የቅርስ ምዝበራ

0
769

የኢትዮጵያ ቅርሶች መመዝበር የጀመሩት ቅርስ ይጠበቅ ተብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ እንክብካቤ ሳይደረግ በፊት ነው። በግራኝ የወረራ ዘመን ተዘርፈው የኦቶማን ቱርኮች መቀመጫ ወደሆነችው የአሁኗ ቱርክ የሔዱት ቅርሶችና ሀብቶችን በዘረፉ አረቦች ጭምር ተፅፎ የሚገኝ ነው። በ16ተኛው ክፍለዘመን ‹የዓባይን ምንጭ› ፍለጋ መጣ የተባለው ጀምስ ብሩስ ካካሄደው ዘረፋም አንስቶ እስካሁን ምዝበራው ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም።

ከነዚያ ጊዜያት ቀደም ብሎ ቅርስ ስለመመዝበሩ በግልፅ የተቀመጠ ማስረጃ ባይኖርም፣ የሚጠብቀውና የሚቆጣጠረው ጠንካራ መንግሥትና ሕዝብ ከሌለ ዘረፋው እንደሚኖር መገመቱ አይከብድም። እንዲህ ዓይነት የሕዝብ ሀብቶች ይበልጥ የሚመዘበሩት የመንግሥት አቅም ደካማ ሲሆንና የእርስ በርስ አለመስማማትና ግጭት ሲበራከት እንደሆነ የታሪክ መጻሕፍትን እያገላበጡ ማመሳከር ይቻላል።

ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ እስካሁን የነበሩ መንግሥታት የቀደማቸው መንግሥት ያጠራቀመውንም ሆነ የተቀበለውን ሀብት ለተተኪው ሳያስተላልፉ እንደአዲስ ሕብረተሰቡን እያስገበሩ አገርን ለማስቀጠል ሲሞክሩ ቆይተዋል። በእንደዚህ ዓይነት የለውጥ ጊዜያት አዳዲሶቹ መንግሥታት አቅሙ ስለማይኖራቸው ቅርስንም ሆነ ሕዝባቸውን በተገቢው መጠን መጠበቅ ሳይችሉ ቀርተዋል። ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነውና እስካሁን የዘለቀው መንግሥታት በተቀየሩ ቁጥር ጠላቶቻችን ድንበር አልፈው መውረራቸውና ግዛት ማስፋፋታቸው ሲሆን፣ በዚህ ዓይነት ግርግር የእኛ መሬት መጥበብ ብቻ ሳይሆን በገንዘብ የማይተመኑ ቅርሶችም በእኛው ዜጎች ትብብር ይመዘበራሉ።

ስለቅርስ ምዝበራ ይህን ያህል ያልነው ሠሞኑን ከኢትዮጵያ ተሠርቀው በውጭ አገራት በግላጭ እየተሸጡ ስለሚገኙ ጥንታዊ የኢትዮጵያ መዛግብት ዓለም መነጋገሩን ተከትሎ ነው። ቅርሶቹ ከእኛ አገር ስለመውጣታቸው ማንም ባይጠራጠርም የወጡበት መንገድና የሚሸጡበት ሒደት መነጋገሪያ ሁኗል።

ጉዳዩን ያራገቡት የውጭ ዜጎችና ሚዲያዎች ከትግራይ ክልል የተዘረፉና ወደ ውጭ እንዲወጡ የተደረጉ ናቸው ቢሉም፣ ማነው ዘራፊና አዘራፊው በሚል የተለያዩ መላምቶችን ሠንዝረዋል። ጦርነት ሲደረግ የነበረው በትግራይ ብቻ እንዳልነበርና ውጊያው ከትግራይ ከወጣ መቆየቱን የሚያነሱ፣ እስካሁን ለምን ቆይተው አሁን አውጥተው ለመሸጥ ፈለጉ በማለት ከትግራይ በጦርነቱ ወቅት የወጡ ናቸው መባሉን ያስተባብላሉ። የትግራይ ታጣቂዎች አማራ ክልልን በወረሩበት ወቅት የተወሰዱ ናቸው የሚሉም ቢኖሩም፣ ከዚህ ደብር ይህ ይህ መዛግብትና ቅርስ በጉልበተኞች ተዘርፏል የሚል የትኛውም ክልል ያለ ደብር ስሞታ ሲያሰማ አለመሰማቱን ማስረጃ የሚያደርጉም አሉ።

ወቅቱን ተጠቅመው ቅርሶቹን ዘርፈው ወደ ውጭ በድብቅ እንዲወጣ ያደረጉ የውስጥ ሠዎች እንደሚሆኑ ግምታቸውን ያሰቀመጡም አሉ። ያም ሆነ ይህ፣ የጦር ማሣሪያና ሌላም ነገር እንዳይተላለፍ በጥብቅ ቁጥጥር ከሚደረግባቸው አካባቢዎች ያንን ያህል ቅርስ በቀላሉ ሊወጣ መቻሉ ብዙዎችን አነጋግሯል።

ከዚህ ቀደምም በርካታ ቁጥር ያላቸው የጥንት ጦር መሣሪያዎች በገፍ ወደ ውጭ ወጥተው በኢንተርኔት አደባባይ ሲሸጡ እንደነበሩ በማስረጃ ተደግፎ ይፋ ቢደረግም፣ ማን ፈቅዶ እየተሸጡ በአውሮፕላን እንደወጡ አጣርቶ ዕርምጃ የሚወስድ ባለመኖሩ፣ ይህኛው እንዲደገም ማድረጉን የሚናገሩ አሉ። ማን አወጣው እያሉ እየተነታረኩ ቅርሶቹ ተሸጠው ግለሰብ እጅ ገብተው እንዲበተኑና ጠፍተው እንዲቀሩ ከማድረግ አሁኑኑ ለማስመለስ መጣር፣ አሊያም ባለሀብቶች ገዝተዋቸው አገር ሠላም ሆና መመለስ እስኪቻል በአደራ እንዲያስቀምጧቸው ተጠይቋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here