ኢትዮጵያ በውስጥም በውጭም የሚደርስባትን ጫና ለማርገብ ከተጠቀመችባቸው ዘዴዎች አንዱ በውጭ የሚኖሩ ኢትጵያውያን ወደ አገራችሁ ግቡና ሕዝባችሁን በኢኮኖሚ ደግፉ፣ የዓለም ማኅበረሠብም ስለኢትዮጵያ የያዘውን የተዛባ አመለካከት በመቀልበስ ዕውነታውን አሳዩ የሚል ነበር።
በዚህም፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀስቃሽነት አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲገቡ ጥሪ ተደርጎላቸው ስንት እንደመጡ እስካሁን ባይገለጽም በርካቶች መምጣታቸው አይካድም።
እንግዶቹ ከመምጣታቸው አስቀድሞም፣ በተለይ በአዲስ አባባ የሚገኙ አጥርና መንገዶች ስለኢትዮጵያውያን መምጣት የሚገልጹ ጽሑፎች ባሉባቸው ማስታወቂያዎች/ባነሮች ተጥለቅልቀው ታይተዋል። ይህ ምኞት መልካም ነው ሊባል ቢችልም፣ የመንግሥት በጀት አላግባብ እንዲበዘበዝ ትልቅ በር የከፈተ መሆኑን የሚያነሱ አሉ። ማስታወቂያ/ባነር መስቀያ ቦታ ጠፍቶ የግለሰቦች አጥር ላይ መስቀል እንደተጀመረም ትዝብታቸውን የሚናገሩ አሉ። ይህም በዳያስፖራ ሠበብ በይፋ የወጣ ይምሰል እንጂ በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባና በሌሎች ሰበቦችም መቀጠሉን የሚያስገነዝቡ አሉ።
እንዲሁም፣ ከዳያስፖራው መምጣት ጋር በተያያዘ በዋና ዋና መንገዶች፣ ጫማ በማፅዳት ሥራ ላይ የተሠማሩ ዜጎች፣ መጽሐፍ ሻጮችና የጉሊት ቸርቻሪዎች ከመንገድ ላይ እንዲነሱ መደረጋቸው አይዘነጋም።
በዚህም ተግባር፣ ጥሪውን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡትና ‹‹የኢትዮጵያን አሜሪካን ፒስ ኮንፈረንስ ካውንስል›› መሥራች ፍርዶት የሱፍ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በዳያስፖራው ሥም ዜጎች ከሥራቸው እንዲነሱ መደረጋቸው አሳዝኖናል ብለዋል። የከተማ አስተዳደሩም ጉዳዩን በተመለከተ ግልጽ ማብራሪያ አለመስጠቱ አግባብ እንዳልሆነ ነው ያነሱት።
አገራችን የምንወዳት ከነችግሯ እና ከነኹሉ ነገሯ ነው ያሉት ፍርዶት፣ የመጣነውም አገራችን ሠላም መሆኗን ለዓለም ማኅበረሰብ በማሳወቅ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የበኩላችንን ለማበርከት እና የምንችለውን ያህል በኢኮኖሚ ለማገዝ ነው ብለዋል።
በዚህም፣ ዳያስፖራ ሊመጣ ነው በሚል የዜጎችን ጉሮሮ መዝጋት መጥፎ ድርጊት መሆኑን ጠቅሰው፣ እንዲህ ዓይነት ሠዎች ከመንገዶች እንዲነሱ ከተደረገ እንኳን ሌላ ቦታ ሥራቸውን ለማስቀጠል በሚችል መልኩ ጥናት ተካሂዶ እና ግልጽ የሆነ አሠራር ተዘርግቶ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን አሜሪካን ዴቬሎፕመንት ካውንስል አባልና የኮሎራዶ “#በቃ” ዘመቻ ቡድን አባል ነኝ ያሉት ሒሩት በቀለም በበኩላቸው፣ በዳያስፖራ ሥም ዜጎችን ከሥራ ገበታቸው ማባረር ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
ከአራት ዓመት በኋላ ነው ወደ ኢትዮጵያ የተመለስኩት ያሉት ሒሩት፣ ደስ የሚል ለውጥ አለ ብለዋል። አያይዘውም በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ መልክ አቀባበል መደረጉም የመጀመሪያ ስለሆነ መልካም ነው ካሉ በኋላ፣ ቢስተካከል ያሉት ደግሞ አንድ ጉዳይ አለ።
ይህም ዳያስፖራው በአገሩ ‹ኢንቨስት› እንዲያደርግ የሚደረገው ጥሪ እና ሔደን ስናየው ያለው ጉዳይ በጣም የተራራቀ ነውና ቢስተካከል ብለዋል። ኢንቨስት ለማድረግ ወደሚመለከተው አካል ስንሔድ የምናገኘውና ለሕዝብ የሚወራው የሚገናኝ አይደለም ያሉት ሒሩት፣ በሚያሳፍር ሁኔታ በጣም ሙስና አለ፤ ለማስረጃም ወደ ኦሮሚያ ክልል ገና ሳንሄድ ስለሚያጋጥመን የምንሰማውን መጥቀስ ይቻላል ሲሉ ነው የተናገሩት።
