ፈንድቃ – የነገ ባህል ማእከል

Views: 167

ካዛንችስ አካባቢ ጥቂት የማይባሉ የአዝማሪ ቤቶች ይገኙ ነበር። ሆኖም በአካባቢው መልሶ ማልማትና መሰል ምክንያቶች በርካቶቹ ሲፈርሱና ቦታውን ለቀው ሲሄዱ፣ ጸንቶ በቦታው ሊቀር የቻለው አንዱ የባህል ቤት ፈንድቃ ነው። ስምረት ሺፈራው እንደ ፈንድቃ ባሉ የባህል ቤቶች ውስጥ የባህል ሙዚቃዎችን ከጓደኞቿ ጋር ሰብሰብ ብላ መስማት ትወዳለች። ፈንድቃ ውስጥ ጊዜ ጠብቀው በወር እንዲሁም በሳምንት በሚቀርቡ ክዋኔዎች ላይ በቻለች መጠንና በተመቻቸላት ጊዜ የመታደም ልምድ እንዳላት ትጠቅሳለች።

‹‹ጊዜና የሥራ ሁኔታ በፈቀደልኝ ጊዜ ፕሮግራሞች ሲኖሩ እታደማለሁ። ቤቱም ከውጪ እንደሚታየው አነስ ያለ ሳይሆን ብዙ ቁምነገርን በውስጡ የያዘ ነው።›› ስትል ለአዲስ ማለዳ አስተያየቷን ሰጥታለች። በቤቱ የሚቀርቡ የአዝማሪ ሙዚቃዎች፣ ውዝዋዜዎችና ትርዒቶችም ቤቱን የባህል ማእከል ቢያሰኙት እንደማይበዛበት ፈገግታን ተሞልታ ስምረት ገልጻለች። ውዝዋዜ የተባለ እንደሆነ ታድያ መላኩ በላይ ሥሙ ሲጠራ የሚያውቀው ሁሉ አስቀድሞ የሚያስታውሰው ጉዳይ ነው። የማያባራ እንቅጥቅጡና የተለያዩ ብሔረሰቦች ውዝዋዜ የሚያቀርብበት መንገድ በብዙዎች ትኩረት እንዲሰጠው አድርጎታል።

ይህም አንዴ ከተመለከተው ዐይን የሚጠፋ አይደለም። ይህ ሰው የውዝዋዜና የሙዚቃ ፍቅር መቼ ጀምሮ ያዘህ ቢባል፣ ‹‹ገና ከእናቴ ሆድ ውስጥ እያለሁ ነው የጀመረኝ›› ይላል። ከዛ በተረፈ ግን ያደገበትና የኖረበት ማኅበረሰብ ያፈራውና ያቆየውን ነገር በተለያየ ማኅበራዊ አጋጣሚ ሊሰጠው እንዳልሰሰተ በኩራት ይገልጻል። ከጥምቀት ደማቅ አከባበር ጀምሮ የተለያዩ በዓላትን ተከትሎ ከሚስተዋሉ ትውፊታዊ ክዋኔዎች፣ ሙዚቃዎችና ውዝዋዜዎች ጋር አብሮ አድጓልና። ይህ ሰው አሁን ላይ ፈንድቃን በባለቤትነት እንዲሁም በሥራ አስኪያጅነት እየመራ ይገኛል።

ቤቱ የኢትዮጵያን ባህል በሁሉም አቅጣጫ ታሳቢ ያደረገ ሆኖ እንዲቀጥልም የተቻለውን እያደረገ ስለመሆኑ ለአዲስ ማለዳ አጫውቷታል። በፈንድቃ ምን ተሠራ? መላኩ ከልጅነት እስከ እውቀት በትዝብቱ መካከል ውሎ ያሳስበው የነበረ ጉዳይ ከአዝማሪዎች ጋር የተገናኘ ነው። ይህም እንደሚታወቀው በትላልቅ ድግሶችና ክዋኔዎች ላይ ዘመናዊ ባንድ የሚከፈለውና የሚጠራበት ዋጋ ቀላል አይደለም።

ያም ሆኖ አዝማሪ ይጠራ የተባለ እንደሆነ ‹‹ሽልማት አለው፤ ምግብ አለ›› ተብሎ በስሱ ይታለፋል እንጂ ራሱን የቻለ ክፍያ የሚቀበለው ከብዙ እጅግ ጥቂቱ ነው። ‹‹ይህ ነገር ሰው ለአገሩ ባህል ያለው ግምት ምን ያህል ዝቅተኛ እንደሆነ ማሳያ ነው›› ይላል መላኩ። በእርግጥ እንኳንና በመኖሪያ ቤቶች፤ በአዝማሪ ቤቶች ውስጥም የቤቱ ባለቤቶች የሥራውን ገቢ ለራሳቸው ሲወስዱ አዝማሪው ግን ከአድማጭና ተመልካች የሚሰጠው ሽልማት ወይ ጉርሻ ነበር ገቢው።

