አሳምኚ!

0
637

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

እችላለሁ፤ ብርቱ የአገር ካስማ ነኝ፣ ፅናት አለኝ፤ አሸንፋለሁ…የሴቶች ጉዳይ ሲነሳ እንደመፈክር የምንሰማቸው ቃላትና ነጥቦች ናቸው። መፈክርም ብቻም አይደሉ፤ እውነት ናቸው። እውነት መሆናቸውን ግን በቃል ብቻ የምንናገረውና የምንለፍፈው መሆን የለበትም፤ በተግባር ዐሳይተን የምናስመሰክረው ሊሆን ነው የሚገባው።

ይህን እታዘባለሁ። በሥራ አጋጣሚ ለቃለመጠይቅ የተለያዩ ሰዎች ጋር እደውላለሁ። ብዙ ጊዜ ጉዳዩ ፖለቲካ ነክ ሲሆንና መናገር ካልፈለጉ ወይም ጉዳዩ ምስጢር ነው ካላሉ በቀር፤ አስተያየት ለመስጠት ስልኩን ያነሱት ወይም ቀጠሮ የተያዘላቸው ወንዶች ከሆኑ መልስ አያጡም። የተሰማቸውን ያሰቡትን ይናገራሉ። አላውቅም የለም፤ ያብራራሉ ይተነትናሉ።

በአንፃሩ ሴቶች ያንገራግራሉ። ቀላል የሚባል ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ማግኘት ከባድ ነው። ሌላ ቀን ይሁንልኝ፣ አስተያየት መስጠት አልወድም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የምለው የለኝም፣ የተወሰነ ቀን ስጡኝና አንብቤ ልመልስ ወዘተ የሚሉ መልሶችን ይሰጣሉ። እንግዲህ እነዚህ የተማሩ የሚባሉትና ከፍ ብለው በመምህርነት ጭምር የሚያገለግሉት ናቸው።

ጥንቃቄ ማድረግ፣ ብዙ ጊዜ አስቦ አንዴ መራመድ ትክክል ሊሆን ይችላል፤ ነውም። ግን ለመሸሽ ምክንያት መሆን የለበትም።

ይህን ስል ሁሉንም በአንድ ጨፍልቄ ለመፍረድ አይደለም። ግን እንደ እኔ ገጠመኝ ከሆነ ብዙ ጊዜ ወንድ እንግዶች ጋር መደወል ድካም ይቀንሳል። ምክንያቱም እነሱ ሐሳባቸውን በቀላሉና ቶሎ ይሰጣሉ። ሴቶችን ለማግኘት ግን ገና ከጅምሩ ሥራው ብዙ ነው። ተገኝተውም ደጅ ጥናት ሳይከተለው አይቀርም።

እህቴ! ትችያለሽ፣ አቅም አለሽ። ታድያ ለምን አታሳይንም። ለምን? ሐሳብሽን አትገልጪም? ለምን አታሳምኚያቸውም? ለምን አቅምሽን አታሳያቸውም? እየቻልሽ ዝም አትበይ፣ እያወቅሽ አትሸሸጊ፣ እጅሽን አውጥተሽ ተናገሪ፣ ሐሳብሽን ግለጪና አሳምኚ! በሥራሽ ውጤት አሳምኚ፣ በለውጥሽና በእድገትሽ ሰዎች ይማራሉ፤ ይጠቀማሉ።

አዎን ትችያለሽ፤ አድርገሽ ዐሳያቸው። ቅንጣት መረጃ አለን ብለው ታብየው እንደ አዋቂ የሚናገሩ እልፍ ሰዎች አሉ። አዋቂና ባለጥበብ ሆነው ነገር ግን ‘የማውቀው ቅንጣት ሆኖ ሳለ ምን እናገራለሁ!’ ብለው ዝም የሚሉቱ ደግሞ ከቀደሙት ይበልጣሉ።

መብትሽን የምታስከብሪው በዝምታም ሆነ በመፈክር አይደለም፤ በተግባር ዐሳይተሽ ስታሳምኚ ነው። ማሳመን ከቻልሽ ጠበቃሽ ብዙኀኑ ይሆናል። እችላለሁ እስክትይ አይጠይቅም፤ ቀድሞ እንደምትችይ ያውቃል። ነጋሪ ምስክር አያሻም። ብቻ ባመንሽበት ፀንተሽ ተራመጂ፣ አሳምኚ!


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here