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግም ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ካፒታል እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ የእኔ ፕሮጀክት ከሚጠይቀው በላይ ነው የሚጠይቁት ብለዋል። ከተማ አስተዳደሩም የያዘው ፖሊሲ 500 ሚሊዮን ብር እና 30 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ የሚል ስለሆነ፣ የተጋነነ ጥያቄ መሆኑን በመረዳት ማስተካከል ቢቻል መልካም ነው ሲሉ አመላክተዋል።
ለራሳቸው ፕሮጀክትም 50 ሚሊዮን ብር በቂ መሆኑንና የመደቡትም ይህንኑ ገንዘብ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ሆኖም ከተማ አስተዳደሩ በያዘው ፖሊሲ ምክንያት ኢንቨስት ማድረግ ተከልክያለሁ የሚል አስተያዬት አላቸው።
በከተማ አስተዳደሩ ለሥራ በሚሆን መሬት አሰጣጥ እና በኢንቨስትመንት ፖሊሲው ላይ ያለኝን ቅሬታም ለተወሰኑ ባለሥልጣናት አሳውቄያለሁ ሲሉ ተደምጠዋል።
ሒሩት አክለውም አዲስ አበባ ነው ተወልጀ ያደኩት፤ መሥራት የምፈልገውም እዚሁ አዲስ አበባ ነውና እንደ እኔ አዲስ አበባ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ አካላት መንግሥት ትብብር ቢያደርግና ቢሮክራሲውም እንዲቀንስ ቢሠራ ባይ ናቸው።
በቢሮክራሲው አሰልችነት የተነሳ ገንዘብ ይዘው መጥተው ትተው የሔዱ አውቃለሁ፣ ይህም ለአገራችን ክስረት ስለሆነ መፍትሔ ይሰጠው ሲሉም አሳስበዋል።
ኢንቨስትመንት ክፍት እንደሆነ ይወራል፤ ሆኖም ወደ ተግባር ስንገባ እንደተወራው ስለማይገኝ መንግሥት ያደረገልንን ጥሪ ተቀብለን ወደ አገራችን የመጣን ብዙዎቻችን ሥራ እና ቤተሰብ ጥለን የመጣንና ያለን ጊዜ አጭር መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በቂ የሰው ኃይል አስቀምጦና ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ዳያስፖራው አገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ወደ አገር ቤት በመምጣት ባደረጋቸው ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎዎች 22 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን የዳያስፖራ ኤጀንሲ ማስታወቁ አይዘነጋም።
የዳያስፖራው ወደ አገር ቤት መምጣት በተለይም በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ዘርፍ ስኬት የተገኘበት ነበር ተብሏል።
ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት መምጣቱ የእርስ በእርስ ትውውቅ እንዲኖረው እና የአገር አምባሳደርነቱ አጠናክሮ እንዲቀጥል ያገዘ ከመሆኑን እና ከገጽታ ግንባታ ባለፈም፣ እስካሁን ከቀጥተኛ ተቋማት በተሰበሰበ መረጃ ብቻ ከአየር ትኬት፣ ከአገልግሎት ዘርፎች እና ከቪዛ አገልግሎት 33 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር መገኘቱን ለማወቅ ተችሏል።
በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ለሰብዓዊ ድጋፍ 239 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ለግሰዋል ነው የተባለው።
ከኤጀንሲው በተሠጠ መግለጫም፣ 450 ያህል የዳያስፖራው አባላት የኢንቨስትመንት ጥያቄ አቅርበው ወደ እንቅስቃሴ ገብተዋል። የቢሮክራሲ ችግሩን ለመፍታትም ተቋማት የጋራ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ነው የተመላከተው።
