“የኢትዮጵያ መስከረም”- በማረሚያ ቤት

0
1201

አርቲስት ደረጀ በለጠ ትውልድ እና ዕድገቱ በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ነው። የደረጀ ሕይወት ከኢትዮጵያ ባህላት ጋር የተጋመደ ሲሆን፣ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ከተከታተለ በኋላ፣ ገና በለጋ ዕድሜው ከሚወደውና ዘርፈ ብዙ ከሆነው የኢትዮጵያ ባህል ጋር የሚያቆራኘውን መንገድ ጀመረ። ደረጀ ከኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ባህላት ጋር የሚያቆራኘውን መንገድ የጀመረው በአንጋፋው እና የብዙዎች ባለውለታ በሆነው በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የባህል ሙዚቃ ውዝዋዜን በማጥናት ነበር።

ከባህል እና ከተፈጥሮ ጋር ሕይወቱ የተቆራኘው ደረጀ፣ በያሬድ መዚቃ ትምህርት ቤት ከተማረው የባህል ውዝዋዜ በተጨማሪ “አዲስ ፋይን አርት” በተባለ ትምህርት ቤት የሥዕል ጥበብን አጥንቷል። በባህል ውዝዋዜ እና በሥነ ሥዕል ትምህርት የተጀመረው የደረጀ ባህልን የማስተዋወቅ እና ባህላዊ ሥራዎችን የመከወን ሕልም፣ በ1987 ወደ ተቋም አድጎ “Face of Ethiopia cultural event organizer” የተባለ የተለያዩ የባህል ኩነቶችን የሚያዘጋጅ ድርጅት እና “Yedegaw Abeba traditional music and folk dance club” የተሰኘ የባህል የሙዚቃ ቡድን (ባንድ) በማቋቋም ተጀምረ።

ደረጃ በቤተሰቦቹ እና በጓደኞቹ ድጋፍ ባቋቋማቸው የባህል ሥራዎችን በሚከውኑ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ባህል እና የባህል ሙዚቃን የማሳደግ ሕልሙን ጀመረ። በኩነቶች (ኢቨንት) አዘጋጅ ድርጅቱ የኢትዮጵያን ልዩልዩ የባህል አልባሳት፣ የባህል ምግቦች እና ሌሎችም የባህል ዝግጅቶችን ለ20 ዓመት ያክል አስተዋውቋል። በ20 ዓመት ውስጥ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የተለያዩ ኢምባሲዎች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ የባህል አልባሳት ለውጭ ዜጎች አስተዋውቋል። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ባህላዊ የቡና ሥርዓት እና የባህል ፋሽን ዝግጅት ማዘጋጀቱንም ከአዲስ ማለዳ ገር ባደረገው ቆይታ አስታውሷል።

በባህል የሙዚቃ ቡድኑ ደግሞ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የተማረውን የባህል ውዝዋዜ ጨምሮ፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ፣ የብሔር ብሔረሰቦችን የባህል የሙዚቃ መሣሪያዎች በአዲስ አበባ፣ በአሜሪካ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በጣሊያን እና በጀርመን ለ20 ዓመት አስተዋውቋል።

ደረጀ ከ20 ዓመታት በኋላ የሚወደውን የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ እና የተለያዩ የባህል ዝግጅቶችን ማስቀጠል አልቻለም። በ1987 የተጀመረው የኢትዮጵያን ባህል የማስዋወቅ ሕልም ከ20 ዓመታት በላይ መጓዝ አልቻለም። ደረጀ የኢትዮጵያን ባህል የማስተዋወቅ ሕልሜ ከተጀመረ ከ20 ዓመት በኋላ የተገታው በ2007 “በሥራ ባልደረቦቼ በተቀነባበረ ክስ ለዕሥር በመዳረጌ ነበር” ይላል ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው ቆይታ።

ደረጀ በ2007 ለዕሥር የዳረገውን በጓደኞቹ የተመሠረተበትን “የማታለል” ክስ ሲያስታውስ፣ በሕይወቴ ላይ ተስፋ እንድቆርጥ ያደረገኝ ነበር ይላል። ጓደኞቹ የመሠረቱበትን “የማታለል” ክስ በወቅቱ ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት የከሳሾቼን እንጅ የእኔን እውነት መስማት ባለመፈለጉ ሒደቱ ተስፋ አስቆራጭ ነበር የሚለው ደረጀ፣ “ሲሰለቸኝ የሚሰማኝ ሳጣ ጥፋተኛ ነህ ካላችሁኝ የፈለጋችሁትን ፍረዱብኝ ብዬ ተስፋ መቁረጤን ተናገርኩ” ይላል።

