በዓመት እስከ 200 ሚሊዮን ብር ገቢ የሚሠበስበው የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ግብር እንደማይከፍል ተጠቆመ

0
837

በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት በዓመት እስከ 200 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሚያገኝ፣ ሆኖም ግን ከሠላሳ ዓመታት በላይ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ዕውቅናና ፈቃድ እንደሌለውና ግብር ከፍሎም እንደማያውቅ ተገለጸ።

አዲስ ማለዳ ከትምህርት ቤቱ ምንጮቿ ያረጋገጠችው፣ በ2010 ከተደረገው ለውጥ በፊት ትምህርት ቤቱ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የደኅንነት ሰዎች ልጆቻቸውን ያስተምሩበት የነበረ በመሆኑ ጉዳዩን ለማንም ለማቅረብ ያስቸግር እንደነበር ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ግን ምንጮቹ ለሚመለከታቸው ተቋማት በሙሉ ጉዳዩን ቢያሳውቁም ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸውን ነው።

እንደ ምንጮቹ ገለጻ ትምህርት ቤቱ አራት የተለያዩ ስሞች ያሉት እና አራት የተለያዩ ማኅተሞች የሚጠቀም ሲሆን፣ አባት እና ልጅ የሆኑ ኹለት ግሪካውያን እንደሚዘውሩት ከመታወቁ ውጭ፣ የማን እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም ብለዋል። ትምህርት ቤቱ በግሪክ ማኅበረሰብ ዕድር ውስጥ ሆኖ ወደ ሠላሳ ለሚጠጉ ዓመታት እያጭበረበረ እንደሚገኝ እና የሠራተኞችን ደሞዝና ጡረታ የሚከፍለው በትምህርት ቤቱ ስም ሳይሆን በዕድሩ ሥም መሆኑን የጽሑፍ ማስረጃ በማቅረብ አሳይተዋል።

በዚህ የተነሳም ክስ ቀርቦበት የነበረ ሲሆን፣ ዕውቅና የለኝም ብሎ የክስ መቃወሚያ ለፍርድ ቤት በማቅረቡ፣ ፍርድ ቤት ማረጋገጫ እንዲያቀርብ በሠጠው ትዕዛዝ መሠረት ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዕድሩ እንጂ ግሪክ ኮሚኒቲ ወይም በሌሎች ሦስት ሥሞቹ የተመዘገበ ትምህርት ቤት በከተማዋ እንደማይገኝ ማረጋገጫ አሠርቶ አቅርቧል ነው ያሉት።

የአዲስ ማለዳ ምንጮች ባቀረቡት ሠነድ ላይ ቂርቆስ ክፈለ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት፣ ‹‹በሔለኒክ ግሪክ ማኅበረሰብ መረዳጃ ዕድር ሥር የተቋቋመ ማኅበር በክፍለ ከተማችን በንግድ መዝገብ የተመዘገበና ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም ስለመሆን አለመሆኑ አጣርተን የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር የኮቂ/33750 በቀን14/11/08 በተጻፈልን መሠረት ከላይ ከተጠቀሰው ድርጅት የክፍለ ከተማችን የአይሲቲ ባለሙያ የመረጃ ቋት ውስጥ ያልተመዘገበ መሆኑን አረጋግጠናል›› የሚል ሕጋዊ መረጃ አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። ይህም ትምህርት ቤቱ ለገቢዎች ግብር እንደማይከፍል ማሳያም ጭምር ነው ተብሏል።

ትምህርት ቤቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከግሪክ ኢምባሲ ጋር ለማያያዝ ጥረቶች እንደሚደረጉ ጠቁመው፣ ሆኖም ግን እኛ ደብዳቤ ጽፈን ምላሽ አላገኘንም፤ ከኢምባሲው ጋርም ግንኙነት የለውም ሲሉ የአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አያይዘውም፣ ለግሪክ ማኅበረሰብ የሚያገለግል የግሪክ ትምህርት ክፍል ብቻ እንዲቋቋም ከሠላሳ ዓመት በፊት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሠጣቸው በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኝ የፈቃድ ወረቀት አለ፤ ኾኖም ትምህርት ሚኒስቴር ለእኛ ለማሳየት ፈቃደኛ አይደለም ብለዋል።

