አጠቃላይ በጀታቸው 84 ቢሊዮን ብር የሚደርስ 60 ፕሮጀክቶች መቆማቸው ተገለጸ

0
770

ለአንድ ፕሮጀክት 1 ቢሊዮን ብር የወሰን ማስከበር ካሳ እየተከፈለ ነው

በመንግሥት በጀት የሚለሙ 84 ቢሊዮን ብር የሚገመት በጀት የተያዘላቸው 60 ፕሮጀክቶች በተለያዩ ምክንያቶች መቆማቸውን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የተቋረጡት ፕሮጀክቶች ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚተገበሩ ሲሆኑ፣ ከ2011 እስከተያዘው በጀት ዓመት የተጀመሩ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡ የግንባታ ሥራቸው የተቋረጡት በመንግሥት በጀት የሚለሙ ፕሮጀክቶች የቆሙበት ምክንያት አንዳንዶቹ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በጸጥታ ችግር ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በኮንትራክተሮች ችግር መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጠቁሟል። ፕሮጀክቶቹ መቋረጣቸው የተገለጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥር 16/2014 የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የስድስት ወር እቅድ በገመገመበት ወቅት ነው።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተቋረጡ ፕሮጀክቶች ላይ ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ሲሆን፣ የተቋረጡት የግንባታ ፕሮጀክቶች በተለያየ ደረጃ ላይ እያሉ መቆማቸውን አስረድቷል። 84 ቢሊዮን ብር የኮንትራት በጀት የተያዘላቸው ፕሮጀክቶች የዓመቱን 24 በመቶ የፕሮጀክት ልማት እቅድ ይሸፍናሉ ተብሏል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል የእቅድ ክለሳ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

የተቋረጡ ፕሮጀክቶች ያሉበት ደረጃ የተለያየ ነው ያለው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ አንዳንዶቹ ገና በጅምር ላይ እያሉ የተቋረጡ፣ የተወሰኑት ግማሽ ደረጃ ላይ የደረሱ እና በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ናቸው ብሏል። ገና በጅምር ላይ ያሉና የተቋረጡ ፕሮጀክቶችን ከኮንትራክተሮች ጋር በመነጋገር የጊዜ ማራዘም፣ እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶችን በጊዜያዊነት የማገድ ሥራ ማከናወኑን የገለጸ ሲሆን፣ ተስፋ የላቸውም ተብለው የታሰቡ ፕሮጀክቶችን ሙሉ በሙሉ የኮንትራት ውላቸውን የማቋረጥ ሥራ መስራቱን አስታውቋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተቋረጡ ፕሮጀክቶች ላይ የወሰናቸው የተለያዩ ውሳኔዎች እንደ አገር የሚደርሰውን ኪሳራ ለመቀነስ ታሳቢ የተደረገ ነው ተብሏል። በአሁኑ ስዓት ከተቋረጡት ፕሪጀክቶች 10 የሚደርሱን ወደ ሥራ ለማስገባት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውም ተመላክቷል። ይሁን እንጂ፣ በጦርነቱ ምክንያት ሙሉ በሙሉ የወደሙ እና የተዘረፉ ፕሮጀክቶችን አሁን ባለው ሁኔታ ሥራ ማስጀመር አዳጋች መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አብራርቷል።

የፕሮጀክቶቹ መቋረጥ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የ10 ዓመት እቅድ ላይ ተግዳሮች ሊፈጥር እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሁን በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በጀት የጸደቀላቸውና ግማሽ ትሪሊዮን ብር የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች መያዙን ጠቁሟል። በዚህም የ10 ዓመቱ እቅድ ተጨማሪ ውይይት እና ክለሳ እንደሚፈልግ ተመላክቷል።

ከፕሮጀክቶች መቋረጥ ጋር በተያያዘ በተለይ በመንገድ ግንባታ ላይ ችግር የሚያጋጥመው ከበቂ ዝግጅት እጥረት የመነጨ ነው ተብሏል። እንዲሁም፣ በፕሮጀክቶች ላይ ሌላ ፈተና የሆነው ጉዳይ የተጋነነ የካሳ ክፍያ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በአንድ ፕሮጀክት እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ለወሰን ማስከበር ካሳ እየተከፈለ ነው ተብሏል። ለተጋነነ የወሰን ማስከበር ካሳ ምክንያቶቹ ፕሮጀክቶች በሚለሙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የአስተዳደር አካላት ናቸው ተብሏል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የወሰን ማስከበር ካሳ በየደረጃው ካሉ አካላት ካር ተናቦ ተገቢውን ካሳ መተመን ካልተቻለ ወደፊትም በፕሮጀክት ልማቶች ላይ እንቅፋት መሆኑ እንደማይቀር ተጠቁሟል።

ለመንገዶችና ለመንግስት ተቋማት ህንፃ ግንባታ መጓተት ዋነኛ ምክንያቶች፣ የተፈጠረው የፀጥታ ችግርና ከዚህ ጋር በተገናኘ ንብረቶች መውደማቸውና መዘረፋቸው፣ የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መናር መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን በመጠቀም ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑ ተገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here