የአንድ አገር ሠንደቅ ዓላማ የሕዝቦቿ ሉዓላዊነትና የክብራቸው መለያ ምልክት መሆኑ ይነሳል። በዓለም ላይ ያሉ ኹሉም ሉዓላዊ አገራት ይወክለናል የሚሉት ሠንደቅ ዓላማ አላቸው።
የታሪክ መዛግብት እንደሚያስረዱት ከሆነ ኢትዮጵያ ረዥም ዕድሜ እና ደማቅ ታሪክ ያላት ጥንታዊ አገር ናት። ሠንደቅ ዓላማንም የሉዓላዊነትና የግዛት መለያ አድርጋ ጥቅም ላይ ማዋል ከጀመረች ዘመናትን ያስቆጠረች አገር መሆኗ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ፣ በተለይ ከ1890ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ፣ ወጥ በመሆን የአራት መዓዘን ቅርጽ እንዲይዝ ከተደረገ በኋላ፣ ከላይ አረንጓዴ ከመሀል ቢጫ ከታች ደግሞ ቀይ ቀለም እንዲኖረው ተደርጎ እስካሁን ድረስ ዘልቋል። እነዚህ ሦስቱ ቀለማት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ አይቀየሩ እንጂ፣ የተለያዩ ገዥዎች ሥልጣን በያዙ ቁጥር የየራሳቸውን አገዛዝ የሚያንጸባርቅ ዓርማ ሲጠቀሙ ይስተዋላል።
ደርግ ሥልጣን ሲረከብ በዘውዳዊው የአገዛዝ ዘመን የነበረውን የአንበሳ ምስል ዓርማ ከቤተ-መንግሥት አስወግዶ የራሱን ምስል አሳርፎበታል። ይህ ድርጊት ከደርግ መውደቅ በኋላም የቀጠለ ሲሆን፣ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝም ደርግ ይጠቀምበት የነበረውን ዓርማ መቀየሩ አልቀረም።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ላይ የሚያርፈው ዓርማ ከበፊቱ ጊዜ ጀምሮም ቢሆን የገዥዎችን ስሜትና ሐሳብ የሚያንፀባርቅ ሆኖ የተቀረጸ እንጂ፣ ሕዝቡ ተስማምቶበትና ይስማማኛል ብሎ የመረጠው እንዳልሆነ አስተያየት የሚሰጡ አካላት አይጠፉም።
ኾኖም በቀደሙት ጊዜያት በሠንደቅ ዓላማ ቀለማት እና በተለይም በዓርማ የተነሳ መከፋፈል እንደነበረ የሚያስረዱ ቅሬታዎች ይነሱ እንደነበር አይስተዋልም። ከዚያ ይልቅ፣ ቀደምት ኢትዮጵያውያን በባንዲራቸው ይስማሙ እንደነበርና ፍፁም የሚባል ዓይነት ክብርና ፍቅር እንደነበራቸው ነው የሚነገረው።
አድዋ ላይ ኢትዮጵያ ጣሊያንን ማሸነፏን ተከትሎ፣ ብዙ አፍሪካ አገራት ነፃነታቸውን ሲያገኙ ሠንደቅ ዓላማቸውን ከኢትዮጵያ ሠንደቅ ቀለማት ጋር ተቀራራቢ አድርገው መቅረጻቸው በታሪክ ይነገራል።
ይሁን እንጂ ከአገር አልፎ ለአፍሪካውያንም ትልቅ የኩራት ስሜት የሚፈጥረው የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ፣ አሁን ላይ የሚገባውን ክብር ሲቸረው እና ጥበቃ ሲደረግለት ይታያል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር እንደሚያስቸግር የብዙዎች ሐሳብ ነው።
አሁን ላይ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ይዞ መገኘትም ሆነ ባንዲራውን የሚወክል ነገር መጠቀም ሲከለከል ይታያል።
በዚህ ወቀት የሠንደቅ ዓላማ ጉዳይ የልዩነት ምክንያት ሆኖ ይስተዋላል። ዓርማ የሌለበት ልሙጡን ሠንደቅ ዓላማ የሚጠቀሙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሲኖሩ፣ ከባለ ኮከቡ ሠንደቅ ዓላማ ውጭ መያዝ አይቻልም የሚሉ አካላትም አሉ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስትያንም ኃይማኖታዊ መገለጫ ነው ያለችውን ዓርማ አሳርፋ ሠንደቁን ትጠቀማለች።
በአንድ አገር ውስጥ የፈለጉትን ሠንደቅ ዓላማ ይዞ መውጣት የግለሰቦች መብት ቢሆንም፣ ከዚህ ባለፈ ግን የአንድ አገር ሕዝቦች በአገራቸው ሠንደቅ ዓላማ መስማማት ካቃታቸውና አደባባይ ላይ ይህን ሠበብ አድርገው ብጥብጥ የሚፈጥሩ ከሆነ፣ በአገራዊ ፍቅራቸውና ስሜታቸው፣ እንዲሁም በጋራ ዓላማቸው ላይ ዕንቅፋት እንደሚፈጥር ይገለጻል።
ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ክልሎች የየራሳቸው ባንዲራ እንዲኖራቸው መፍቀዱም፣ ረዥም ዕድሜና ታሪክ ያለው የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ በብዙዎች ዘንድ የልዩነት መነሻ እንዲሆን አድርጎታል የሚሉ አሉ።
በተለይ ባለ አምስት ኮከብ ዓርማ የያዘው ሠንደቅ ዓላማ እስከ ኢሕአዴግ መፍረስ ባለው ጊዜ ድረስ፣ በፌደራል መንግሥቱ ዕውቅና ተሰጥቶት በመላ አገሪቱ ከዚያ ውጭ ያለ ዓርማ መያዝ የተከለከለ ነበር። ሆኖም ለውጥ ከተደረገ በኋላ በተፈጠረ አንፃራዊ ድፍረት የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይገልጸናል የሚሉትን ባንዲራ ሲጠቀሙ ተስተውሏል።
ቀድሞም ቢሆን ባለ አምስት ኮከብ አርማው የሕዝብን ፍላጎት ያላካተተ ነው ከሚሉ ቅሬታዎችም በላይ፣ የአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚታይበት እና የባዕድ አምልኮ መገለጫ ነው በሚል የማይቀበሉት አካላት በርካቶች ናቸው።
የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ ሦስት ላይ ስለ ኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ዓርማ ሲገልጽ፣ ‹‹ከሠንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ኃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንጸባርቅ ይሆናል›› ይላል።
ሆኖም ሕገ-መንግሥቱ ስለ ብሔራዊ ዓርማው ምንነት እና ማን እንደሚቀርጸው የሚገልጸው ነገር ባለመኖሩ፣ ኮከቡን ብሔራዊ ዓርማ ብሎ ለመቀበል እንደማይቻል ነው ይህን ከሚቃወሙ ወገኖች የሚሠማው ቅሬታ።
ስለሆነም፣ ማንም ሰው ይገልጸኛል የሚለውን ባንዲራ ይዞ መውጣት መከልከል ባይኖርበትም፣ በዚህ የተነሳ የሚፈጠረውን ዕሰጥ አገባ ለማስቀረት ተፈልጎ ከሆነ ግን፣ ሕዝብ ተወያይቶበት ኹሉም ባይስማማበት እንኳ አብላጫ ቁጥር ባላቸው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ቅቡልነት ያገኘ ዓርማ ማዘጋጀት እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሚሠነዝሩ በርካቶች ናቸው።
በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ማየት የማይፈልጉ፣ የዜጎችንም መብት የሚነፍጉ ኃይሎች በየጊዜው ብቅ ብቅ ሲሉ ይስተዋላል።
ከሠሞኑም የጥምቀትን በዓል መነሻ አድርገው የአገራቸውን ሠንደቅ ዓላማ የያዙ፣ እንዲሁም ሠንደቅ ዓላማውን የሚገልጹ ልዩ ልዩ ነገሮችን ይዘው ወደ አደባባይ ከወጡት አማኞች ውስጥ በዚህ የተነሳ የታሠሩ፣ የተደበደቡ፣ የሞቱ እንዲሁም አደባባይ እንዳይወጡ አስቀድሞም የተከለከሉ መኖራቸው የሚታወቅ ነው።
ይህ በዚህ ዓመት የታዬ እንግዳ ክስተት ሳይሆን፣ በየዓመቱ የአደባባይ በዓላት እና ሌሎች ዝግጅቶች ሲኖሩ የሚፈጠር የቆዬ ውጥረት ነው። የመብት ጥሰቱ የሚፈጸመው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ አካላት መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ ትኩረት ያሰጠዋል። መንግሥት በዜጎች መካከል ልዩነት መፈጠሩን ካስተዋለ፣ እንደየፍላጎታቸው እንዲሆኑ መፍቀድ ወይም ለጉዳዩ ዕልባት ለመፍጠር መሞከር እንጂ ያለበት፣ በቸልተኝነት መመልከት፣ ማሰር ወይም መከልከል ተገቢ እንዳልሆነ ብዙዎች ያወሳሉ።
