መርህ ያደረገ ዲጂታል ‹ሙዳራባህ› የብድር አገልግሎት ከተቀላጠፈ የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ መተግበሪያ ጋር ይፋ እንደሚያደርግ ለአዲስ ማለዳ አሳውቋል ።

“ተቋሙ መሠረቱን የጣለው በሱማሌ ክልል በመሆኑ የተቋሙ ደንበኞች በአብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታዮች ስለሆኑ ኢስላማዊ መርህን የተከተለ ዲጂታል ብድር ለመስጠት እየተንቀሳቀሰስን ነው፤ የብድሩ መጠንም የሚወሰነው የደንበኛው ግብይት እና ተቀማጭ መሠረት ባደረገ መልኩ ሊሆን ይችላል” ሲሉ አብዲአዚዝ ሐሰን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል ።

የኤሌክትሮኒክ መገበያያው ‹ስማርት ኪዮስክን› እንደሚጨምር እና ይህም የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚፈልገውን ዕቃ ማግኘት ባይችል እስከ አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት የሚፈጀውን ጊዜ እና የሚደርስበትን እንግልት ለመቀነስ ታስቦ የተሠራ መሆኑ ተገልጿል።
ይህን መገበያያ ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ ከብድር አገልግሎት ጋር አጣምረን፣ ለማከፋፈያዎች እና ትዕዛዝ አድራሾችም ጭምር በቅርቡ አገልግሎት ለመስጠት እየተዘጋጁ እንደሆነ አብዲአዚዝ ገልጸዋል።

ጌቱ ሚሊዮን በዲጂታል ባንክ ዘርፍ ከ12 አመት በላይ በተለያዩ ባንኮች የሠሩ ሲሆን፣ “ተመሳሳይ ችግር በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋል ነው፤ የክፍያ አማራጮች እየበዙ ቢሆንም ተጠቃሚው ግን እምብዛም ነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል
የሬየስ ማይክሮ ፋይናንስ እህት ኩባንያ በ ሴኮንድ 1 ጊጋ ባይት ማስተናገድ የሚችል የራሱ ‹ሰርቨር› አለው የተባለ ሲሆን፣ በ2ጂ እና 3ጂ ኔትዎርክ መሥራት የሚችሉ የ‹አንድሮይድ እና አይ.ኦ.ኤስ› መተግበሪያዎች፣ እንዲሁም በ‹ዩ ኤስ ኤስ ዲ አችር› ቁጥር ለየትኛውም ዓይነት ስልክ ተጠቃሚ ምቹ ሆኖ የተዘጋጀ ነው።

የፋይናንስ መሠረተ ልማት አንድ ችግር ቢሆንም፣ በነጋዴው እና በሸማቹ መካከል ያለው የእውቀት ክፍተት ግን ዘርፉ ላለመሻሻሉ በተለይም በከተማ እንደ አንድ ምክንያት ነው ብለዋል። ባንኮችም ሆነ ‹ዋሌቶች› እና ሌሎች የክፍያ አማራጮች ምርታቸውን ለገበያ ከማዋላቸው በፊት እውቀት ማስጨበጥ ላይ ቢሠሩ የተሻለ ውጤት ይመጣል ተብሏል።

በተጨማሪም፣ መንግሥትም በደንብ ትኩረት ሠጥቶ ሊሠራበት እና ሊያበረታታው የሚገባ ዘርፍ ነው። ገንዘብ ወደ ዲጂታል መስመር ሲገባ መንግሥት ገንዘብ ለማተም የሚያወጣው ወጪ ይቀንሳል። በተጨማሪም ሕገ ወጥ ግብይቶችን መቆጣጠር ያስችላል የሚል ዕምነት አለ።
ባሳለፍነው ሳምንትም ሬይ ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ. ከ460 በላይ ቅርንጫፍ ካለው አዋሽ ባንከ ጋር የተጣመሩበትን መተግበሪያ በይፋ ያስመረቀ ሲሆን፣ በጥምረታቸውም የትኛውም የሳሃይ ፔይ ተጠቃሚ የትኛውም የአዋሽ ባንክ ኤቲኤም ባለበት ቦታ ያለ ካርድ ገንዘብ ወጪ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ይፈጥራል ።

በተመሳሳይም የአዋሽ ባንክ ሒሳብ ያለው ደንበኛ በየትኛውም አካባቢ በተለይም የባንክ አገልግሎት ማግኘት በማይቻልባቸው ገጠራማ ቦታዎች፣ የሰሃይ ወኪል ባለበት አካባቢ ገንዘብ ማዘዋወር የሚያስችል ጥምረት ከአዋሽ ባንክ ጋር እንደፈጸሙም አብዲአዚዝ ገልጸዋል ።
ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ እና ከ 76 ቢሊዮን ብር በላይ የደንበኞች ተቀማጭ ሒሳብ ያለው አዋሽ ባንክ፣ በቀጣይ ባንክ ወዳልደረሰቸው አካባቢዎች፣ በተለይም ወደ ምስራቅ ሐራርጌ እና አንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች እንደ ሰሃይ ባሉ መተግበሪያዎች ደንበኞችን ለማፍራት ዕቅድ መያዙን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የባንኩ የዲጂታል ዘርፍ የሥራ ኃላፊ ጠቁመዋል። ከሰሃይ ጋር በመሥራታችን በተለይም አርብቶ አደሩ አካባቢ ያሉ ማኅበረሰቦች ከቦታ ቦታ ስለሚዘዋወሩ ቴክኖሎጂው የባንክ አገልግሎት የማግኘት ዕድላቸውን ከፍ ያደርገዋል ሲሉም ገልጸወል ።

በአሁኑ ሰዓት ወደ አንድ ሚሊዮን የሰሃይ ፔይ ተጠቃሚ ሲኖር፣ በቀን ከ920 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ወይም የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here