የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት የ2014 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ ክንውን ስኬታማ መሆኑን ገለፀ

0
668

ሰኞ ጥር 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት የ2014 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ ክንውን ስኬታማ መሆኑን አስታውቋል።

ተቋሙ ከሐምሌ 1 ቀን 2013 እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2014 ድረስ ታቅደው የነበሩ የሰነድ ማረጋገጥና መመዝገብ ተግባራት ክንውን አመርቂ ውጤት የተመዘገበ መሆኑን የተቋሙ ካውንስል አባላት ባደረጉት የሪፖርት ግምገማ መርሀ ግብር ተገልጿል፡፡

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው፤ በተለያዩ አገልግሎት ዘርፎች 485 ሺህ 834 ጉዳዮችን ለማስተናገድ በዕቅድ ተይዞ 498 ሺህ 370 ጉዳዮችን በማስተናገድ የዕቅዱን 102 ነጥብ 6 በመቶ ለማሳካት ተችሏል፡፡

እነዚህን ጉዳዮች ይዘው በመምጣት አገልግሎቱን ያገኙ ተገልጋዮች ብዛት 792 ሺህ 967 ያህል ሲሆን፤ ተቋሙ በቀን በአማካይ 6 ሺህ 7 ተገልጋዮችን እንደሚያስተናግድም ገልጿል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ብር 326 ሚሊዮን ገቢ ለመሰብሰብ በዕቅድ ተይዞ ብር 316 ሚሊዮን በመሰብሰቡ የዕቅዱ 96 ነጥብ 9 በመቶ ያሳካ ሲሆን፤ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ63 ሚሊዮን ብር ወይም 24 ነጥብ 9 በመቶ ያህል ብልጫ እንዳለውም ተገልጿል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ውስጥ ተዓማኒነት ያለው ተገልጋይን ያረካ ጥራት ያለው ሰነድ በማመንጨት በሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች፤ በውልና ውክልና ዘርፍ 265 ሺህ 752 የሚሆኑ አገልግሎቶች በኦን-ላይን ሲስተም ታግዘው ተሰጥተዋል፡፡ ይህንን አሰራር ወደ ሌሎችም አገልግሎቶች ለማስፋት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል አንዳንድ ተገልጋዮች ይዘዋቸው የሚቀርቡ ሀሰተኛ ሰነዶች መበራከት የተቋሙን የተረጋጋ ህጋዊ አሰራር ከሚያውኩ ሁኔታዎች አንዱና ዋነኛው መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ ለተቋሙ የሚቀርቡ ሰነዶችን ትክክለኛነትና ህጋዊነት የማረጋገጥ ተግባር ላይ በሀሰተኛ (ህጋዊ ባልሆነ) ሰነድ ለመጠቀም የተገኙ ተገልጋዮች ላይ አስፈላጊው የህግ እርምጃ እንዲወሰድ መደረጉንም ገልጿል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሐሰተኛ ሰነድ ይዘው የተገኙ 231 ሐሰተኛ ማስረጃዎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በማድረግ ሊደርስ የነበረዉን ጉዳት ለማስቀረት መቻሉንም ነው ተቋሙ ያስታወቀው፡፡

በተቋሙ ፍትሀዊነትንና ሁሉን አቀፍነትን ከማረጋገጥ አንጻር ለ4 ሺህ 256 አቅመ ደካማ ግለሰቦች፣ በህመም ምክንያት ከቤታቸዉ መንቀሳቀስ ለማይችሉ፣ ለአካል ጉዳተኞና ለሚያጠቡ እናቶችም ጭምር የተቋሙ ባለሙያዎች ያሉበት ስፍራ ድረስ በመሄድ ቅድሚያ በመስጠት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ በመድረጉ የማህበረሰባዊ ኃላፊነቶችን እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጿል።

በተጨማሪም ተቋሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንኙነትና ቅንጅት በመፍጠር ከፌደራል የፋይናንስ ደህንነት ማዕከል፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከፌደራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ጋር የመረጃ ልውውጦች ተደርገዋል፡፡

ወንጀልንም ለመከላከል ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና የክልል ፖሊስ እንዲሁም ከተለያዩ የፍትህ አካላት ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠሩንም ገልጿል፡፡
___________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here