በባህላችን ድግስም ሆነ የትኛውም ግብዣ ቦታውና ሠዓቱ ተጠቅሶ ለተጠሪ ይላካል። ተጋባዡም ሆነ በጉባዔው እንዲካፈል የተጠራው ወገን ቦታውም ሆነ ሠዓቱ ይቀየርልኝም ሆነ እዚህ ቦታ ይሁን ብሎ የጠሪዎቹን መርሃ-ግብር ሠርዞ የራሱን አቅዶ የጥሪ ጥሪ ማቅረብ አይቻለውም።
ተጠሪ ሠዓቱም ሆነ ቦታው ካልተመቸው ይቀራል እንጂ፣ እንደፍርድ ቤት የክስ ምላሽ የመልስ መልስ አይሰጥም። ይህ በድግስም ሆነ በማንኛውም ግብዣ ላይ ብቻ ሳይሆን በሽምግልናም ሆነ በሐዘን፣ አሊያም በማንኛውም ስብሰባና ውይይት ሲተገበር የቆየ ነው።
በያዝነው ሳምንት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ-ክርስትያን ጥሪ መሠረት ለውይይት የተጠሩት የአዲስ አበባ ከንቲባ በቀጠሮው ቦታ ሳይገኙ መቅረታቸውን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የሠጠው ምላሽ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል። ከባህልና ሥርዓት ውጭ የሆነ ብቻ ሳይሆን የአንድ ብዙ ሚሊየን ተከታይ ያላትን ተቋም ክብር ያልጠበቀ፣ ኹሉንም በእኩል አያለሁ ብሎ ሥልጣንን ከተረከበ መንግሥት የማይጠበቅ ሲሉ ብዙዎች ድርጊቱን ኮንነውታል።
ውይይቱን የጠራው ማን እንደሆነ እየታወቀ “አልመጣም” ማለት ያባት ሆኖ ሳለ፣ በሕዝብ ገንዘብ ያልተጠሩበት ቦታ ወጪ አውጥቶ መጠበቅ ምን የሚሉት ድፍረት ነው በማለት ትዝብታቸውን ያጋሩ አሉ። ጉዳዩ ለሳምንታት ሲንከባለል የቆየ እንደመሆኑ፣ ከንቲባዋ አይገኙም ብለው የሚሄዱበትን ሲተነብዩ የቆዩ ነበሩ። እንደማይገኙ ሲገምቱ የነበሩ ግን ራሳቸው ሌላ ቦታ ጠሪ ይሆናሉ ብለው አላሰቡም ነበር።
የተጠሪ ጠሪ ሆኖ መድረክ ይዞ፣ “እናንተ ኑ” ብሎ ጠብቆ እንዳልመጡለት የተናገረው የከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ ስለመጠራቱና ቦታ ስለመቀየሩ ምንም ሳይል እንደእግር ኳስ በ‹ፎርፌ› የሚያሸንፍ መስሎት፣ “አልተገኙልኝም” ሲል የኃይማኖት አባቶችን ከሷል ሲሉ ድርጊቱን ውንጀላ አድርገው የተመለከቱት ተናግረዋል። መንግሥትን ወክለው ከከንቲባዋ ጋር መድረክ ላይ ሆነው ፎቶ ተነስተው ስንጠብቅ ነበር ያሉት 7 የካቢኔው አባላት የተባሉ ሰዎች ማንን ወይም የትኛውን ኃይማኖት ወክለው እንደተገኙ ባይነገርም፣ አንድ ከንቲባ እንዲያብራሩ በተጠሩበት መገኘታቸው ጫና ለማሳደር መሞከራቸው ነው ሲሉ የተቀነባበረ ነገር ሳይኖር እንደማይቀር የተናገሩም ነበሩ።
የኃይማኖት መሪዎች ይቅርና የዕምነት ሰዎች ኃይማኖታቸው በሚያዛቸው ቦታና ሠዓት ብቻ እንደሚገኙ ይታወቃል። ሙዚቃ እንዳይሰማ የሚከለከልን ጭፈራ ቤት፤ መጠጥ የማይፈቀድለትን መጥመቂያ ፋብሪካ፣ ሥጋ እንዳይበላ የተከለከለን ቄራ እንዲገኝ መጋበዝም ሆነ መጥራት፣ እንዳይመጣ ከመከልከል አይተናነስም በሚል መንግሥት የኃይማኖት አባቶቹን የጠራበትን ቦታም የኮነኑ አሉ። “ሒድ አትበለው እንዲሔድ አድርገው” የሚለው የቀደመችው የኢሕአዴግ ዘመን መፈክር ተገልብጣ መጣች ያሉም ነበሩ።
ከንቲባዋ የዕምነቱ ተከታይ ባይሆኑም፣ እንደሌሎች ባለሥልጣናት በጥምቀት ሆነ በእሬቻም ማክበሪያ እንደተገኙት፣ ጥሪውን ንቀው ካልሆነ በስተቀር አይቀሩም ነበር እያሉ የአንድ ግለሰብ ስቱዲዮ መገኘታቸውን ማነጻጸሪያ አድርገው አንዳንዶች ተችተዋል። ያም ተባለ ይህ፣ የጠሪና የተጠሪ መብትና ግዴታዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው በባህልም ሆነ በሕግ ሊከበሩ ይገባል።
ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014



