የአስችኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ መመሪያን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ባለሙያዎች

0
801

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዙ ኅዳር 22/2014 ማምሻ ላይ ባደረገው ስብሰባ፣ የዐዋጁን አፈጻጸም ገምግሟል። በግምገማውም አዋጁን በመፈጸም ረገድ የሕዝቡ ተነሳሽነትና ቆራጥነት የሚደነቅ በመሆኑ ምስጋና አቅርቦ፣ ያገኘኛቸውን ተደጋጋሚ ድሎች ጠብቆ ለማስቀጠል እንዲቻልም የሚከተሉትን ትዕዛዞች አስተላልፏል።

1. ከአሸባሪው የህወሐት ዕጅ ነጻ በወጡ አካባቢዎች ሠላምንና ጸጥታን ለማስፈን እንዲሁም የሕዝብንና የንብረትን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ የሰዓት ዕላፊ ታውጇል።

2. ከአሸባሪው ህወሐት ነጻ በወጡ አካባቢዎች የታወጀውን የሰዓት ዕላፊ በተመለከተ ወደ አካባቢው የገቡ የመንግሥት የጸጥታ አካላት፣ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ፣ እንዲሁም የሰዓት ዕላፊውን እንዲያስፈጽሙ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

3. ከአሸባሪው ህወሐት ነጻ በወጡ አካባቢዎች፣ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በክልሉ መንግሥት ከሚመደብ ሲቪል አስተዳደር ጥምር ኮሚቴ በአስቸኳይ እንዲቋቋም። በዚህ ኮሚቴ አማካይነት በአሸባሪው ወራሪ ኃይል በመንግሥት ተቋማት፣ በግለሰብ ንብረቶች፣ በማኅበራዊ ተቋማትና በመሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመትን የሚያሳዩ ማስረጃዎች እንዳይጠፉ እንዲጠበቁ፣ በተገቢው መንገድ እንዲመዘገቡ፣ ማስረጃዎችም እንዲሰነዱ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዙ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

4. የፍትሕ አካላት በየቦታው ከተቋቋሙ ጥምር ኮሚቴዎች ማስረጃዎችን ተቀብለው በማደራጀት ለሚመለከተው አካል እንዲያስረክቡ ታዟል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በሚያጸድቅበት ጊዜ፣ ይህ አካል በተለያዩ ጊዜ፣ እንደአስፈላጊነቱ የተለያዩ መመሪያዎች እና ደንቦችን፣ እንዲሁም መግለጫዎችን በማውጣት ተግባር ላይ እንዲውሉ የማድረግ ሙሉ ሕገ-መንግሥታዊ መብት ተሰጥቶታል። በዚህ መሰረት ኅዳር 22/2014 ባደረገው አሰቸኳይ ስብሰባ፣ በህወሓት ቡድን ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ፣ ከላይ የተገለጹትን አራት ትዕዛዛት አውጥቷል።

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ጦርነቱ ከተጀመረ አንድ አመት አልፎታል። በዚህ ጦርነት፣ ከ 200 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም፣ 7 ሚሊዮን ሕዝብ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በጦርነቱ ለችግር ተዳርጓል። የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ባወጣው መረጃ መሠረት፣ ከ 2 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ቤት ንብረቱን በመተው ተፈናቅሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ የወደሙትን ንብረቶች፣ መሠረተ ልማቶች፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ተቋማትን፣ ወደቀደመ ሁኔታቸው ለመመለስ በማሰብ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ ከላይ የተጠቀሱትን መመሪያዎች ተግባር ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ ጀምሯል። መመሪያውን መሬት ላይ ከማውረድ እና ተግባራዊ ከማድረግ፣ እንዲሁም ሊገጥሙት ከሚችሉት ተግዳሮቶች አንጻር፣ ከዚህ ባለፈም የመመሪያዎቹን ክፍተት፣ የሕግ ባለሙያና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ የሆኑትን አለልኝ ምህረቱ ሐሳብ እንዲሰጡበት አዲስ ማለዳ አነጋግራቸዋለች።

እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ ያወጣው መመሪያ ተገቢና ወቅቱን የዋጀ ነው። አሻራዎችና ማስረጃዎች ከመጥፋታቸው በፊት ጊዜ ባለመስጠት እንዲጣራ መመሪያ መውጣቱ ተገቢ ነው። በተጨማሪም፣ የጸጥታ አካሉ ከሲቪል ማኅበረሰቡ ጋር በመጣመር ፣የአስገድዶ መድፈር፣ የንጹኃን ጭፍጨፋ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙን ለመለየት ጥናት እንዲጠና መደረጉ አዎንታዊ ነው በማለት መመሪያውን ደግፈውታል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለእስቸኳይ ጊዜ አካል በዐዋጅ የሰጠው መብት አለ። እሱም፣ መመሪያዎችንና ደንቦችን ማወጣት፣ መተግበር፣ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ኮሚቴ ማቋቋም፤ ከጸጥታ ኃይሎች እና ከመንግሽት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመቀናጀት አስቸኳይ ሥራዎችን ማከናወን፣ እንዲሁም ፣ከተለያየ የሥራ መስክ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ እና ኮሚቴ በመመስረት፣ ከመደበኛው ውጪ አስቸኳይ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ማድረግና የመሳሰሉትን የማከናወን ሕጋዊ መሠረት አለው።

ከላይ የተገለጹት መመሪያዎችን ለመተግበር በቅንጅት እና በተደራጀ የሰው ኃይል ከተሠራ በጣም ቀላል እና በተፈለገው ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል የሚሉት ባለሙያው፣የመጀመሪያው የሰዓት ዕላፊ ገደብ የሰብዓዊ መብት ሳይጣስ የአስፈጻሚ አካላት ጥንቃቄ የተሞላ ሥራ ከታከለበት ግቡን መምታት እና ተግባራዊነቱን ዕውን ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል። ሲቪሉ ማኅበረሰብ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመጣመር፣ ወራሪው ኃይል በመንግሥት ተቋማት፣ በግለሰብ ንብረቶች፣ በማኅበራዊ ተቋማት፣ እና በመሠረተ ልማቶች ያደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመትን የሚያሳይ ማስረጃዎች እንዳይጠፉ፣ እንዲጠበቁ ፣ በተገቢው መንገድ እንዲመዘገቡ ብሎም ማስረጃዎችም እንዲሠነዱ ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህንን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ ባለሙያው ይጠቅሳሉ። ለምሳሌ፣ የሕግ ባለሙያዎች የተፈጸሙትን ወንጀሎች ለማጣራት ያስፈልጋሉ። ትንታኔ በመስጠት እና ከሕግ አንጻር ምን አይነት ማስረጃዎች እንደሚያስፈልጉ ሙያዊ ምከር ይሰጣሉ።

በጦርነቱ የተጎዱ ሕፃናትና ሴቶች፣ እንዲሁም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን፣ የሥነ-ልቦና ሥብራት ጥናት ለማድረግ የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉ አለልኝ ምህረቱ ጠቁመዋል። ከነሱ በተጨማሪ፣ ተጨባጭ የሕክምና ማስረጃ ለማቅረብ እና አስፈላጊውን ሐተታ ለመስጠት የሕክምና ባለሙያዎች ሊካተቱ ይገባል። የኢኮኖሚ አጥኒ ባለሙያዎች የወደመውን ንብረት፣ የጠፋውን መሠረተ ልማት በዝርዝር ለማስረዳት እንደሚያስፈልጉ ባለሙያው ተናግረዋል።ከዚህ በተጨማሪ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ በጦርነት የተጎዱትን ክልሎች የወደፊት የኢኮኖሚ ሁኔታ ትንበያ እንዲሰጡ ይጠበቃል። ሌሎችም በየሙያ ዘርፉ እንደአስፈላጊነቱ ተመድበው የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ አበርክቶ ካደረጉ ሥራውን በሚገባ እና በተፈለገው ጊዜ ማድረስ ይቻላል።

የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪው አክለውም ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መመሪያ የአገሪቱን አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የሚወጣ ነው። ስለሆነም መመሪያው የሚመለከተው አካል የማስፈጸም ግዴታ አለበት በማለት ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ያላካተተውን ወይም ቢያካትተው መልካም ውጤት ያመጣል ብለው ያሰቡትን ባለሙያው ዘርዘር አድርገው ሲገልጹ፤ አንደኛ ፣ ከአሸባሪው ነጻ የወጡ አካባቢዎች የታወጀውን የሰዓት ዕላፊ በተመለከተ፣ ህወሓት በያዛቸው ቦታዎች በየጥጋጥጉና በየሸጡ ተቆርጠው የቀሩ የህወሓት ርዝራዦች መኖራቸው ስለማይቀር መመርያው አግባብ ነው ይላሉ ። ይሁን እንጂ፣ ወደአካባቢው የገቡ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲሰጡ ከሚል ይልቅ፣ ከሕዝቡ በተውጣጡ አካላት ትምህርቱ ለሕዝቡ እንዲደርስ ቢደረግ ውጤታማነቱ ይጨምራል። ምክንያቱም ሕብረተሰቡ ቅርቡ የሆነው አካልን የበለጠ የማመን ዝንባሌ ስለሚኖረው ነው ብለዋል። በተጨማሪም ከሕዝቡ የተውጣጡ የሲቪል አካላት፣ የሚኖሩበትን የሕብረተሰብ ሥነ-ልቦና መረዳት ስለሚችሉ ለሕዝቡ ግንዛቤ በመስጠት ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖራቸዋል። ስለዚህ በቀላሉ መመሪያው ተግባራዊ እንዲሆን ያግዛል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ኹለተኛ የፍትሕ አካላት በየቦታው ከተቋቋሙ ጥምር ኮሚቴዎች ማስረጃዎችን ተቀብለው በማደራጀት፣ለሚመለከተው አካል እንዲያስረክቡ የሚለው ትዕዛዝ ክፍተት እንዳለው ገልጸዋል። የፍትሕ አካላት ማስረጃዎችን፣ አስተያየቶችን ከጥምር ኮሚቴው ከመጠበቅ፣ ራሳቸው ቀጥታ ተሳታፊ በመሆን ማስረጃዎች እና መረጃዎች መሰብሰብ ቢችሉ የተሻለ አፈጻጸም ይኖረዋል። ባለሙያው፣ የፍትሕ አካላት ወንጀል ነክ ጉዳዮችን፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በውስጥ ገብተው እንዲያጠኑ ማድረግ ተገቢ ነው ያሉ ሲሆን፣ የፍትሕ አካላቱ ግንዛቤ እና በጉዳዩ ላይ በቂ ዕውቀት ስለሚኖራቸው ጉዳዩን ቶሎ ቶሎ ተከታትሎ ሪፖርት ለማድረግ ያግዛሉ ብለዋል።

ይሁን እንጂ፣ ይህ የሆነው ከሕጉ አንጻር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በቀጥታ የፍትህ አካላቱን የማዘዝ ሕጋዊ መብት ስለሌለው ሊሆን እንደሚችል አልሸሸጉም። ነገር ግን፣ የተፈጸሙ ወንጀሎችን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከማጥናት አንጻር፣ ዐቃቤ ሕግ ማጥናቱ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው። የፍትሕ አካላቱም እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን አካል በማሳወቅ መሳተፍ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በሦስተኛ እና በመጨረሻ ደረጃ ያስቀመጡት፣ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የተለያዩ ባለሙያዎች ሙያዊ አስተዋጾ ቢያደርጉ፣ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ቀላሉና አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ነው። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዙ፣ በቀጣይም ዝርዝር መመሪያዎችን እና ተጨማሪ ማብራሪያዎች ሊያወጣ እንደሚችል በመጠቆም አስተያታቸውን አጠቃለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here