የአፍሪካ ኅብረት ስዋሂሊ የሥራ ቋንቋው እንዲሆን የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ማጽደቁ ተገልጿል።
ውሳኔዉ የፀደቀዉ የታንዛኒያ ምክትል ፕሬዝዳንት ፊሊፕ ምፓንጎ ለአፍሪካ ኅብረት ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ እንደሆነም ነው ለማወቅ የተቻለው።
ፕሬዝዳንቱ ሠሞኑን አዲስ አበባ ላይ ተካሄዶ በነበረው 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት ስበሰባ ላይ፣ ስዋሂሊ ቋንቋ በአፍሪካ ከ100 ሚሊየን በላይ ተናጋሪዎች እንዳሉት ማንሳታቸውም ነው የተብራራው።
ስለሆነም፣ በአፍሪካ አህጉር በሥፋት ከሚነገሩ ቋንቋዎች አንዱ በመሆኑ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ሐሳብ ማቅረባቸው ተመላክቷል።
ቀደም ብሎም የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች የአፍሪካ ኅብረት ስዋሂሊ የፓን አፍሪካ ቋንቋ እንዲሆን ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸዉ ተገልጿል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት መሠረት ቋንቋው መነሻው ምሥራቅ አፍሪካ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት በ14 የአፍሪካ አገራት ማለትም በታንዛኒያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሞዛምቢክ፣ ማላዊ፣ ዛምቢያ፣ ኮሞሮስ እና በመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ኦማን እና የመን ድረስ የሚነገር ቋንቋ ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014


