ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 71.82 ሚሊዮን ብር ቀንሷል
የብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ ከእንስሳት ክትባት ምርቶች ሽያጭ 98.99 ሚሊዮን ብር ማግኘቱን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ከ1998 ጀምሮ ዓለም አቀፍ የክትባት አመራረት ዘዴዎችን ተግባር ላይ በማዋል የጥራት ሥራ አመራርን ዘርግቶ እየተገበረ ይገኛል የተባለው ተቋሙ፣ በ2014 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ስድስት ወር ውስጥ ብቻ ከእንስሳት ክትባት ሽያጭ 98.99 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የኢንስቲትዩት የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አደይአበባ ታምሩ ገልጸዋል።
በ2014 በጀት በግማሽ ዓመቱ ከእንስሳት ክትባት ሽያጭ የተገኘው ገቢ ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ71.82 ሚሊዮን ብር ቅናሽ አሳይቷል።
ለዘንደሮው ገቢ መቀነስ ምክንያቱ አገሪቱ ያለችበት የጦርነት ሁኔታ ሲሆን፣ በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ በቆዩት የትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ሠላም በነበረበት ወቅት ሲሸጥ የነበረው መድኃኒት በተለመደው መልኩ ባለመሸጡ መሆኑን ኃላፊዋ ተናግረዋል።
በዚህ ግማሽ ዓመት የክትባት ሽያጭ በዋናነት ዝቅ ያለበት ምክንያት፤ የዶሮ እርባታ ዘርፍ በመቀዛቀዙ ምክንያት የዶሮ ክትባት ሽያጭ በመቀነሱ፣ በተለይም የባክቴሪያል ክትባት ምርት በመቀነሱና የአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ በሽያጭ ላይ ተፅዕኖ በማድረጉ መሆኑን ኃላፊዋ አብራርተዋል።
በሌላ በኩል፣ እቅዱን ለማሳካት ካጋጠሙ ችግሮች መካከል የመብራት እና የዉጭ ምንዛሬ እጥረትም ተጠቃሽ ናቸዉ ነው የተባለው።
በ2014 በጀት ዓመት በስድስት ዓይነት የእንሳሳት መድኃኒቶች 22 ሚሊዮን ብር በላይ ‹‹ቦለስ›› ለማምረትና ለገበያ ለማቅረብ ባቀደዉ መሰረት፤ በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ኹለት የተለያዩ መድኒቶችን አምርቶ ለክልሎች መሸጡ ነው የተጠቆመው።
በበጀት ዓመቱ ለመመረትና ለመሸጥ ታስበው የነበሩት መድኃኒቶች Albendaze፤ Tetramisole፤ Albendaze፤ Tetramisole፤ Albendaze፤ Oxyclozanide፤ Levamisole፤ Oxyclozanide እና Levamisole (blister pack) Tetracycline ሲሆኑ፤ ከእነዚህም መካከል Tetracycline እና Albendazole የተሰኙት መድኃኒቶች ተሸጠዋል ነው የተባለው።
በዚህም፣ በአጠቃላይ በግማሽ ዓመቱ በውስጥና በውጭ አገር 175.43 ሚሊዮን ዶዝ የክትባት ምርት በመሸጥ 134.78 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ከታቀደው ውስጥ 123.42 ሚሊዮን ዶዝ የክትባት ምርቶችን በመሸጥ፣ የዕቅዱን 70.35 በመቶ በመጠን እና 73.4 በመቶ በገንዘብ ማሳካቱ ተመላክቷል።
በ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በውስጥና ውጭ አገር 377.90 ሚሊዮን ዶዝ የክትባት ምርት በመሸጥ፤ 240.49 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፤ ከታቀደው ውስጥ 267.85 ሚሊዮን ዶዝ የክትባት ምርቶችን በመሸጥ፤ 170.81 ሚሊዮን ብር በማግኘት የዕቅዱን 71 በመቶ በመጠን እና በገንዘብ ማከናወን ተችሎ ነበር።
የአገር ውስጥ ምርት ሽያጩ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን 23.57 ሚሊዮን ዶዝ (17 በመቶ) ዝቅ ያለ ሲሆን፣ በገንዘብ ደግሞ 14.68 ሚሊዮን ብር (20 በመቶ) ከፍ ያለ አፈጻጸም አሳይቷል።
ኢንስቲትዩቱ ትርፍና ትርፋማነትን ከማሳደግ አኳያ በ2014 በጀት ግማሽ ዓመት ከታክስ ክፍያ በፊት 42.57 ሚሊዮን ብር ትርፍ በማግኘት ካቀደው ውስጥ 59.49 በመቶውን ማሳካቱ ተገልጿል።
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ ከሆነ፣ ኢንስቲትዩቱ ክትባት ላልተመረተላቸው የእንስሳት በሽታዎች የክትባት ማበልፀግ ሥራና መሻሻል የሚያስፈልጋቸውን በመለየት የማሻሻል ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተጠቁሟል።
የብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ደረጃ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባት ምርቶችን በመጠንና በወቅት በማምረት ከታወቁ ተቋማት አንዱ ነው።
ተቋሙ መጀመሪያ ላይ በአራት የክትባት ዓይነቶች አራት ሚሊዮን ዶዝ ዓመታዊ ምርት በማምት ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ አሁን ላይ በ23 የክትባት ዓይነቶች በዓመት ወደ 336 ሚሊዮን ዶዝ የእንስሳት ክትባት ምርቶችን በማምረት ለውስጥ እና ለውጭ አገር ደንበኞች በማቅረብ ላይ ይገኛል።
ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014