ጥር 12/2014 በአዲስ አበባ ዙሪያ የወይ ብላ ማርያም እና የቅዱስ ሚካኤል ታቦትን ወደ መንበራቸው ለማስገባት የሔዱ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች፣ በመንግሥት የፀጥታ አካላት ማንኛውንም የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የሚገልጽ ነገር ካላስወገዳችሁ ማለፍ አትችሉም መባላቸውን ተከትሎ፣ በተፈጠረ ውዝግብ የሰው ሕይወት መጥፋቱ እና ብዙዎችም መጎዳታቸው የሚታወስ ነው።
ይህም ሠንደቅ ዓላማን ሠበብ የሚያደርግ ፖለቲካዊ ጫና መሆኑን ከማኅበረሰቡ የሚሠነዘሩ ቅሬታዎች ይጠቁማሉ። መከልከል ካለበት እንኳን ሊከለከል የሚገባው በአሸባሪነት የተፈረጀ ቡድን የሚጠቀመው ባንዲራ እንደሆነም ይነሳል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ ከዘንድሮው የጥምቀት በዓል ጋር በተያያዘ በዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቅሶ፣ ጉዳዩን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የኦሮሚያ የፀጥታ ዘርፍ አካላት ታቦታቱ እየተመለሱ ባለበት ወቅት ወደ ቤተ ክርስትያኗ ማለፊያውን መንገድ አጥረው በመያዝ ታቦታቱን ያጀቡ ምዕመናን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያለባቸውን ማንኛውንም ቁሶች (ግንባር ላይ የሚታሰር፣ እጅ ላይ የሚደረግ፣ የሴቶች የሀገር ባህል ቀሚስ ጥለት፣ ቲሸርት እንዲሁም የቤተ ክርስትያን መገልገያ የሆኑ ከበሮዎችን) ይዘው እንዳይገቡ በመከልከላቸው ከፍተኛ የሆነ ችግር ተፈጥሯል።
በዚህም ግጭት ኃይማኖታዊ በዓሉ በጸጥታ አካላት ምክንያትነት ከመረበሹም በላይ፣ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ሊደርስ ችሏል። ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥፋት ያጠፉ አካላት ድርጊታቸው በአግባቡ ተጣርቶ ዕርምጃ ሳይወሰድባቸው በመቅረቱ ተመሳሳይ ጥፋቶች እንዲበራከቱ በር ከፍቷል። የፀጥታ ኃይሎች የሕዝብን ደኅንነት ከማስጠበቅ ይልቅ እራሳቸው ስጋት ከመሆን መታረም አለባቸው›› ብሏል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በባንዲራ ሠበብ በዓሉን በሚያከብረው ሕዝብ ላይ የተፈጠረውን ጉዳት መሠረት አድርጎ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹በዚህ ግጭት ከልጅ እስከ አዛውንት የአካልና የሥነ-ልቦና ጉዳት በምዕመናኑ ላይ መድረሱን ተገንዝቤያለሁ›› ሲል ገልጿል። አክሎም መንግሥት አሁንም ሕግ የማስከበር ተቀዳሚ ተግባሩን አለመወጣቱን እንደሚያወግዝ ገልጾ፣ አሁንም እየደረሰ ላለው ውጥረትና ግጭት መንግሥት ሕግ እንዲያስከብርና ጉዳት ያደረሱ የጸጥታ አካላትም ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቋል።
ጠበቃ አበበ አሳመረም እንዲሁ ጉዳዩን አስመልክቶ ሀሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ፣ የሠንደቅ ዓላማውን ጉዳይ ከሕግ አንጻር ከማየት ይልቅ ከፖለቲካ አንጻር ማየት ይሻላል ይላሉ። ምክንያትም የሚሉት ሠንደቅ ዓላማ ከፖለቲካዊ ሥነ-ልቦነ ጋር በጣም የተቆራኘ መሆኑን ነው።
የተወሠነ የሕብረተሰብ ክፍል ሠንደቅ ዓላማውን በግዴታ እንድቀበለው ሆኛለሁ ይላል፣ ሌላው ደግሞ ሲነገር በነበረ ትርክት ጥላቻ አድሮበታል። ሕግ የማይፈታቸው ነገሮች እና ሕግ ስለወጣ የማይቀየሩ ማኅበራዊ ችግሮች ወይም ሥነልቦናዎች እንዳሉ ገልጸው፣ የሠንደቅ ዓላማውን ጉዳይም ሕግ ይፈታዋል ብሎ መናገር እንደሚያስቸግር ጠቁመዋል።