ደረጀ በፍርድ ሒደቱ ተስፋ በመቁረጡ እና ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን እንዲመረምርለት ቢጠይቅም ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ፣ 10 ዓመት ቅጣት ተፈረደብኝ ይላል። ለ20 ዓመት የዘለቀው የደረጀ የባህል ሙዚቃን እና የኢትዮጵያን ባህል የማስተዋወቅ ሕልም ደረጀን ተከትሎ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ገባ። ደረጀ እንደሚለው ባላሰበው እና ባልጠበቀው ኹኔታ በጓደኞቹ በተመሠረተበት ክስ 10 ዓመት ሲፈረድበት የተስፋ መቁረጥ እና የሞራል ጉዳት ደርሶበት እንደነበር ያስታውሳል።

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ደረጀ 10 ዓመት በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ሲፈረድበት በተስፋ መቁረጥ ስሜት ነበር ወደ ማረሚያ ቤት የተሸኘው። ከተወሠነ ጊዜያት በኋላ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤት የተዘዋወረው ደረጀ፣ የውጭ ሕይወቱን ባገኘው አጋጣሚ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ሆኖ ለመከተል ይሞክራል። በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎችን ሰብስቦ ባገኙት ነገር በኢትዮጵያ ባህል በዓላትን ተሰባስበው እንዲያከብሩ ይደርጋል።

የማረሚያ ቤት ታራሚዎች ማኅበራዊ ግንኙነታቸው እንዲጠናከር የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ እንደነበር የሚያስታውሰው ደረጀ፣ ዝዋይ ማረሚያ ቤት በታራሚዎች መካከል ኹል ጊዜ ጸብ እና ደብድብ የማይጠፋበት ነው ይላል። ታዲያ ደረጀ እንደሚለው ከሆነ፣ በዝዋይ ማረሚያ ቤት ታራሚዎች ሲጣሉ እና እርስበርስ ሲጋጩ ሲያስታረቅ እና ማኅበራዊ ግንኙነታቸው እንዲጠነክር ሲሠራ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ይገልጻል።

ደረጀ በማረሚያ ቤት የሚወደውን የባህል ሙዚቃ ሥራ መከወን ባይችለም፣ በማረሚያ ቤት ማከናወን የሚችለውንና ከሙያዎቹ አንዱ የሆነውን ሥዕል በመሳል ጊዜውን ያሳልፍ እንደነበር ያስታውሳል። የሚስላቸው የተለያዩ ሥዕሎች የማረሚያ ቤቱ ሠዎች እና ታራሚዎች ስለሚወዷቸው እንደ ፍሬም እና ቀለም የመሳሰሉ የሥዕል ግብዓቶችን እንደሚገዙለት ይገልጻል።

ደረጀ 10 ዓመት ቢፈረድበትም ከስድስት ዓመት ከሰባት ወራት ዕስር ብኋላ፣ በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውደ ውሳኔ መሠረት ከወራት በፊት ከዝዋይ ማረሚያ ቤት መውጣት ችሏል። ደረጀ ከዕስር ቤት የወጣው ከፕሬዝዳንቷ ለማረሚያ ቤቱ በተጻፈ ደብዳቤ ሲሆን፣ ከስድስት ዓመት ዕስር በኋላ ወደሚወደው ሥራ ለመመለስ ደፋ ቀና አያለ መሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ ጠቁሟል።

ደረጀ በስድስት ዓመት የማረሚያ ቤት ቆይታው፣ ከሥዕል ሥራ በተጨማሪ መጻሕፍትን አንብቧል፤ በማረሚያ ቤቱ የሚሠጡ የተለያዩ አጫጫር ሥልጠናዎችንና ትምህርቶችን ተከታትሏል። በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ሳለ በኮምፒውተር ሳይንስ እስከ ደረጃ አራት የተማረ ሲሆን፣ በሥነ-ልቦና፣ በሕግ ክህሎት የተለያዩ ሥልጠናዎችን ወስዶ ሠርተፍኬት ማግኘቱን ይገልጻል።

ይሁን እንጂ፣ ደረጀ በማረሚያ ቤት ቆይታው የሚወደውን የባህል ሥራዎች መከወን አልቻለም። በወቅቱ ከሥዕል፣ ከትምህርትና ከማንበብ ውጭ ሌላ አማራጭ ስላልነበረው በስድስት ዓመት የማረሚያ ቤት ቆይታው 700 ግጥሞችን እንደጻፈ ይናገራል። ደረጀ በማረሚያ ቤት ስለሚታዘባቸው ነገሮች፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አገር፣ ስለ ተፈጥሮ አና ሌሎች ጉዳዮች ለስድስት ዓመታት ግጥም ደርድሯል።

