የዳያስፖራው መምጣት ለሆቴሎች የሚጠበቀውን ገቢ እያስገኘ አለመሆኑ ተገለጸ

0
870

ኢትዮጵያ በውጭ አገራት የሚኖሩ ዳያስፖራዎች እና የኢትዮጵያ ወዳጆች የገናን በዓል በኢትዮጵያ እንዲያከብሩ ያደረገችውን ጥሪ ተከትሎ፣ የዳያስፖራው መምጣት
ለሆቴሎች ያስገኛል ተብሎ የታሰበው ገቢ እንደተጠበቀው አለመሆኑን የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማኅበር ገለጸ።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባሳለፍነው ኅዳር ወር በውጪ አገራት ለሚኖሩ ለአንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ፣ ኢትዮጵያውያን ከብዙ የዓለም ክፍሎች የገና በዓልን ለማክበር ወደ ትውልድ አገራቸው በመመለስ ላይ ናቸው። ይህንንም ተከትሎ ወደ ኹለት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ በነበረው የቱሪዝም አገልግሎት ላይ፣ በተለይም በእንግዳ መቀበል ሥራ ላይ በተሰማሩ ሆቴሎች፣ አበርታች ምላሸ
እየታየ አለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

ምንም እንኳን፣ ምን ያክል ቁጥር ያላቸው ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን የገናን በዓል ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ በእርግጠኝነት ማወቅ ባይቻልም፣ በአዲስ አበባ
ከተማ ያሉ ሆቴሎች ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ አዎንታዊ የሚባል ቁጥር እያስተናገዱ አለመሆኑን ማኅበሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ኮቪድ-19 በ 2012 መጋቢት ወር ላይ በኢትዮጵያ ከተከሠተ ጀምሮ፣ በክፍተኛ ደረጃ ጉዳት ካደረሰባቸው መስኮች መካከል የሆቴል ዘርፉ ዋነኛው ነው። ይህንንም ተከትሎ የሆቴሎች አልጋ የመያዝ መጠን እስከ ኹለት በመቶ ድረስ ወርዶ እንደነበር ይታወሳል።

ከ170 በላይ አባላት ያሉት የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማኅብር ሥራ አስኪያጅ አምሃ በቀለ ለአዲሰ ማለዳ እንደገለጹት፣ የቫይረሱ መከሰትን ተከትሎ የተላለፉ የጉዞ ዕገዳዎች እና ሌሎች መመሪያዎች ዘርፉን ጫና ውስጥ እንደከተቱት ጠቁመው፣ በመሀል የመሻሻል ምልክት አሳይቶ እስከ አርባ በመቶ ደርሶ የነበረውን መነቃቃት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ ኹለት በመቶ እና ከዛም በታች ዝቅ እንዲል አድርጎታል ብለዋል።

የገና በዓልን ለማክበር ወደ አገራቸው የገቡ የዳያስፖራው አባላት ከሆቴሎች ይልቅ እንግዳ መቀበያ ቤቶችን (ገስት ሀውሶችን) ምርጫ ማድረጋቸው፣ በሆቴሉ ዘርፍ ላይ ይፈጠራል ተብሎ የታሰበው መነቃቃት እንዳይኖር አድርጎታል ብለዋል። “ዳያስፖራው ከሆቴሎች ይልቅ በየዘመድ ቤት እና ዕቃዎች ያሟሉ እንግዳ ማረፊያዎች ምርጫው ሆኗል” ሲሉ አምሀ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሥራ አሰኪያጁ አክለውም፣ የእንግዳ ማረፊያዎችን (ገስት ሀውሶችን) ምርጫችው ያደርጉበት ምክንያት ምናልባትም ለወራት በሆቴል ውሰጥ ከመቆየት ይልቅ፣ ማቀዘቀዣ እና ማብሰያ ያሟሉ እስከ ሦስት ምኝታ ያላችው የእንግዳ ማረፊያ ቤቶች ማግኝት በመቻላቸው ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዳያሰፖራ ኤጅንሲ ዳይሬክተር በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን ተከትሎ፣ በመዲናዋ የሚገኙ ሆቴሎች እና እንግዳ ማረፊያዎች ከነበረባቸው የገበያ መቀዛቀዝ የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰዓት የዳያስፖራውን መምጣት ተከትሎ በቦሌ እና ካዛንችስ አካባቢ የሚገኙ ዕቃ ያሟሉ የእንግዳ ማረፊያዎች እስክ 2500 የአሜሪካ ዶላር ድረስ እየተከራዩ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ለማረጋገጥ ችላለች። እንዲሁም ግለሰቦች መኖሪያ ቤቶቻቸውን ከተሟላ ዕቃ ጋር ወደ የእንግዳ ማረፊያ በማድረግ በወር በአማካይ እስክ 30 ሺሕ ብር እያከራዩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

አዲስ አበባ ውስጥ በኮኮብ ደረጃ ያሉ ሆቴሎች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከ16 ሺሕ የማይበልጥ አልጋ ነው ያላቸው የሚሉት የሆቴል ባለሙያው ኤርሚያስ አለሙ፣ ከ100 በላይ አልጋ ያላቸው ዘጠኝ የሚሆኑ እንደ ኔክሰስ፣ ሳፋየር እና ሆሊዴይ ያሉ በአሁኑ ሰዓት ታሽገው ያለምንም መፍትሔ የቆሙ ሆቴሎች ሲቀንሱ ደግም ቁጥሩ ያንሳል ብለዋል። ይህ ደግሞ እንግዶች ምን አልባትም ጸጥታቸው እና ደኅንነታቸው ባልተጠበቅ እንግዳ ማረፊያዎች ሲያርፉ ላልተፈለገ ውጪ እና እንግልት ሊዳረጉ
ይችላሉ የሚል ሥጋት እንዳላቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here