መንግስት ወደ ኦሮሚያ ክልል የመለሳቸው ተፈናቃዮች “የከፋ በመሆኑ” ወደ ደብረብርሃን እየተመለሱ ነው

0
1228

የኦሮሚያ እና አማራ ክልል አስተዳደሮች ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት ምክክር ማድረጋቸውን ተከትሎ ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ለመመለስ ተስማምተው ተፈናቃዮችን ማጓጓዝ መጀመሩን አዲስ ማለዳ ዘግባ ነበር። ይሁን እንጂ ወደ ኦሮሚያ ክልል የተመለሱ ተፈናቃዮች ወደመጡበት ደብረ ብርሃን መልሱን የሚል ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

አዲስ ማለዳ ያነጋግረቻቸው ደብረ ብርሃን በቻይና መጠለያ ጣቢያ የተፈናቃዮች ተወካይ የሆነ ግለሰብ “መንግስት ኃላፊነቱን ወስዶ የነበርንበትን አካባቢ ሰላሙን አረጋግጦ ይመልሰን፤ ለ4 ዓመታት በተፈናቃይ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ቆይተናል። እዚ በቂ ድጋፍም የለም የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች ስለሌሉ ማህበረሰቡ ወደ ቀዬው ተመልሶ ስራው እንዲሰራ አድርጉልን ብለን ጠይቀን ነበር” ይላሉ።

ተፈናቃዮችን ከመመለሱ ሂደት ከአንድ ወር ገደማ አስቀድሞ ያለውን ሁኔታ ለመቃኘት ወደ ክልሉ ከሄዱት ተወካዮች መካከል አንዱ የሆነው ተፈናቃይ ግለሰብ፤ በወቅቱ ወረዳዎች ላይ ካልሆነ በስተቀር የገጠራማው አካባቢ መንግሥት ሸኔ በማለት የሚጠራው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚለው ታጣቂ ቡድን የተያዘ ስለነበር በአካባቢው ተፈናቃዮችን ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ እንደሌለ ገልጸናል ይላሉ።

ነገር ግን መንግስት አቋሙ “እኛን መመለስ ስለነበር፣ መመለስ ግዴታ ነው አለ። እኛም አይሆንም፤ ገበያ መሄድ ካልተቻለ፣ ሰው የራሱ ማሳ ላይ መንቀሳቀስ ካልቻለ ለመጠለያ እዚም መጠለያ ጣቢያ ነው። ቢያንስ እዚህ [ደብረ ብርሃን] ገበያ በነጻነት መሄድ ይቻላል፣ ስራ ከተገኘም መስራት ይቻላል” በማለት ተፈናቃዮችን መመለስ እንደማይቻል ማሳወቃቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። 

በአንጻሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሳምንታት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ ሲሰጡ ብልጽግና ፓርቲ “ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ወደ ስፍራቸው መመለስ አለባቸው። በኦሮሚያ መኖር መብታቸው ነው። ይህ መብታቸው መከበር አለበት” ብሎ መወሰኑን አስታውቀው ነበር።

“የሁለቱ ክልል አመራሮች የተፈናቀሉበት አካባቢ ድረስ ሄደው፤ የሕዝቡን ዝግጁ መሆን አይተው ቀያቸው መጠበቁን አይተው እንዲመለሱ ሥራ ጀምረዋል” ሲሉ የተደረገውን ዝግጅትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጻቸው አይዘነጋም። 

የኦሮሚያ ክልል እና የአማራ ክልል መንግስታት “ኃላፊነቱን እንወስዳለን” በማለታቸው በደብረ ብርሃን ከቻይና፣ ባቄሎ እና ወይንሸት የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የመጀመሪያ ዙር ተመላሾች የካቲት 10 ቀን 2016 ወደ ኦሮሚያ ክልል ተመልሰዋል። ከደብረ ብርሃን የተመለሱ ተፈናቃዮችም በምዕራብ ሸዋ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች በመጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ።  

የተፈናቃዮች ተወካዩ ይህን ዘገባ እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ ከቻይና ካምፕ ወደ ኦሮሚያ ክልል ከተወሰዱ አባ ወራዎች 13 የሚሆኑ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ወደ ደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ መመለሳቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከተመላሾቹ አብዛኞቹ ሃሳባቸውን ለመግለጽ ስጋት እንዳደረባቸው አዲስ ማለዳ መረዳት ችላለች።

