“የማዕድን ሀብታችን ለብልጽግናችን” በሚል መሪ ቃል የማዕድን ኤግዚቢሽን እና ፎረም በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው

0
802

ሰኞ ጥር 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) “የማዕድን ሀብታችን ለብልጽግናችን” በሚል መሪ ቃል የማዕድን ኤግዚቢሽን እና ፎረም በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመድረኩም የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና ሌሎች በየደረጃው ያሉ የክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተውበታል።

ማዕድን ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል የተፈጥሮ ሀብት ቢሆንም በአገራችን ለረጅም ዘመናት ሳይንሳዊ ምርምሮችን በማድረግ በሚፈለገው መልኩ ሀብቱን ሥራ ላይ ማዋል እንዳልተቻለ ተገልጿል።

የኦሮሚያ የማዕድን ሀብት ባለሥልጣን በዚህ ዓመት ለሥራው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ እንደሆነ ተጠቁሟል።

በፎረሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ “ማዕድን ምድራችንን የሞላ የተፈጠሮ ሀብት ነው፤ ቢሆንም ይህን የተፈጠሮ ስጦታ በአግባቡ ተጠቅመን የሥራ አጥነት ችግሮችን መቅረፍ ሲገባን ትኩረት ሳንሰጠው በመቅረታችን ከሀብቱ ልናገኘው የሚገባንን ያህል ጥቅም አላገኘንም” ብለዋል።

አሁን ግን በየደረጃው ያለው አመራር ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ይህን የማዕድን ጎተራ ከፍተን የወጪ ንግድን በመጨመር የሀገራችንን ምጣኔ ሃብት ማሳደግ ይጠበቅብናል ሲሉም መናገራቸውን ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማም በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ “ኦሮሚያ የማዕድን ሀብት የተከማቸበት የማዕድን ጎተራ ነው ። ጎተራውን በሁሉም መልኩ ተጠቅመን የህዝባችንን ህይወት ሊለወጥ፤ አገራችን ከሀብቱ ልትጠቀም ይገባል።” ብለዋል።

አክለውም ኤግዚብሽኑ በማዕድን ዘርፍ ያለንን ተስፋ ሰፊና ብሩህ መሆኑን የሚያሳይ ነው ያሉ ሲሆን፤ “እኛም በጥረታችን ተስፋውን በተግባር እንዲገለፅ እናደርጋለን።” ሲሉ ገልጸዋል።
___________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here