መነሻ ገጽርዕስ አንቀፅመፍትሔን እንጂ አጀንዳን አታብዙ!

መፍትሔን እንጂ አጀንዳን አታብዙ!

ኢትዮጵያ አገራችን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ቁልቁል ወርዳ አዘቅት ውስጥ ከገባች ዓመታት ተቆጥረዋል። የሠላም ዕጦት፣ የኑሮ ውድነት፣ በሽታና ድርቅን የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች እያደር እየጨመሩባት የሕዝቧን ጭንቅና መከራ እያፈራረቁ ይገኛሉ። በአንዱ ላይ ሌላው እየተተካበት ማብቂያ ያለው ወደማይመስል ሥቃይና ዕንግልት እያደር እያመራ ያለው ሕብረተሠብ፣ ለማውራትና ብሶቱን ለመናገር እስኪያቅተው ድረስ ችግሮች ተደራርበው እንደወደቁበት አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች።

ኢትዮጵያውያንን በየጊዜው እያሸማቀቀ፣ እያንከራተተና አሰቃይቶ ለሞት እየዳረገ ያለው ተደጋጋሚ መከራ ከውጭ በመጡ ሳይሆን፣ በአብዛኛው በእኛው በራሳችን ወገኖች በቀጥታ የሚፈፀም ነው። ሕብረተሠቡ ራሱን ከውጭ ጠላት እንደሚከላከለው፣ ራሱን ከእኩዮች እንዲጠብቅና መከራውን አልፎ ወደተሻለ ኹኔታ እንዳያመራ መንግሥት ነው ብሎ ኃላፊነት የሠጠው አካል እንቅፋትና መሰናክል ሲሆንበት ደጋግሞ ይታያል። እንደራሱ ጥቅም ዐይቶ ካለው ላይ እየገበረለትና ለችግሬ ይደርስልኛል ብሎ ባመነው አካል ሙሉ በሙሉ መተማመኑ ለደረሰበት ግፍና ለሚገኝበት ጨለማ ዋናው ምክንያት ነው። ሕዝብ በመንግሥት ሲጠራ ሳያመነታ ሒዶ ሕይወቱን እንደሚሰጠው፣ በሀብቱ ያቋቋመው መንግሥት ግን “ድረስልን” ሲባል እንዳልሠማ መሆኑ፣ አሊያም የእናቴ መቀነት ጠለፈኝ ወይም እጄ አጠረኝ ማለቱ እየተለመደ ይገኛል።

ገና ከመነሻው ችግር ሲፈጠር በአፋጣኝ መፍትሔ ይዞ መምጣት የተሳነው መንግሥት፣ ኹኔታዎችን ሲያድበሰብስና ማስቀየሻ አጀንዳ በደጋፊዎቹና በራሱ ሲፈጥር ቆይቷል። የሕብረተሠቡን ዋና ዋና ችግሮች ያስረሳሉ በሚል በየቦታው የሚፈጠሩና ሆን ተብለው የሚለኮሱ እሳቶችን ማጥፋትም እየተሳነውና ሰደድ እየሆኑበት፣ ሌላውንም ኾነ እራሱን በእሳቱ እያስበላ ይገኛል። የፖለቲካው ኹኔታ ትኩሳት ሲፈጥርበት የኃይማኖቱን ካርድ በመምዘዝ ባለው እሳት ላይ ቤኒዚን እየጨመረ ቃጠሎውን እያባባሰው እዚህ ደርሷል።

አዲስ ማለዳ በአገርና በሕዝብ ላይ መዓትን የሚያስከትል ዳተኝነት አይደለም በመንግሥት አካል በማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ መፈፀም የሌለበት፣ አገር አፍራሽ ብቻ ሳይሆን አጥፊም መንገድ እንደሆነ ታምናለች። የሕዝብን ችግር ከሥር መሠረቱ ተረድቶ መፍትሔ መስጠት ያልቻለው መንግሥት፣ የሕዝብ ሰቆቃን እየሠማ መከራ እስኪደራረብበትና መፍትሔ ማግኘት ቢፈልግ እንኳን ወቅቱ አምልጦት አማራጭ መፈለግ እስኪያቅተው ጊዜ መውሰድ አልነበረበትም።

“አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ” እንደሚለው አገራዊ ብሂል፣ አግጦ የወጣና ሕዝብ ያስቆጣ አንድ ችግር በተከሠተ ቁጥር ከነመንስዔው ጎልጉሎ ችግሩን አውጥቶ ከመጣልና ተመልሶ እንዳይመጣ ከመሥራት ይልቅ መሸፋፈን ሲመረጥ ቆይቷል። እንደተዳፈነ እሳት ሲፈልጉ እየቆሰቆሱ፣ ሕዝቡ “የባሰም አለ” እንዲል፣ አንዱን ጉዳይ በሌላ አስከፊ ጉዳይ ለመሸፈን ሲሞከርም እስካሁን ድረስ ይታያል።

በመንግስት እንዝህላልነትና በሌሎች ጭካኔ ሕዝብ ለሞትና መፈናቀል ሲዳረግ፣ ችግር ፈጣሪውን ከማስወገድና ለነዋሪው ዋስትና ከመስጠት ይልቅ፣ “ሕዝቡ እንዲህ ስለሆነ፣ እንዲህም ስላደረገ ነው ይህ የሆነው” የሚል ተልካሻ ምክንያት እየሠጡ ለአጥፊ የልብ ልብ መስጠት ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ለውጥ የተባለው የአመራር ቅይይር ከተደረገ ወዲህ እንኳን፣ በአደባባይ ቦንብ ከተወረወረበት ክስተት ጀምሮ፣ ግልፅ በሆነ ሒደት ችግሮች መፍትሔ ሳይሰጣቸው እንዲረሱ እየተድበሰበሱና ለሕዝቡ ሌላ አጀንዳ እየተሠጠ መቆየታችን አይዘነጋም። ሕዝብ የአጭር ጊዜ የማስታወስ ብቃት ነው ያለው በሚል ብሒል፣ ከባድ ከባድ ክስተቶች ሲፈጠሩ ከሚዲያ መጥፋት፣ “የመንግሥት ያለህ” ሲባል ዝም ማለት ፋሽን እስኪመስል ሲደጋገም አይተናል። ለችግሮች “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብሎ ቆይቶ፣ በጎ ነገር አደረግን ለማለት ሲባል በአደባባይ ለመቅረብ ሲሞከርና መልሶ የሕዝብን ልቦና ለመግዛት አላስፈላጊ ወጪ ሲወጣም እየተመለከትን ነው። እንዲህ ዓይነት የሕብረተሠቡን ትዕግስት የሚያሟጥጡ እና ሕዝቡ ወደተስፋ መቁረጥና ሥርዓት አልበኝነት እንዲያመራ የሚያደርጉ ገፊ ምክንያቶችን መንግሥት አውቆትም ይሁን ሳያውቀው ተግባራዊ ማድረጉ፣ በራሱ አንገት ላይ ያለ ሸምቀቆን ሳያወልቅ የቆመበትን ወንበር እንደመገንበር ይቆጠራል።

ቅድሚያ መሠጠት ያለባቸውን የሕዝብ አንገብጋቢ ችግሮችን በመተው፣ ቅንጡ የሚባሉ የማብለጭለጭም ይባል የማስዋብ ሥራዎች ላይ ጊዜንና የድሃ አገር ሀብትን ያለሐሳብ ማዋል ተገቢ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ አጽንዖት ሰጥታ ትናገራለች። የሕዝብ ችግርንም ኾነ ሰቆቃን ትቶ፣ በወቅቱ ሊያሳፍሩ የሚገቡ ተግባራትን በአደባባይ እየወጡ መሥራት ብቻ ሳይሆን፣ ባለሥልጣናቱ ሌላውን ለማስተማር የሚሞክሩበት መንገድም ፈር የለቀቀ፣ የሚያስተዛዝብና የሚያቆራርጥ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

ሕዝብ በጅምላ የሚያልቅባቸው ጦርነትና ጭፍጨፋዎች ሲካሄዱ እንደማንኛውም ሕዝብ አብሮ እንደሚሠማ የሚናገረውና ለቅሶ አብሬ ካልተቀመጥኩ እያለ የሕብረተሰብን ሐዘንም ለመንጠቅ የሚሯሯጥ ባለሥልጣን አስቀድሞ ጥፋቱ እንዳይፈፀም ለመሥራት ሲጥር አይታይም። አልፎ አልፎ ከሕዝብ ልቦና አልወጣ ያሉ ከባድ የመንግሥት ጥፋቶችን ለማስረሳት፣ የቆየንም ሆነ የታወቀን ጭፍጨፋም ሆነ ግፍን አራብቶ በእገሌ ተፈጸመ ብሎ በማራገብ የሕዝብን ጥላቻ ለማዞር መርዶ ነጋሪ የሚሆንበት ጊዜም እየተደጋገመም ይታያል።