ወደ ደብረ ብርሃን የተመለሱ ተፈንቃዮች ተመላሾቹ በኦሮሚያ ክልል ዞኖች የሚገኙበትን ሁኔታ ሲገልጹ “እንጨት እንኳን መስበር አንችልም። ለህይወታችን አስጊ ነው፤ ከመጠለያችን መውጣት አንችልም። 

በዛ ላይ ከመንግስት ምንም አይነት ድጋፍ እየተደረገልን አይደለም። ከዚህ [ከቻይና መጠለያ ጣቢያ] የባሰ ኑሮ ሆነብን። እዚህ ስንኖር ቢያንስ ከማህበረሰቡ እንኳን ድጋፍ እናገኛለን” በማለት መመለሳቸውን ገልጸዋል።

በስፍራው በየዕለቱ የተኩስ ድምጽ ይሰማል የሚሉት ተፈናቃዮች ታጣቂዎቹ “ከዛሬ ነገ ይመጣሉ በሚል ተሳቀቅን” ሲሉ ስጋታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በደብረ ብርሃን ያለው ተፈናቃይ “በረሃብ ሊያልቅ ነው” የሚሉት ተወካያቸው “መንግስት ድጋፍ ከተደረገላቸው እሺ ብለው አይመለሱም የሚል አቋም ያለው መሰለኝ” ሲሉ ሃሳባቸውን ተናግረዋል። እንደ ማሳያ ከተጠቀሰውም በቻይና መጠለያ ጣቢያ ብቻ ሰባት የጤና ማዕከላት የነበሩ ሲሆን አሁን ግን አንድ ብቻ መቅረቱ ተመላክቷል። 

በደብረ ብርሃን በቻይና ካምፕ 12 ሺህ 143 የሚሆኑ ተፈናቃዮች ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፤ ህክምና ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች በሁለትና በሶስት ቀናት ውስጥ የማግኘት እድል ነው ያላቸው። ተፈናቃዮች ወደ ሌላ የጤና ማዕከላት ለመሄድ እና ለመድኀኒት መግዣ ገንዘብ እንደማይኖራቸው ደግሞ አዲስ ማለዳ ሰምታለች። 

ላለፉት ሁለት ወራት ከመንግስት ምንም አይነት ድጋፍ “ባለመደረጉ” አረጋውያን፣ ህጻናት እና ታማሚዎች ለሞት እየተዳረጉ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ተፈናቃዮች ባለፈው ሳምንት ብቻ ከቻይና መጠለያ ጣብያ አምስት አረጋውያን መሞታቸውን ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል መንግስትን እርዳታ እንዲያደርግላቸው መጠየቃቸውን ገልጸው “ገና አልተጫነም፤  ከፌደራል መንግስት አልተለቀቀም” የሚል ተደጋጋሚ ምክንያት እንደሚሰጣቸውም ተወካዩ ጠቁመዋል።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአምስት ልጆች አባት የሆኑ ተፈናቃይ ግለሰብ ከሶስት ዓመታት በፊት በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው ግጭት ያላቸውን ቤት፣ ንብረት፣ አትክልትና ግማሽ ሄክታር የተለቀመ ቡና ትተው መውጣታቸውንና ሁሉም እንደወደመ በትካዜ ያስታውሳሉ።

አሁን አካባቢው ባልተረጋጋበት ሁኔታ ወደመጡበት በመለሷቸው ወቅትም “እዛ ከደረስን በኋላ የምግብ እርዳታ የለም። በዛ ላይ መጠለያው እጅግ ሞቃት እና አጫጭር ሸራ ነው። የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ የለም። እሱ ላይ ጥይት ይተኮሳል። ስጋቱም እንዳለ ነው። እኔ ቤተሰቤን ይዤ ሾልኬ መጣሁ” ሲሉ በስፍራው የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል።

ከመመለሳቸው በፊት ሃኪም አለ፣ ቀለባቹ ምንም አይቸግራቹም የሚል ቃል ተገብቶላቸው እንደነበር ገልጸው አንድም ሰው ገንዘብ እጁ ላይ ባልነበረበት ሁኔታ አረጋውያን ታመው ህክምና ለማግኘት ተቸግረው እንደነበር አመላክተዋል።

