ከኦሮሚያ ክልል ከወለጋ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው የሚገኙ ተፈናቃዮች በመንግሥት አካል ወከባ እየደረሠባቸው መሆኑን እና በመንግሥት በኩል ምንም ዓይነት ድጋፍ ተደርጎላቸው እንደማያውቅ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ተፈናቃዮች ወደ ከተማዋ ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ በደረሰባቸው ወከባ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቤተ ክርስትያናት እና ሌሎች ቦታዎች ተጠልለው እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።
ተፈናቃዮቹ በከተማዋ መኖር ከጀመሩ ከኹለት ወር በላይ ቢሆናቸውም፣ ከየትኛውም የመንግሥት አካል ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው ነው የታወቀው። ዕርዳታ የሚያድርጉላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እና አንዳንድ በጎ ፈቃደኛ አካላት መሆናቸው ታውቋል።
ተፈናቃዮቹ ዕርዳታ እንዲደረግላቸው እና መፍትሔ እንዲሠጣቸው ብዙ የመንግሥት ተቋማትን ቢጠይቁም፣ ማንም ጆሮ እንዳልሰጣቸውና ይባስ ብሎም ችግራቸውን ለመገናኛ ብዙኃን እንዳይገልጹ ብሎም ድምጻቸውን እንዳያሠሙ ወከባና ማስፈራሪያ እየደረሠባቸው እንደሆነ ከተፈናቃዮች ለማወቅ ተችሏል።
በአዲስ አበባ በየካ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን ተጠልለው ከሚገኙ ተፈናቃዮች ውስጥ ሥሜ ባይጠቀስ ያሉ አንድ አባወራ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ጥቅምት 8/2014 ከምሥራቅ ወለጋ ለቀምት ዞን ተፈናቅለው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ የከተማውን መውጫ መግቢያ ስለማያውቁት ብዙዎቹ ተፈናቃዮች ወጣ ብለው በሚገኙ የተዘጉ ቤቶች ውስጥ እንደሚያድሩ ገልጸዋል። ከከተማ ነዋሪዎች ከሚቀርብላቸው አነስተኛ ድጋፍ ውጭም ከመንግሥት አካል የሚቀርብላቸው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
አክለውም፣ ከመንግሥት አካል ምንም ፍትሕ አላገኘንም፤ ያልገባንበት የመንግሥት ቢሮ የለም። ለአብነትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ብንሄድም፣ ከንቲባዋ አፋር ክልል ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ሊያደርሱ ሔደዋል በሚል አስተዳደሩ ምንም ሊያደርግልን አልቻለም ነው ያሉት።
ከንቲባ ጽሕፈት ቤቱም፣ “ችግሩ ከአቅሜ በላይ ነው፣ አማራ ልማት ማኅበር ሔዳችሁ ጠይቁ” ብሎን ተመልሰናል የሚሉት ተፈናቃዮቹ፣ መንግሥት የአገሪቱ ዜጎች መሆናችንን ዐይቶ፣ ሲሆን በአፋጣኝ መጠለያ፣ ምግብና አልባሳት ሊያቀርብልን በተገባው ነበር። ይባስ ብሎ ግን “ለምን ትሰባሰባላችሁ? ምንድን ናችሁ?” በማለት የከተማው ፖሊሶች ይረብሹናል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም እኛ የፖለቲካ አጀንዳ አራማጆች እንዳልሆን ለማስረዳት ሕፃናቶቻችንን ተመልከቱ እንላቸዋለን ብለዋል። በየክፍለ ከተሞች ተበታትነው የሚገኙ ሌሎች ተፈናቃዮችም እንዲሁ “ዕውነት ሕግ ካለ ፍርድ ይሰጠን፤ ሀብት ንብረታችን ወድሞ ሕጋዊ ይዞታችንም በሌላ ኃይል ቁጥጥር ውስጥ ገብቷል። እኛ ከተጨፈጨፉትን ወገኖቻችን ተርፈን እዚህ ብንደርስም ከዚያ ያላነሰ ስቃይ እየደረሰብን ነው” ሲሉ ይሰማል።
“እኛ ከመንግስት የምንለምነው የተለዬ ነገር አይደለም፤ የምንበላው ምግብ እና የምንለብሰው ልብስ ነው። የቤት ኪራይ የሚሆን ገንዘብም ስለሌለን አፈር ላይ ኹሉ እንተኛለን። ስለዚህም መንግሠት እንዲደርስልን እንማፀናለን” በማለት ይናገራሉ።
በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ፖሊስ በተፈናቃዮች ላይ ምንም ዓይነት የማዋከብ ሥራ አልሠራም ያሉ ሲሆን፣ ይልቅስ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ከየት እንደመጡና ማን እንደሆኑ የማረጋገጥ ሥራ አከናውኗል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም፣ ተፈናቃዮች ከወለጋ ሳይሆን ከአርሲ ዞን አቦምሳ ወረዳ መርቲ ጃጁ ቀበሌ የመጡ እና የመርቲ እርሻ ልማት ሲረዳቸው የነበሩ ናቸው ብለዋል። ድጋፉ ሲቆምባቸው ለኦሮሚያ ክልል አስተዳደር አቤቱታ ለማቅረብ የመጡ መሆኑንም አክለዋል።
በመስቀል አደባባይ አጠገብ በሚገኘው ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤቴክርስቲያን 96 ሰዎች ተሰባስበው እንደነበርና ከዚህም ውስጥ 27ቱ ሕጻናት መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ምሽት ብዙ ሆነው በመምጣታቸው ጥበቃው ለፖሊስ አቤቱታ አቅርቦ ፖሊስ ወደ ቦታው ሊያጣራ ማምራቱንም አንስተዋል። አሁን ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆነን ወደ መጡበት እንዲመለሱ እያደረግን ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ተመሳሳይ ጽሁፎች
ከምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ተፈናቅለው በቡሬ ከተማ የሚገኙ 4500 አባወራዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)
በጦርነት ተፈናቅለው የነበሩ ተመላሾች ድጋፍ ስላላገኘን ችግር ላይ ነን አሉ – Addis Maleda
ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014