በዝዋይ ማረሚያ ቤት የተደረደሩት 700 የደረጀ ግጥሞች፣ የደረጀን ከዕሥር መፈታት ተከትሎ፣ የኅትመት ብርሃን ለማየት ቋምጠዋል። ደረጀ ከዕሥር እንደተፈታ የጻፋቸውን ግጥሞች ለማሳተም ውሎ ሳያድር ነበር አሳታሚዎችን መፈለግ የጀመረው። ደረጀ የግጥሞቹን የኅትመት ብርሃን የማየት ጉጉት ለማሳካት ባደረገው ጥረት የመጀመሪያ የግጥም መድብሉን የሚያሳትሙለት ሰዎችን አገኘ።

የደረጀ የዝዋይ ማረሚያ ቤት ሥራዎች፣ “የኢትዮጵያ መስከረም” ተብለው ለመታተም በቅተዋል። የደረጀ የበኩር ልጅ የሆነው “የኢትዮጵያ መስከርም” የግጥም መድብል፣ ጸሐፊው ከጻፋቸው 700 ግጥሞች መካከል 100ዎቹን ያቀፈ ነው። በዝዋይ ማረሚያ ቤት ተከትበው፣ በ“የኢትዮጵያ መስከረም” ታቅፈው ለኅትመት ብርሃን የበቁት የደረጀ ግጥሞች ለሕዝብ የሚደርሱበትን ቀናት እየተጠባበቁ ሲሆን፣ በቅርቡ ከሚካሄደው የግጥም መድብሉ ምርቃት በኋላ ለአንባቢያን እንደሚደርሱ ደረጀ ጠቁሟል።

100 ግጥሞች የያዘው የ“ኢትዮጵያ መስከርም” የግጥም መድብል ተመርቆ ለሕዝብ ከደረሰ በኋላ፣ እንደየኹኔታው ቀሪዎቹ 600 የዝዋይ ማረሚያ ቤት ውጤቶች ለኅትመት ብርሃን እንደሚበቁ ደረጃ ይናገራል። “የኢትዮጵያ መስከረም” ውስጥ የቀረቡት ግጥሞች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተጻፉ እና በተመረጡ ቃላት የተሠደሩ መሆናቸውን ጸሐፊው ይገልጻል። የግጥም መድብሉ በየዓመቱ ሲመጣ ልዩ ስሜት እና የአዲስ መንፈስ መገለጫ በሆነው በመስከረም ወር መሰየሙን ደረጀ ይናገራል።

ደረጀ በ“የኢትዮጵያ መስከረም” የግጥም መድብሉ ምርቃት ላይ ቀድሞ ይሠራቸው የነበሩ የጥንት ኢትዮጵያ ባህል የማስተዋወቅ ሥራን እንደሚጀምርና የጥንት የአገር ባለውለታ የሆነ ተቋማተን እንደሚያመሰግን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ይመሰገናሉ ከተባሉት የጥንት የአገር ባለውለታ ተቋማት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ አንበሳ አውቶቡስ፣ ኢትዮጵያ ሆቴል እና ሌሎችም እንደሚገኙበት ደረጀ ጠቁሟል።

ደረጀ ከ“የኢትዮጵያ መስከርም” የግጥም መድብል ምርቃት በኋላ ለ20 ዓመታት ወደ ሠራው የባህል ሙዚቃ እና የባህል ማስተዋወቅ ሥራ የመመለስ ዕቅድ እንዳለው ለአዲስ ማለደ ጠቁሟል። ኢትዮጵያ የግዙፍ ባህል ባለቤት ናት የሚለው ደረጀ፣ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የጥንት የኢትዮጵያን ባህላት በማስተዋወቅ እና የባህል ዝግጅቶችን በማዘጋጀት ረገድ ሠፊ እንቅስቃሴ እንደማይታይ ይገልጻል። የኢትዮጵያ ባህል ለዓለም ገበያ በሥፋት ቢተዋወቅ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚኖረው ሚና የጎላ ቢሆንም፣ ባህልን የመጠበቅ እና የማስተዋወቅ ሥራዎች በሥፋት አይታዩም ብሏል።

ኢትዮጵያ በውስጧ የያዘቻቸው የተለያዩ ባህሎችን የመጠበቅ፣ በአገር ውስጥ እና በዓለም ላይ ባህልን የማስተዋወቅ ሥራ ቢሠራ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ እንድትታወቅ እና ያሏት ባህሎች ትልቅ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚቻል ደረጀ ይገልጻል።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here