ከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ እንዲነሱ ትዕዛዝ አልሰጠሁም ብሏል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት፣ በመዲናዋ ዋና መንገድ ላይ ጫማ በማጽዳት የሚተዳደሩ ሰዎች (ሊስትሮዎች) በቋሚነት ሥራ እንዲያቆሙ መወሰኑን አስታወቀ።
በታኅሣሥ 29/2014 የተከበረውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጥሪ የተደረገላቸውን ዳያስፖራዎች መምጣት ተከትሎ፣ በመዲናዋ ውስጥ በጫማ ጽዳት ሥራ ተሠማርተው ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ዜጎች ከሥራቸው መታገዳቸውን በመግለጽ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ፣ በጫማ ማጽዳት የሚተዳደሩ ግለሰቦች ሠሞኑን ደግሞ ለአዲስ ማለዳ በድጋሚ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት የዳያስፖራውን መምጣት ተከትሎ “ደንቦች የከተማዋን ገጽታ ታደበዝዛላችሁ” ብለው ሥራ እንዲያቆሙ ያስገደዷቸው መሆኑን ገልጸው፣ በወቅቱ ቅሬታቸውን አቅርበው “ከ15 ቀን በኋላ ሥራ ትጀምራላችሁ” ተብለው እንደነበር ነው ያብራሩት።
አሁን ላይ ግን፣ ሠሞኑን አዲስ አበባ ላይ የሚካሔደውን የአፍሪካ ኅብረት ስብስባ ምክንያት በማድረግ ደንቦቹ በድጋሚ ከሥራቸው ተነሱ እንዳሏቸውና እስከመጨረሻው መሥራት እንደማይችሉ እንዳረዷቸው ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል፣ በሊስትሮ ሥራ ቤተሰባቸውን እንደሚያስተዳድሩ የሚገልጹትና በባምቢስ አካባቢ ሲሠሩ የነበሩት መስፍን አርሳዶ የተባሉ ግለሰብ እንደሚሉት ከሆነ፣ ደንቦች በድጋሚ መጥተው እስከመጨረሻው ሥራ ማቆም እንዳለባቸው እንደነገሯቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በላቸው ማት የተባሉ ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው፣ የዳያስፖራውን መምጣት ተከትሎ ለአንድ ወር ሥራ እንዳልሰሩ ገልጸው፣ አራት ቤተሰቦቻቸውን ከሊስትሮ ሥራ በሚገኝ ገቢ የሚያስተዳድሩ በመሆኑ ሥራ ካቆምኩ ቤተሰባቸውን በምን ማስተዳደር እንዳለባቸው እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከዚህ ቀደም ከሥራ በመነሳታቸው ለአንድ ወር ችግር ላይ እንደነበሩ ገልጸው፣ አሁን ላይ ደግሞ በቋሚነት ተነሱ ስለተባሉ መንግሥት ችግራቸውን ተመልክቶ መፍትሔ ሊሠጣቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አዲስ ማለዳ የሠራተኞቹን ቅሬታ ይዛ ወደ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ያቀናች ሲሆን፣ ከኃላፊዎቹ ያገኘችው ምላሽም በሊስትሮ ሥራ የተሠማሩ ሠራተኞች በመዲናዋ ውስጥ ባሉት ዋና መንገዶች ከዚህ በኋላ መሥራት እንደሌለባቸውና በቋሚነት ሥራቸውን ማቆም እንዳለባቸው የሚገልጽ ነው።
በጉዳዩ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሻምበል ኑርልኝ፣ ሊስትሮዎቹ በከተማዋ በሚገኙ ዋና መንገዶች እንዳይሠሩ በቋሚነት መታገዳቸውን መስክረዋል።
ሊስትሮዎቹ በቋሚነት መሥራት የሚችሉት በኹለተኛ መንገድ ላይ እንጂ በዋናዎና መንገዶች ላይ መሆን የለበትም የሚሉት ኃላፊው፣ ሁኔታው የመንገዶችን ውበት መቀነሱ ብቻ ሳይሆን የጸጥታ ሥጋትም እየፈጠረ በመሆኑ በዋና መንገድ ላይ መሥራት አይችሉም ነው ያሉት።
መመሪያው በከተማ አስተዳደሩ በአቅጣጫ የተቀመጠ ነው የሚሉት ሻምበል፣ በዋና መንገድ ላይ የሚቀመጡ በሊስትሮ ሥራ የተሠማሩ ሰዎችን በኹለተኛ መንገድ እንዲቀመጡ የማድረግ ሥራችንን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ ግለሰቦቹ ባቀረቡት ቅሬታ መሠረት፣ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩት ከዚሁ ሥራ በሚያገኙት ገቢ መሆኑንና አሁን ላይ ከሥራ በመታገዳቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ገልጻ፣ ምን ሠርተው ይበላሉ? ስትል ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ ኃላፊውም የከተማዋን ውበት በማያደበዝዝ መልኩ በላሜራ ቤቶች ተዘጋጅተውላቸው እንዲሠሩ የማድረግ አቅጣጫ እየታሰበ መሆኑን ገልጸዋል።
በጉዳዩን በማስመልከት ለአዲስ ማለዳ ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ዳይሬክተር ዮናስ ዘውዴ “ልጆቹ ይነሱ የሚል መልዕክት አልተላለፈም። መነሳት አለባቸው ብዬም አላምንም” የሚል ምላሽ ሠጥተዋታል።
አክለውም፣ “እነዚህ ሰዎች ዜጎች ናቸው፤ አንዳንድ ሰዎች ለከተማ ገጽታ ሲባል የሊስትሮ ሠራተኞች መነሳት አለባቸው ቢሉም እኔ አልስማማበትም” ነው ያሉት።
በመጨረሻም፣ ሊስትሮ የሚሠሩ ሰዎች ጥሩ የጫማ ማጽጃ ቦታዎችና ዕቃዎች ተሟልተውላቸው እንደተባለው ቦታ ተቀይሮላቸው እንዲሠሩ ማድረግ እንጂ፣ የዕለት ተዕለት ምግብ የሚያገኙበትን ሥራ እንዲያቆሙ ማድረግ መፍትሔ እንደማይሆን ተናግረዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014