ለዛም ነው ‹‹ተቀበል!›› የተባለውን ሁሉ ያለማንገራገር የሚቀበለው። አልፎም ስድብና ምፀት አዘል ግጥሞችን ሲያቀርቡ ሰዎች የበለጠ ስለሚዝናኑና ስለሚስቁ፤ ይህም የተሻለ ጉርሻ እንዲያገኙ ስለሚያስችላቸው፣ ትርፍ ለማግኘት ሞያው ወደ ጎን ይቀመጣል። ይህ ነገር በአንድ ጎን አዝማሪው ስለ ጥበብ የሚያስብ ሳይሆን የእለት ገቢው ብቻ የሚያስጨንቀው እንዲሆን አድርጓል።

በሌላ በኩል ‹አንዳንድ› ከሚለው ሻገር የሚል ቁጥር ያለው ታዳሚ፣ ስድቡን በመፍራትና በመጥላት ከአዝማሪ ቤቶች ገለል እንዲል ያደረገ ነው። ይህን ሁሉ ችግር ለመፍታት መላኩ በፈንድቃ የተጠቀመው ዘዴ ለባለሙያዎች ቋሚ ደመወዝ መስጠትን ነበር። ይህም ለባለሙያዎቹ ድጋፍ ከመሆኑ ባሻገር ሌሎችን ተተኪ ባለሙያዎች ለማፍራትም ብዙ እድል የከፈተ ነው። በፈንድቃ ስለ ጥበብ ብቻ ይታደራል፤ ስለ ጥበብ ብቻ ይዘመራል። ከዚህም ጋር በተያያዘ መላኩ ራሱ ሙያዊ ሥልጠና ብቻ ሳይሆን በሥነ ልቦናም ከወጣቶቹ ጋር እንደሆነ ይጠቅሳል። ይህ እንቅስቃሴው ውጤታማ ለመሆኑ ማሳያ የሚሆኑደግሞ ውጪ አገራት የሚደረጉ ጉዞዎች ናቸው።

ባለሙያዎቹ ባህል ለማስተዋወቅ እንዲሁም በግብዣ ወደ ተለያዩ አገራት የሚሄዱባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው። በዚህ አጋጣሚ ታድያ ዘርፉ የተዘነጋ መሆኑን ቢያውቁም፣ ለሙያው ያደሩ በመሆናቸው ተመልሰው ወደ አገራቸው ይመጣሉ። ይህም በሥነልቦና በኩል ሙያውን ለግል ጥቅሙ የሚያውልና የሚገለገልበት ባለሙያ ሳይሆን፤ ራሱን ሙያውንና ጥበቡን ለመጠበቅ የተሰጠ ባለሙያ በማፍራት በኩል ከፍተኛ ሚናውን እንደተጫወተ መላኩ ይገልጻል። መላኩ ከዓመታት በፊት ፈንድቃን በእጁ ካስገባ በኋላ በቤቱ በርካታ ለውጦችን አድርጓል። በአንድ ጎን ብዙዎች የሚያነሱትን ሐሳብ ያነሳል፤ ይህም ቦታው የደከመና የድሮ መሆኑን ነው።

ካዛንችስ አካባቢ የነበሩ በርካታ የአዝማሪ ቤቶች አሁን ላይ ጨርሶ የሉም በሚያስብል ደረጃ ጠፍተዋል። ያም ብቻ አይደለም በመልሶ ማልማት ሰበብ በአካባቢው ያሉ የቆዩ ቤቶች ፈርሰው ደብዛቸው ጠፍቷል። በዚህ መካከል ፈንድቃ የሚገኝበትን አነስተኛ የሚመስል ቤት ሊያፈርስ ያልፈቀደው ቤቱ ለአካባቢው የተረፈ ቅርስ በመሆኑም ነው። ሌላው ቀርቶ የውስጥ ግንባታና አሠራርን በተመለከተ ‹‹ሴራሚክና ፍሪጅ የመሰለ ግንባታ በለመደ ዐይን፣ ተመልካች ወፍጮ ቤት ይመስለዋል›› ሲል መላኩ ዙሪያ ገባውን እያየ በፈገግታ ገለጸ።

