በኤሌክትሪክ እና በፀሐይ ብርሃን የሚሠሩ ተሸከርካሪዎችን በኢትዮጵያ ለመገጣጠም ዝግጅት እያደረግኩ ነው ሲል ‹ግሪን ቴክ አፍሪካ› አስታውቋል።
አማራጭ የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን በመጠቀም አገልግሎት የሚሠጡትን ተሸከርካሪዎቹን በአሁኑ ሰዓት ወደ አገር ቤት አስገብቶ ለገበያ ማቅረቡን የተናገረው ድርጅቱ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ሠፋ ያለ ተደራሽነትን ለመፍጠር እየሠራሁ ነው ማለቱ ተዘግቧል።
በፀሐይ ብርሃንና በኤሌክትሪክ ኃይል ይሠራሉ የተባሉት ተሸከርካሪዎቹ፣ ለሕብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ጭምር መሆናቸውን የተናገሩት የግሪን ቴከ አፍሪካ ሥራ አስኪያጅ ፍፁም ደሬሳ ናቸው። መኪኖቹ በተለይም በአገሪቱ ላይ ለሚታየው የነዳጅ ዕጥረት ሁነኛ መፍትሔ መሆናቸውን ተናግረዋልም ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ተሸከርካሪዎቹ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ለመጓዝ ከ50 ብር የዘለለ የኤሌክትሪክ ፍጆታን እንደማይጠቀሙ የተናገሩት ደግሞ የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን እና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ታደሰ መሆናቸው ተመላክቷል።
በመሆኑም፣የተሸከርካሪዎቹ ባለንብረት መሆን የሚፈልጉ ግለሰቦች ድርጅቱ ባመቻቸው የ40/60 መርሃ ግብር ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ዳይሬክተሮቹ አሳውቀዋል ነው የተባለው።
በሌላ በኩል ተሸከርካሪዎቹ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ኢትዮጵያውያንን ጭምር ታሳቢ ያደረገ ዋጋ እንደተተመነላቸውም መገለጹ ተዘግቧል።
ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014