ስራ እንኳን ሰርቶ ገንዘብ ለማግኘት ፈጽሞ የማይታሰብ መሆኑን የገለጹት ተፈናቃዩ ከመጠለያው ለመውጣት የማይቻል ነው ብለዋል። ወደ ደብረ ብርሃን ከተመለሱ በኋላ ኃላፊዎቹን ማነጋገራቸውን ገልጸው “ድጋፍ እየተደረገልን አይደለም ሲሉ አንዴ ሄዳችኋል ብለውናል” ሲሉ በሀዘን ይናገራሉ።

“አሁን የምፈልገው ከዚ በኋላ ለእኛ ምንም ተስፋ የለንም፤ ባይሆን የቀን ስራም እየሰራሁ ህጻናት ልጆቼን ማሳደግ ነው። ቢያንስ ልጆቼ በህይወት ይቆዩልኝ” ይላሉ ተፈናቃዩ።

በተመሳሳይ የቻይና መጠለያ ጣቢያ የተፈናቃዮች ተወካዩን ሃሳብ የሚጋሩት የባቄሎ መጠለያ ጣቢያ ተፈናቃዮች ተወካይ፤ 29 አባ ወራዎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ገልጸው፤ “በስልክ ስናነጋግራቸው ተቸግረው ነው፤ ያሉት በዛ ላይ ስጋትም አለ” እንደሚሉ ገልጸዋል።

ከፍተኛ የደህንነት ስጋት በመኖሩ የመኖሪያ ቀዬቸውን እንኳን ሄደው መመልከት ያልቻሉበት ሁኔታ ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። ለዚህም ከስድስት ቀናት በፊት ምስራቅ ወለጋ ዞን ሲቡሱሬ ወረዳ ጨሪ ቀበሌ ታጣቂዎች ሌሊት በመግባት ሰባት ሰዎችን በማገት እንዲሁም 68 የቀንድ ከብቶችን ይዘው መሄዳቸውን በስፍራው ከሚገኙ ሰዎች መስማታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከታጋቾቹ መካከል አንዱ ከደብረ ብርሃን የተመለሰ ግለሰብ መሆኑን ያነሱት ተወካዩ “ከደብረ ብርሃን የተመለሰ ነው” በሚል 800 ሺህ ብር እንደተጠየቀበት ገልጸው በድርድር 500 ሺህ እንዲከፍል መጠየቁን ተናግረዋል። 

ተፈናቃዮችን ወደ ስፍራቸው መመለስ የሚያስችል የተረጋገጠ ሰላም እንደሌለ ሲያሳስቡ ቢቆዩም “አንሄድም አንልም፤ ነገር ግን ወደ ቀዬችን ተመልሰን እንደበፊቱ ነው መኖር የምንፈልገው። ለስድስት ወራት መንግስት ካገዘን ከዛ በኋላ ማምረት እንችላለን። አሁን ግን ሰላም በሌለበት መሄድ አንችልም” ይላሉ።

መንግስት ቅድሚያ የክልሉን ሰላም ሊያስጠብቅ ይገባል የሚሉት ተወካዮቹ ጎቡ ሰዮ ወረዳ ላይ ባለፈው ሳምንት ውጊያ እንደነበር ጠቁመው የሄዱት መልሱን የሚል ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን አንስተዋል።

ከመንግስት ምንም አይነት ድጋፍ እየተደረገልን አይደለም የሚሉት ደብረ ብርሃን የሚገኙ ተፈናቃዮች “ከበጎ ፈቃደኞች እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አልተመለሳቹም እንዴ? የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ እየቀረበልን ነው። ይኼም እንደ አዲስ ሌላ ስራ ነው እየጠየቀን ያለው” ሲሉ ገልጸዋል።

ከግለሰቦች ይገኝ የነበረው ድጋፍ አሁን በደብረ ብርሃን ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት መቀዛቀዙን የገለጹት ተወካዩ ከ4 ሺህ በላይ ተፈናቃይ የሚገኝበት ባቄሎ የመጠለያ ጣቢያ የሚገኙት ተፈናቃዮች ችግር ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