እንዲሁም ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የተማሪ ወላጅ፣ ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ያለው ሙስና ለማመን ያቅታል ብለዋል። ትምህርት ቤቱ ከሕዝብ 200 ሚሊዮን ብር እየሰበሰበ ግብር እንደማይከፍል ትምህርት ሚኒስቴር እያወቀ ለምንድን ነው? ብለን ስንጠይቃቸው “እናሳውቃለን” እያሉ “ያላግጣሉ” በማለት ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር በመጭው ሳምንት የግሪክ ኢምባሲን ለማናገር ቀጠሮ መያዙን፣ ሆኖም ግን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር እናት በግሪክ ኢምባሲ ውስጥ ቪዛ የሚመቱ በመሆናቸውም፣ ትምህርት ቤቱን በኢምባሲው ሥር እንደሚገኝ አድርጎ ለማስመዝገብ ቀድመው አሻጥር ሊሠሩ ይችላሉ የሚል ጥቆማ አዲስ ማለዳ ደርሷታል። ግሪክ ኢምባሲ ከዚህ በፊት ስለ ትምህርት ቤቱ ተጠይቆ እንደማያውቀው በደብዳቤ ማሳወቁም እንዲሁ ተጠቁሟል።

ኹሉን ነገር በገንዘብ ነው የሚያስፈጽመው የተባለለት ይህ ትምህርት ቤት፣ በዓመት ከሚሰበስበው ከፍተኛ ገቢ አንጻርም ለተማሪዎች የሚመጥን የመማሪያ መሠረተ ልማት አለመኖሩ ተመላክቷል። ይህም ለአገሪቱ የሚገባውን ግብር ካለመክፈሉም በላይ የሚያገኘውን ገቢ ወደ ውጭ በመላክ በአገሪቱ ተማሪዎች ላይ እንደሚቀልድ ነው የተነገረለት።

የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቱ የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ ወሰን ውበት፣ ትምህርት ቤቱ ዕውቅና አለው የለውም የሚለውን ጥያቄ መመለስ አልችልም ብለዋል።

የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት በተለይ የእንግሊዘኛ ክፍሉ (English Section)፣ ከቅድመ መዋለ ሕፃናት እስከ ቅድመ ኮሌጅ የሚማሩ ከ1200 የማያንሱ ተማሪዎች እንዳሉት እና አንድ ወላጅ በዓመት በአማካይ እስከ 150 ሺሕ ብር ለአንድ ልጅ እንደሚከፍል ተመላክቷል።

አዲስ ማለዳ ትምህርት ሚኒስቴርን ስለጉዳዩ ጠይቃ አጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴታ ፋንታሁን ማንደፍሮ (ዶ/ር) ትምህርት ቤቱ የማኅበረሰቡ ይሁን የእድሩ አልተለየም ስለዚህም ለማክሰኞ ኢምባሲውን ለማናገር ጠርተነዋል ብለዋል።

በአንፃሩ የትምህርት ኢንስፔክሽን ጀኔራል ዳይሬክተር ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) ትምህርት ቤቱ የማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ተብሎ ፈቃድ አለው ያሉ ሲሆን፣ በየኹለት ዓመቱም ፈቃዱን ያሳድሳል ብለዋል። ይሁን እንጅ አዲስ ማለዳ ለትምህርት ቤቱ የተሰጠውን ፈቃድ ከትምህርት ሚኒስቴር ለማግኘት ብትጠይቅም የቀረበላት ሰነድ ፈቃድ የተሰጠበት ሳይሆን በየኹለት ዓመቱ የሚታደሰውን ነው።

ተመሳሳይ ጽሁፍ 

ግሪክ ስኩል ያሉ መምህራን ደሞዝ እንደተቀነሰባቸው ተናገሩ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)


ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here