ይሁንና ቤቱ በምሽት አገልግሎቱን ሲሰጥ ግን ሁሉም በተገቢው ቦታ እንደሚገኝ ለማወቅ አያስቸግርም ይላል። በፈንድቃ ጊቢ ውስጥ የስዕል አውደ ርዕይ፣ የግጥም ዝግጅትና መሰል ጥበባዊ ክዋኔዎች ይሰናዳሉ። በተለይም የስዕል አውደ ርዕይ በየወሩ የሚካሄድ ሲሆን፤ ይህንንም አገልግሎት ፈንድቃ በነጻ የሚሰጠው ነው። በተለይም መተንፈሻ የሆኑና በቦታ ማጣትና እጥረት ምክንያት ክህሎታቸውን እንዲደብቁ የተገደዱ ወጣቶች ስለ ገንዘብ ሳያስቡ የሚተነፍሱበት፤ ሰዓሊዎች ሥዕሎቻቸውን የሚሸጡበት እንዲሁም ለእይታ የሚያቀርቡበትን መድረክ ነው ፈንድቃ ያመቻቸው።

ወደ ውዝዋዜ እንመለስ፤ የውዝዋዜ ባለሙያ የሆነው መላኩ፤ ዘመናዊ ወይም ባህላዊ በሚባል ውዝዋዜ መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ እንደሚቸገር ይናገራል። እንደውም ዘመናዊና ባህላዊ የተባለ እንደሆነም፤ እነዚህ አባባሎች መካከል ያለው ልዩነትም ሆነ እይታ ጤናማ ነው ብሎ አያስብም። በተለይም ‹‹ዘመናዊነት ማለት የራስን ነገር አውቆና ተረድቶ በአግባቡ መያዝ ነው›› ብሎ የሚያምነው መላኩ፤ መሰንቆን ጥሎ ጊታርን መያዝ ምኑ ጋር ዘመናዊነት እንደሆነ ወይም ዘመናዊ ማለት በራሱ ትርጉሙ ምን እንደሆነ መልሶ ይጠይቃል።

በፈንድቃ የአዝማሪ ሙዚቃን ዳግም መቀስቀስ ላይ ያተኮረ አንድ ፕሮጀክት መላኩ አዘጋጅቶ ነበር። ይህ የእቅድ ሥራ በጊዜው ከተወዳደሩ በቁጥር 900 የሚሆኑና ከ20 አገራት የተውጣጡ ወረቀቶችን ማሸነፍ የቻለ ነው። መላኩ በዚህ አሸናፊነት አምስት መቶ ዶላር ሽልማት ያገኘ ሲሆን፤ ሽልማቱንም ለግሉ ከማዋል ይልቅ ከተለያዩ ክፍላተ ኢትዮጵያ በተለያየ ቋንቋ የአዝማሪ ሙዚቃ የሚያቀርቡ ባለሙያዎችን አምጥቶበታል። እናም አዝማሪ ሲባል በፈንድቃ አዳራሽ በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በኦሮምኛና በትግረኛ እንዲሁም በሌላውም የሚቀርብ ነው። እነዚህ ሁሉ ተግባራት በፈንድቃ ሲከናወኑ በሚገርም ሁኔታ ግን ቢሮ የለውም።

ይህንንም ጥያቄ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያቀረበ ቢሆንም፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ‹‹ጠይቁኝ›› ከማለት ውጪ ምንም የሰጠው ተግባራዊ ምላሽ የለም። ያም ሆነ ይህ ፈንድቃ በኅብረ ቀለማቱ ድምቀትና በሥራ ፈጠራና በኣዳዲስ ሐሳቦች ምክንያት፤ የባህል ማእከል ለሌላት አዲስ አበባ አንድም የባህል ማእከል ዓይነት ድርሻን እየተወጣ እንዳለ ግልጽ ነው። ፈንድቃ የባህል ምሽት ቤት ከመሆኑ ሌላ ‹ኢትዮ ከለር› የባህል የሙዚቃ ቡድን አቋቁሞ በወር ኹለት ጊዜ የሙዚቃ ድግሶችን ያቀርባል።

ይህም በንቀት ለሚታየውና ‹ሽልማትና ምግብ በቂው ነው› የሚሰኝለትን አዝማሪነት፤ ከፍለውበት የሚታደሙበት መርሃ ግብር ያደረገ እንቅስቃሴ ነው። ከውጪም የተለያዩ ሰዎች ለፈንድቃ ትኩረት እንዲሰጡ ያስቻለው፤ በልዩነት ብቻውን እና በአዳዲስ የፈጠራ ሐሳቦች ብቅ ማለት በመቻሉ ነው። ይህም መላኩን የሚያስመሰግን ሆኖ፣ በዚህ ላይ ለተሠማሩትም አዳዲስ ሐሳብን በማምጣት ሊሠሩበት የሚችሉት ሰፊ መስክ እንዳለ ማሳያ ይሆናል።

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com