በሕገ-መንግሥቱ ዕውቅና የተሠጠው ሠንደቅ ዓላማ መኖሩ ይታወቃል፤ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ሠንደቅ ዓላማው ላይ የራሷ ዓርማ አላት። ይህ የሚያመላክተውም ሕዝብ ውስጥ ከዚህ ጋር የተያያዘ ኃይማኖታዊ ሥነልቦና መኖሩን ነው ብለዋል።
በዚህም ቤተክርስትያኗ በሠንደቅ ዓላማው ኃይማኖትን እና የአገርን ሉዓላዊነት ትገልጽበታለች የሚል ሐሳባቸውን አስቀምጠዋል። ስለሆነም በሕግ የተቀመጠ ሠንደቅ ዓላማ መኖሩን ተከትሎ ቤተክርስትያን የምትጠቀመው ሠንደቅ ዓላማ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ የሕግ መሠረት አለ ብዬ አላምንም ሲሉ ነው የተናገሩት።
እንዲሁም፣ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ራሱን ከባለ ኮከቡ ሠንደቅ ዓላማ መነጠሉን ነው ያነሱት። በዚህም ሕጉ የሚያወራው ሌላ፣ የሕዝቡ ፍላጎት ደግሞ ሌላ ነው ይላሉ።
ጠበቃው ለዚህ መፍትሔ ያመጣል ብለው ያስቀመጡት ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ነው። ብሔራዊ መግባባት ይደረጋል ሲባል ጥቅሙና ምንነቱ የሚገለጠው እዚህ ላይ ነው ያሉት ጠበቃው፣ ሕግ አለ ግን አይከበርም። ማኅበረሰቡም ሠንደቅ ዓላማ ይፈልጋል፤ ይህንም በተለያዩ ቦታዎች ይዞ በመውጣት ፍላጎቱን ሲያንጸባርቅ ይስተዋላል። መንግስት ደግሞ በሌላ በኩል ሕጋዊ ሠንደቅ ዓላማ አለና አስከብራለሁ ሲል ይታያል በማለት ገልጸዋል።
ይህን መሠረት አድርጎም የተፈጠረውን ምስቅልቅል የሚፈታ ብሔራዊ መግባባት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ብሔራዊ መግባባት መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች ላይ ምን ዓይነት ተመሳሳይ አቋም እንያዝ የሚለውን የሚመልስልን በመሆኑም፣ ኹሉም የሚስተካከለው ብሔራዊ መግባባትን በማሳደግ ነው ብለዋል። አክለውም፣ ይህን በመጠቀም አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ዓላማ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ይዘት እንደሌለው ለሕዝብ ማስገንዘብ ይገባል ባይ ናቸው።
ኾኖም፣ ብሔራዊ ምክክር አድርጎ እንዲህ ዓይነት የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት ቅድሚያ የዲሞክራሲ ባህል ሊኖር ይገባል። ይህ በሌለበት ግን ችግሩን መፍታት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሠንደቅ ዓላማው ላይ ለምን ልዩነት እንደተፈጠረ ይታወቃል። በዚህም ይደረጋል የተባለው ብሔራዊ መግባባት ለችግሩ መንስዔ የሆነውን የተሳሳተ ትርክት አስወግዶ ይህን ልዩነት እንዲፈታ ከተፈለገ በጣም ሥልታዊ እና ጥበባዊ አካሄድ ይፈልጋል ሲሉም ነው ያስገነዘቡት። ይህን ለማድረግም ጥሩ የሞራል መሠረት ያለው መንግሥት እንደሚያስፈልግ አትኩሮት ሰጥተውበታል።
በሠንደቅ ዓላማ የተነሳ የሚፈጠሩ ልዩነቶች እና ተያያዥ ችግሮች ታች ባለው ማኅበረሰብ ዘንድ እንደማይታወቁ እና አሉ ከተባለም በብሔር አቀንቃኞች ወደ ማኅበረሰቡ የወረዱ መሆናቸውን ገልጸው፣ አሁንም ቢሆን ችግሩ የሚፈታው እነዚህ አካላት ኃላፊነት የተሠማቸው እና መግባባት የቻሉ እንደሆነ ነው ሲሉ ዕምነታቸውን አክለዋል።
ተመሳሳይ ጽሁፎች
ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014



