ትምህርት ሚኒስቴር ለዓመታት ያለ ዕውቅና እና የሚጠበቅበትን ግብር ሳይከፍል ሲሠራ የኖረውን የግሪክ ማኅበረሠብ ትምህርት ቤት፣ ዕውቅና እንዲኖረውና ከተሠጡት ሦስት አማራጮች አንዱን ይዞ እንዲቀጥል ትዕዛዝ መስጠቱን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
በዚህም፣ የማኅበረሠብ ትምህርት ቤት፣ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ወይም መደበኛ የግል ትምህርት ቤት ኾኖ እንዲቀጥልና በአምስት ሳምንት ውስጥ አንዱን መርጦ ውሳኔውን እንዲያሳውቅ በግሪክ ኤምባሲ በኩል ለትምህርት ቤቱ ትዕዛዝ እንደተላለፈለት ነው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የገለጸው።
ኾኖም በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ያሉበት የእንግሊዘኛ ክፍሉ (English Section) እንዴት ኾኖ የግሪክን ሥርዓተ ትምህርት ሊከተል ይችላል በሚል ለቀረበው ጥያቄ፣ በሚኒስቴሩ የትምህርት ኢንስፔክሽን ጀኔራል ዳይሬክተር የሆኑት ሙሉቀን ንጋት(ዶ/ር) ማንም የፈለገውን አገር ሥርዓተ- ትምህርት ለመማር ፍላጎት እስካለው ድረስ አይከለከልም የሚል መልስ ሠጥተዋል።
ትምህርት ቤቱ እስካሁን በግሪክ ኤምባሲ ሥር ሆኖ መቆየቱን የግሪክ አምባሳዳር ቀርበው አስረድተዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የመማሪያ ቋንቋው ግሪክኛና እንግሊዝኛ ተብሎ ተከፋፈለ እንጂ ኹለት ትምህርት ቤት እንዳልሆነ አምባሳደሯ መናገራቸውን ነው ያስረዱት።
ዳይሬክተሩ ይህን ይበሉ እንጂ፣ ትምህርት ቤቱ ይህን እንደማይቀበልና ከኤምባሲው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ኖሮት እንደማያውቅ ለትምህርት ሚኒስቴር ደብዳቤ ጽፎ እንደነበር ከተማሪ ወላጆች የተገኘው ደብዳቤ ያመላክታል።
እስካሁን በነበረው አሠራር ኢንተርናሽናልና ማኅበረሠብ ትምህርት ቤቶችን ለመቆጣጠር የተዘጋጀ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ መቆጣጠር አስቸጋሪ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ፣ አሁን ላይ የግሪክ ማኀበረሠብ ትምህርት ቤትም ሕጋዊ መስመር ይዞ እንዲሠራ ትዕዛዝ እንደተሠጠው አብራርተዋል። በዚህም በተለይ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ለመሆን ከወሰነ፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ፣ ንግድ ፈቃድ፣ እንዲሁም ከካምብሪጅ የሥርዓተ-ትምህርት ፈቃድ ማምጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ኾኖም የትምህርት ቤቱ ግሪክ ክፍል ከ100 ዓመታት በላይ፣ የእንግሊዘኛ ክፍሉ ደግሞ ከ25 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ መቆየቱን አዲስ ማለዳ አስታውሳ፣ እንዴት የንግድም ይሁን የኢንቨስትመንት ፈቃድ መጀመሪያ አልተጠየቁም በሚል ላቀረበችላቸው ጥያቄ፣ የራሳቸውን ዜጎች ለማስተማር የግሪክ ማኅበረሠብ ትምህርት ቤት በሚል ፈቃድ ካገኘኙ በኋላ፣ በዚህ ሠበብ የኢትዮጵያና ሌሎች አገራት ተማሪዎች የሚማሩበትን የእንግሊዘኛ ክፍል አቋቁመው እንደሚያስተምሩ ሳይታወቅ እንደቆየ ጠቅሰዋል።
አያይዘውም፣ የሚከታተላቸው ቡድን ቦታው ድረስ ሔዶ ትምህርት ቤቱን ካየ በኋላ፣ ኹሉም ነገር በሥርዓት እየተከናወነ ነው ብሎ ለትምህርት ሚኒስቴር ሪፖርት ሲያደርግ እንደኖረ ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ ስለጉዳዩ ፍትሕ ሚኒስቴርን ጠይቃ፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አወል ሱልጣን፣ ከግብር እና ያለንግድ ፈቃድ የሚሠሩ ተቋማትን በተመለከተ ምርመራ የሚያካሂድ፣ ክስ የሚመሠርት እና አጥፊዎች እንዲቀጡ የሚያደርግ ክፍል መኖሩን ጠቅሰው፣ ቅሬታና ማስረጃ ያላቸው አካላት ልደታ ለሚገኘው ይኸው ክፍል ቀርበው ማሳወቅ ይችላሉ ነው ያሉት። አክለውም፣ እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ከማኅበረሠቡ የቀረበ አቤቱታ፣ እንዲሁም በዐቃቤ ሕግ የተመሠረት ክስ ስለመኖሩ መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል። ከዚህ በኋላም በቀረቡ አቤቱታዎች ላይ ተመርኩዞ የሚመለከተው ክፍል በትምህርት ቤቱ ላይ ምርመራ ይጀምራል፤ የማይጀምር ከሆነም ምክንያቱን ግልጽ ያደርጋል ብለዋል።
ለአዲስ ማለዳ ሥሜ ባይጠቀስ ብለው አቤቱታቸውን ያቀረቡ አንድ የተማሪ ወላጅ እንደገለጹት፣ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ለሙያው ብቁ እንዳልሆኑ እና ችግሩ ሲነገራቸውም፣ “ጮኸህ ጮኸህ ዝም ትላለህ ምንም አታመጣም” የሚል ምላሸ እንደሚሠጡ ተናግረዋል።
እንዲሁም፣ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ከተማሪ መማሪያ ክፍሎች አጠገብ ‹‹ማፍያዎች›› ተሰባስበው እንደሚያድሩና ይህም በተለይ በሴት ልጆቻቸው ደኅንነት ላይ ሥጋት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል። ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ገቢ የሚሰበስብ ቢሆንም በመማሪያ ክፍል ዕጥረት አዳራሽ ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
አስተያየት የሠጡን ወላጅ አያይዘውም፣ የማኅበረሠብ ትምህርት ቤት የሚሆን ከሆነ እስካሁን ግብር ባለመክፈሉ ተጠያቂ ስለሚሆን፣ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት በማድረግ የሠራው ጥፋት ተዳፍኖ እንዲቀር ትምህርት ሚኒስቴር እየገፋፋና ኹኔታዎችን እያመቻቸ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ ያረፈበት ቦታም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የተሠራው ‹‹ግሪክ ኮሚኒቲ ድርጅት›› ተብሎ እንጂ በትምህርት ቤቱ ሥም እንዳልሆነ የሚገልጹት አስተያየት የሠጡን ወላጅ፣ በዚህ ሥም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደርና ግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን በ2004 የተሠጠውን ድብዳቤ አቅርበዋል።
ሌላኛው ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የተማሪ ወላጅ በበኩላቸው፣ ትምህርት ቤቱ የማስተማሪያ ዕቅድ የሌለው በመሆኑ የዓመቱን ትምህርት አሁን ላይ የጨረሱ መምህራን መኖራቸውን ተናግረዋል። ትምህርት ቤቱ ለማጭበርበር ያመቸው ዘንድ የተማሪዎችን ቁጥርም እንደማይዝና እንደማይታወቅ ነው ያመላከቱት።
አዲስ ማለዳም ይህን በሚመለከት ሙሉቀን ንጋቱን (ዶ/ር) የጠየቀች ሲሆን፣ ትምህርት ቤቱ የራሱ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት እንዳለውና በዚያ ሲመራ እንደኖረ ገልጸዋል።
የግሪክ ማኅበረሠብ ትምህርት ቤት የሠው ኃይል አስተዳደር ወሰን ውበት፣ ትምህርት ሚኒስቴር ለትምህርት ቤቱ ስላቀረባቸው ሦስት አማራጮች ያውቁ እንደሆን ተጠይቀው፣ ‹‹እኔ እስከማውቀው ድረስ ትዕዛዝ አልተሠጠውም›› የሚል ምላሽ ሠጥተዋል። አዲስ ማለዳ ስለጉዳዩ በጥልቀት ትምህርት ቤቱን ለማነጋገር ቀጠሮ ለማስያዝ ብትሞክርም ሳይሳካ ቀርቷል።
በከተማዋ በሚገኙ የማኅበረሠብና ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤቶች በርካታ ትውልድንና አገርን የሚጎዱ ሕጋዊ ያልሆኑ ሥራዎች እንደሚሠሩ በተደጋጋሚ ይነገራል። አዲስ ማለዳም ከዚህ በፊት የግሪክ ማኅበረሠብ ትምህርት ቤት ያለሕጋዊ ዕውቅና እንደሚሠራ፣ በዓመት እስከ 200 ሚሊዮን ብር እንደሚሰበስብ እና ተገቢውን ግብር ከፍሎ እንደማያውቅ ዘገባ መሥራቷ ይታወሳል።
ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014