“አሁን ነገሮች እየከፉ ነው ያሉት፤ ከዚህ በኋላ ወደ ቀዬችን እንመለሳለን የሚል ተስፋ የለንም። እዚህ ከገባን ሶስት ዓመት ሊሆነን ነው። መንግስት ያንን ቦታ ተቆጣጥሮ ሰላም አስፍኖ እኛን መመለስ አልቻለም” የሚሉ ተፈናቃዮች ጥቂት አይደሉም።

ስለዚህ መንግስት የሚያሰፍርበትን ቦታ ቢያመቻችልን እና በቋሚነት እኛን በማደራጀት እራሳችንን ችለን መኖር የምንችልበት ሁኔታ ቢፈጥርልን የሚለው ሃሳብ በርካታ ተፈናቃዮች የሚስማሙበት መሆኑን አንስተዋል።

አዲስ ማለዳ ከቻይና እና ባቄሎ ጣቢያዎች በተጨማሪ ወይንእሸት መጠለያ ጣቢያ ተወካዮችን ለማናገር ያደረገችው ሙከራ ባይሳካም ከሁለቱ እምብዛም የተለየ ሁኔታ አለመኖሩን ተገንዝባለች። 

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ ደረጀ ይንገሱ፤ ድጋፍ ለሁለት ወራት አለመደረጉን አረጋግጠው ተፈናቃዮቹ ይኼን ጥያቄ ማንሳታቸው አግባብ ነው ብለዋል። 

“ነገር ግን እርዳታ ከፌደራል መንግስት አልተላከም። እኛ ማድረግ የምንችለው ሲላክ ማከፋፈል አልያም አልተላከም ብለን መናገር ብቻ ነው” ሲሉ ደረጀ ይንገሱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ድጋፉ የተቋረጠው ተፈናቃዮቹን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከተጀመረው ሂደት ጋር በተያያዘ ነው ወይ በሚል ከአዲስ ማለዳ ለቀረበላቸው ጥያቄም “እኔ ስለ እሱ ምንም የማውቀው ነገር የለም” ሲሉ መልሰዋል። 

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ስነ ሕዝብ ባለሙያ እና የጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች አስተባባሪ አንተነህ ገብረ እግዚአብሄር በበኩላቸው በደብረ ብርሃን የነበሩ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬቸው መመለሳቸው እንዲሁም በክልሉ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን እንደሚያውቁ የገለጹ ሲሆን ነገር ግን ይኽ ጉዳይ የክልል እና የፌደራል መንግስትን የሚመለከት መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች እርዳታ ሳያገኙ ወራት እንዳለፏቸው ገልጸው “ሶስት ዓመታት ሊፈታ ያልቻለ ችግር ነው” ያሉትን ይኼን ጥያቄ በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካላት ቢያቀርቡም ዘላቂ ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን ይገልጻሉ።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በመጠለያ ጣቢያው የነበሩና ከምዕራብ ወለጋ ዞን በታጣቂው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የመንግስት ኃይል መካከል በነበረ ግጭት ከመኖሪያ ቀዬቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን “የብልፅግና አገዛዝ በፖሊስ እያስገደደ ወደ ወለጋ አካባቢ እየጫኗቸው መሆኑን ተፋቃዮቹ ነግረውኛል” ሲል መግለጹ ይታወሳል።

ባለፉት ዓመታት በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በፈጸሙት ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ጥቃቱን በመሸሽ ከቀያቸው ተፍናቅለው ይገኛሉ። 

ይህንን በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ሲፈጸም የቆየውን ጥቃት መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንደፈጸመው በተደጋጋሚ ቢነገርም፣ ቡድኑ ግን ድርጊቱን አለመፈጸሙን በመግለጽ መንግሥትን ተጠያቂ ሲያደርግ ቆይቷል።

መንግስት በአገሪቱ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል እንዲሁም “ጽንፈኞችና አሸባሪዎች” የሚላቸው አካላት ላይ በተደጋጋሚ እርምጃ መውሰዱን ሲገልጽ ቢደመጥም በተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች ዜጎች ለሞትና መፈናቀል እየተዳረጉ በመሆኑ ትኩረት አልተሰጠውም ሲሉ ተፈናቃዮች ይተቻሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here