የአቢሲኒያ ባንክ አጠቃላይ የሀብት መጠን በአንድ ዓመት ውስጥ የ56 ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳየ

0
1005

አቢሲኒያ ባንክ ሰኔ 30/2013 በተገባደደው 2020/21 በጀት ዓመት የተከፈለ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ በ2019/20 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከ56.89 ቢሊዮን ብር ወደ 103.85 ቢሊዮን ብር ማደጉ ተገለጸ።
ለጭማሪው እንደ ዋና ምክንያት የተጠቀሰው የብሔራዊ ባንክ ቢልን ጨምሮ የተደረጉ የመወዕለ-ነዋይ ፍሰቶች፣ ቋሚ ንብረቶች እና በዋነኝነት 75.45 ቢሊዮን ብር የሚደርሰውን ብድርና ቅድመ ክፍያዎች እንደሆኑ ለማወቅ ተቸሏል። የባንኩ አጠቃላይ የሀብት ዕድገት መጠን 82.5 በመቶ ሆኗል።

የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከባለፈው በጀት ዓመት ማለትም 2019/20 ጋር ሲነጻጸር ከ3.15 ቢሊዮን ብር ወደ 5.18 ቢሊዮን ብር ማደጉ ታውቋል። ይህም የባንኩ የተከፈለ የካፒታል መጠን በ64.6 በመቶ ማደጉን ያሳያል።
አሁን ላይ የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል የ52.3 በመቶ ዕድገት በማሳየት 8.65 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የባንኩ አጠቃላይ መጠባበቂያ ገንዘብ የ334.89 ሚሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት 1.5 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመላክቷል።

የአቢሲኒያ ባንክ የበጀት ዓመቱ አጠቃላይ ገቢ 10.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ካለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 4.4 ቢሊዮን ብር ወይም የ79 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የባንኩ ቦርድ ሰብሳቢ መኮንን ማንያዘዋል ተናገረዋል። ሰብሳቢው አክለውም፣ ከተገኘው ገቢ 8.15 ቢሊዮን ብር ወጪ መድረጉን ጠቁመዋል።

ሰብሳቢው እንደሚሉት፣ ለወጪው መጨመር የአንበሳውን ድርሻ በዋናነት የሚይዘው የተቀማጭ ገንዘብ ማደግን ተከትሎ የተከፈለው ወለድ ሲሆን፣ ይህም ተከፋይ ገንዘብ 33 በመቶ ድርሻ መያዙን ገልጸዋል። በተያያዘም የባንኩን ቅርንጫፎች 608 ማድረስ መቻሉም ተነግሯል።
“ምንም እንኳን ያሳለፍነው የበጀት ዓመት አገራዊና እና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች የበዙበት የነበረ ቢሆንም፣ ባንካችን 2.05 ቢሊዮን ያልተጣራ ትርፍ አስመዝገቧል” ሲሉ የቦርድ ሰብሳቢው ማንዘዋል መኮንን ተነናግረዋል።

ሰኔ 30/2013 በተገባደደው በጀት ዓመት ባንኩ በዲጂታል ዘርፉ ላይ ዓበይት ሥራዎች መሥራቱን ሰብሳቢው ገልጸው፣ ከነዚህም ውስጥ ‹ኦን ላይን› መገበያያ መንገዶችን ጨምሮ፣ የ‹ኢኮሜርስ ፔይመንት ጌትዌይ› አገልገሎት፣ ‹ጊዜፔይ› የተሰኘ ሞባይል ‹ዋሌት› ዋናዋናዎቹ ናቸው።

በተያያዘም የባንኩ የሞባይል እና የካርድ ተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን መጠጋቱ ተመክላቷል። በሌላም በኩል ባንኩ ለዐይነ ሥውራን አገልግሎት የሚሰጥ የኤቲኤም ማሽን ሥራ ማስጀመሩ የቅርብ ገዜ ትውስታ ነው።
በሌላም በኩል ባንኩ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ሜክሲኮ አደባባይ ፊትለፊት ባለ 9673 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ 60 ፎቅ ያለው ሕንጻ ለመገንባት ያወጣውን ዓለም አቀፍ ጨረታ ካሸነፈው ተቋራጭ ጋር በዋጋና ሌሎች ቴክኒካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የነበረውን ድርድር ማጠናቀቁ ተገልጿል። በዚህም ባንኩ የሕንጻ ሥራውን ግንባታ ለማስጀመር ከተቋራጩ ጋር ውል ለመፈራረም በዝግጅት ላይ እንደሆነ ማንያዘዋል መኮንን ተናገረዋል።

ባንኩ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በጅማ፣ በባህር ዳር፣ ሐዋሳ፣ ዲላ፣ ዱከም እና ድሬደዋ ከተሞች ላይ በአጠቃላይ 16 ይዞታዎች ያሉት ሲሆን፣ ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ እና ያልተጀመሩ የባንኩን ይዞታወችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑ ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here