ህወሃት እንደ አዲስ ጦርነት በከፈተበት በአፋር ክልል ከ300 ሺህ በላይ ንፁሃን ዜጎች መፈናቀላቸው ተገለፀ

0
903

ዕረቡ የካቲት 2 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የህወሃት ቡድን እንደ አዲስ ጦርነት በከፈተበት በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን 6 ወረዳዎችን በመቆጣጠር፣ በተለይም ህፃናት፣ ሴቶችና አዛውንቶችን በአሰቃቂ ሁኔታ የዘር ማጥፋት መፈፀሙንና፤ ከእነዚህ ወረዳዎችም ከ300 ሺህ በላይ ንፁሃን አርብቶ አደሮች እንዲፈናቀሉ እና ከባድ ለሆነ ስቃይና እንግልት መዳረጋቸውን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አወል አርባ ገለፁ።

የክልሉ ፕሬዝዳንት ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና መሀመድ ከተመራው ልኡክ ጋር በሰመራ ከተማ ተወያይተዋል።

በውይይቱም ፕሬዝዳንት አወል አርባ ህወሃት በአፋር ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት የጅምላ ግድያ ግፍና ሰቆቃ አስመልክቶ ለልኡኩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የህወሃት ቡድን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በአፋር ንፁሀን አርብቶ አደሮች ላይ እያደረሰ ያለው የዘር ማጥፋት እንዳልቆመና አርብቶ አደሩ ህዝብን ከጅምላ ግድያ የዘር ማጥፋት ጀምሮ ስቃይ እና እንግልት እያደረሰ መሆኑን ገልፀዋል።

አፋር ከትግራይ ክልል አንድ ሴንቲ ሜትር እንኳን ሳይገባ የህወሃት ቡድን የአፋርን ወሰን በርካታ ዞኖችንና ወረዳዎችን ዘልቆ በመግባት እጅግ አሰቃቂ የሆነ ግፍ እና በደል አለም አቀፍ ወንጀል ፈፅሟል ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ በገለፃቸውም ቡድኑ ህፃናትን ፣ ሴቶችንና አዛውንቶችን ያለምንም ርህራሄ አረመኔያዊ በሆነ መልኩ በከባድ መሳሪያ በመድብደብ ዘር የማጥፋት ወንጀል በንፁሃን አርብቶ አደሮች ላይ መፈፀሙን አውስተው፤ ይህም ድርጊቱ በተፈፀመባቸው አካባቢዎች ሁሉ እውነታ በተጨባጭ የሚታይ እውነታ መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑ በተለይም እንደ አዲስ ጦርነት በከፈተበት በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን ስድስት ወረዳዎችን በመቆጣጠር በገቡባቸው ወረወዳዎች ሁሉ በተለይም ህፃናት፣ ሴቶችና አዛውንቶችን በአሰቃቂ ሁኔታ የዘር ማጥፋት የፈፀመ ሲሆን ከነዚህ ወረዳዎችም ከ 300 ሺህ በላይ ንፁሃን አርብቶ አደሮች እንዲፈናቀሉ እና ከባድ ለሆነ ስቃይና እንግልት መዳረጋቸውን ፕሬዝዳንት አወል አርባ ገልፀው፤ በከበደ ችግር ውስጥ ላለው የአፋር ህዝብ አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይቱም ፕሬዝዳንቱ “አለም የገዳዮችን ድምፅ የሚሰማበት የሟቾችን ድምፅ የማይሰማበት ምክንያት ምን ይሆን?” ሲሉ በመጠየቅ የአለም መንግስታትና ሚዲያዎች የሟቾችን ድምፅ ሊሰሙ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከውይይቱ በኋላም ልኡካን ቡድኑ ህወሃት በቅርቡ በኪልበቲ ረሱ ዞን በከፈተው ጦርነት በከባድ መሳሪያ ባደረገው ድብደባ የተጎዱ ህፃናትን በዱብቲ ሆስፒታል በመገኘት የጎበኙ ሲሆን በጉብኝታቸው ባዩት ነገር በጣም ማዘናቸውንና ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ እንደሚሰሩም መገለፁን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

  

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here