በአጠቃላይም፣ ዲያስፖራው ለኢትዮጵያ ያለው አስተዋጾ ሲተመን እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል። በአገሪቱ ያልተመጣጠነ የወጪ ገቢ ንግድ ምክንያት የሚፈጠረው የውጪ ምንዛሪ Xeጥረት፣ ማስታገሻ የሚያገኘውም ዲያስፖራው ወደ አገሩ በሚልከው ገንዘብ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩትም በ2012 ብቻ ከአገራቸው ውጪ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ድጋፍ እና የተለያዩ ስራዎችን ለማሳለጥ በሚል ከላኩት የተገኘው ገንዘብ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር። ይህም አገሪቱ ላለባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ትልቅ አስተዋጾ መሆኑ አይካድም።
በዚህም በውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚላከው ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመምጣቱም በላይ በኢትዮጵያ ያላቸው የኢንቨስትመንት ተሳትፎም በየጊዜው እያደገ መሄዱ ነው የሚነገረው።
እስካሁንም በኢትዮጵያ ወደ 5100 የኢንቨስትመን ስራዎች በዲያስፖራው ተመዝግበው እንደሚንቀሳቀሱ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይሁን እንጅ አገሪቱ አሁንም ድረስ ለዲያስፖራ አንቨስተሮች ምቹ እንዳልሆነች ተደጋጋሚ ሀሳቦች ይሰነዘራሉ። አስተማማኝ ጸጥታ አለመኖር ዋናው ፈታኝ ጉዳይ ሲሆን፣ ያለው አሰልች ቢሮክራሲና ብልሹ አሰራር፣ የውጪ ምንዛሪ እጥረት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደልባቸው ኢንቨስት እንዳያደርጉ እና አገሪቱም ከኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዳትጠቀም እንቅፋት የሆኑ ነገሮች ናቸው።
መንግስትም ለዘርፉ የሚገባውን ያህል ትኩረት ባለመስጠቱ ለዲያስፖራው አገሪቱ ስላላት የኢንቨስትመንት አማራጮች በቂ መረጃ ያደርሳል ብሎ ለመናገር እንደማያስደፍር ይገለጻል።
ስለሆነም፣ በትኩረት ቢሰራበት ዲያስፖራውን የሚስቡ የኢንቨስትመንት አማራጮች በርካታ በመሆናቸው፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ብሎም የቴክኖሎጅ ዘርፍ ከማሳደግ ባለፈ፣ ከመንግስት ቀጥሎ የስራ አጥ ቁጥርን ለመቀንስ ትልቁ ቀጣሪ የዲያስፖራው ኢንቨስትመንት መሆኑ ይነሳል።
የአገሪቱ መንግስት ቀደም ብሎ እስረኞችን ለመፍታት ያደረገው ድንገተኛ ውሳኔ፣ እንዲሁም በየቀኑ የሚሞቱትን ንጹሀን ሰቆቃ ማስቆም አለመቻሉ፣ መቋጫ ባላገኘው ጦርነትና በሌሎችም ጉዳዮች የተነሳ በውጭ አገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ተስፋ እንዲቆርጡና ትብብርም እንዳያደርጉ የሚገፋፋ መሆኑን የሚያነሱም በርካቶች ናቸው።
በዚህም መንግስት ዲያስፖራውን ወደ አገር ቤት ከመጥራት በተሻለም፣ ለዲያስፖራው ፍላጎት አጋዥ እርምጃዎችን መውሰድ ያለበት ሲሆን፣ የአገሪቷን ሰላም ለማስጠብቅ የሚያደርገው ጥረት እንዲሁም በዜጎች ዘንድ ያለው ተቀባይነት እያደገ በሄደ ቁጥርም፣ በውጪ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ለአገሩ የሚያደርገው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ይታመናል።
አሁንም ቢሆን በውጭ አገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚደረገው ጥሪ ዓመቱን ሙሉ እንደሚዘልቅ እና ተጨማሪ ጠቃሚ ስራዎች እንደሚሰሩበትም በዳያስፖራ ኤጀንሲው በኩል ተጠቁሟል።
ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014



