የደህንነት ችግር እንዳያስከትሉ ለተሰጉ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ፍቃድ መሰጠት ተጀመረ

0
644

ዕረቡ የካቲት 2 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የደህንነት ችግር እንዳያስከትሉ ለተሰጉና ለ25 ሺህ በግለሰብ እና በመንግስት እጅ ለሚገኙ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ፍቃድ መሰጠት መጀመሩን የቴክኖሎጂ እና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ገለፀ፡፡

ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም በአገር አቀፍ ደረጃ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን የያዘ አካል እንዲያስመዘግብ ማሳወቁ ይታወሳል።

የቴክኖሎጂ እና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በተቋቋመበት አዋጅ በተሰጠዉ ሃላፊነት መሰረት የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን መመዝገብ አንዱ እና ዋነኛዉ ሃላፊነቱ ነዉ ያሉት፤ በኤጀንሲዉ የቴክኖሎጂ መረጃ እና መገናኛ ቁጥጥር እና ዉል ዝግጅት ቡድን መሪ የሆኑት ተመስገን አስማረ ናቸው፡፡

ቡድን መሪው ተቋሙ ይህንን ሃላፊነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ለቴክኖሎጂ መሳሪያዎቹ ፍቃድ መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በአገራችን ላይ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እና ማህበራዊ ችግሮችን እንዳያስከትሉ ከደህንነት አንጻር ምዝገባዎች ተካሂደዉ ፍቃዱ መጀመሩ ነዉ የተገለጸዉ፡፡

ፍቃዱ የሚሰጣቸዉ መሳሪያዎች 6 ሲሆኑ ድሮን፣ ጂፒኤስ፣ የሬድዮ መገናኛዎች፣ የወታደር መነጽሮች፣ ሳትፎኖች እና ቪሳቶች መሆናቸዉ ተገልጿል፡፡

እነዚህ መሳሪያዎች በጥቅሉ 25 ሺህ ሲሆኑ፣ በህዳር ወር ለተከታታይ 20 ቀናት ምዝገባቸዉ መካሄዱን ገልጸው፤ ከሰኞ ጀምሮ ፍቃዱ እየተሰጣቸዉ ያሉትም እነዚህ ማስመዝገብ የቻሉት ብቻ ናቸዉ ብለዋል፡፡

ምዝገባዉ የተካሄደዉ በመላዉ አገራችን ሲሆን በአካል ቢሮዉ ድረስ መምጣት አስፈላጊ እንደነበርም ነዉ የተነሳዉ፡፡ ኤጀንሲዉ ፍቃዱ ለመስጠት መስፈርቶች አስቀምጧል፡፡

ለመስፈርቶቹ መካከል ከግልም ሆነ ከተቋም ሲመጣ ስለመሳሪያዉ ባለቤትነት የሚገልጽ ህጋዊ ደብዳቤ እና ህጋዊ መታወቂያ ይዞ መገኘት መሆኑ አንዱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

እንደየስራ ባህሪያቸዉ መሰረት መቆጣጠር፣ አደጋ እንዳያስከትል መጠንቀቅ እና ሃላፊነት መዉሰድ የሚችሉ ከኤጀንሲዉ ጋር ሥምምነት በመግባት ንብረቶቻቸዉን እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

ፍቃድ መስጠቱ ለተከታታይ 3 ሳምንታት ይቀጥላል መባሉን ኢትዮ ኤፍ ኤም ዘግቧል፡፡

ከዚህ በፊት በተሰጠዉ ግዜ ማስመዝገብ ያልቻሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች በቂ እና አሳማኝ ምክንያት ይዘዉ ሲቀርቡ እና ከመንግስት ፍቃድ ሲያገኙ ምዝገባ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here