በሕዝብ ዘንድም ሆነ የማኅበረሠብ አንቂ በሚባሉ አካላት የሚፈፀሙና በዕውቀትም ይሁን ባለማስተዋል ለተሠራ በደል ሽፋን የሚሠጡም ሆነ ሳይጠየቁ የሚያስተባብሉም ተበራክተዋል። “ብቻውን ኾኖ ነው እንጂ…፣ ዙሪያውን የከበቡት ናቸው…፣ ውስጡ የተሰገሰጉትን መለየት ስላስቸገረው ነው፣ ታዲያ ምን ያድረግ፣ ሕዝብ አጣ እንጂ…” የሚሉና የመሳሰሉ ማዘናጊያ ቃላትን እየተጠቀሙ መንግሥት ወደለየለት አምባገነንነት እንዲያመራ፣ አሊያም ሕዝብ ተታሎ ወደአራጁ ጉያ እንዲገባ የሚያደርጉ መኖራቸው ይታወቃል።

መንግሥት ችግር እንዳይፈጠር አስቀድሞ በደኅንት ሰዎቹ ክትትል ከማስደረግ፣ ኹሉ መረጃ እንዲደርሰው ከመሥራትና የመከላከል ተግባር ላይ ከማተኮር ይልቅ እሳት የማጥፋት ድርጊት ላይ ነው በአብዛኛው የሚታየው። ለሥልጣኑም ሆነ ለስሙ የማያሠጋው ከሆነ ትኩረት የማይሰጠው ቢሆንም፣ እሳቱ ነዶ ነዶ የማያበቃና ማገዶ የሚሆነውን በቀላሉ የሚያገኝ ከመሰለው፣ እገሌ የጫረው ብሎ ጥላቻ በሚፈጥር መልኩ ወላፈኑን ለማጥፋት የሚሔድበትን ልምድ መቀየር እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች።

አገር በአንድ ግለሰብ ፍላጎት ልትመራ እንደማትችልም ሊታወቅ ይገባል። አማካሪ የሌለው መሪ ከዓመት በላይ አይዘልቅም እንደሚባለው፣ መሪ ነኝ ብሎ ኹሉም ውስጥ ገብቼ ካልወሰንኩ ማለት አምባገነን ከማስባሉ በላይ ሥራው ለትውልድ የማይዘልቅ ይሆናል። ለ5 ዓመት የተመረጠ መሪ መገበያያ ገንዘብ ላይ ምስሉን ከመለጠፍ የማይለይ አክሳሪ ድርጊት በተደጋጋሚ ሲፈጸም ይታያል።

ሕዝብ የሚታከምበት በጀት ዕጥረት ባለባት አገር፣ የሚበላውም ሆነ የሚጠለልበት ቤት ዕጥረት ናላውን የሚያዞረው ኢትዮጵያዊ በርካታ በሆነበት ኹኔታ፣ አገርን የዕዳ ቁልል ላይ እየሰቀሉ በአፍጢሟ ተምዘግዝጋ እንድትደፋ ከሚያደርጋት፣ ሕዝቧን ከድህነትና ጉስቁልና ከማይታደጋት ግንባታና ዕድሳት ላይ ትኩረት ማድረግ የጤና አይሆንም። ኹኔታውን “የራስዋ አሮባት የሠው ታማስላለች” እንዳንለው፣ እየሆነ ያለው ኹሉም እንዲያር የማድረግ ተግባር ነው። “መጀመሪያ የመቀመጫዬ እሾህ ይነቀልልኝ” እንዳለችው ዝንጀሮ እንኳን፣ ቅድሚያ የሚሰጠውን ነገር መገንዘብ ያልቻሉ ባለሥልጣናት፣ ሕዝባቸው የሚለብሰው አጥቶ ጎረቤት እንዳያየው ሊያከናንቡት እየከጀላቸው ይገኛሉ።

ለመቁጠር የሚያዳግት ሠው በየጊዜው አላግባብ እየተገደለ፣ በጅምላም እየተጨፈጨፈ ጉዳዩ የሕዝብ መወያያና መፍትሔ ማምጫ እንዳይሆን፣ በሕዝብ መሀል ሆነው ትኩረትን የሚያስቀይሱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እኩል ተጠያቂ መሆናቸው እንደማቀርም ኹሉም ሊገነዘበው ይገባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች