በወለጋ በግፍ ስለሚጨፈጨፉ ዜጎች መንግሥት ለምን አይገደውም?

0
962

ሰይድ ሁሴን (ስሙ የተቀየረ) መንገድ ላይ ብቻውን እያወራ ይጓዛል። ሲያዩት ደህና ቢመስልም ቀርበው ሲያወሩት የሚናገረው እጅግ ልብ የሚሠብር ነው።

የሚኖረው አዲስ አበባ ሲሆን፣ በአንድ ትልቅ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ተቀጣሪም ነው። ሙሉ ቤተሰቦቹ የሚኖሩት ወለጋ በመሆኑም ለመጨረሻ ጊዜ ጥቅምት ወር ላይ ወደዚያው አቅንቶ ከቤተሰቦቹ ጋር ጥሩ ጊዜን ማሳለፉን እና ከሠፈር ጓደኞቹ ጋርም ውኃ ዋኝተው፣ በቆሎ ጠብሰው በልተውና ተጫውተው መመለሱን ያስታውሳል።

አሁን ላይ ያ ኹሉ ድርጊት ትዝታ ሆኗል። አብዛኛዎቹ ዘመዶቹ አልቀዋል። እህቱ ደግሞ ዘመዶቿ እና ጎረቤቶቿ ቤት ተዘግቶባቸው በእሳት ሲቃጠሉ ስላየች የአዕምሮ መታወክ አጋጥሟታል።

ሰይድ መንገድ ላይ ብቻውን እያወራ የሚጓዘውም በዚሁ ነው። የሚወዳት እህቱ የአዕምሮ መቃወስ ስላጋጠማት እሷን ለማዳን ኹሉንም መንገድ ሞክሮ ስላልዳነች አሁን የአዕምሮ ሕሙማን መታከሚያ እንዳስገባት ነው የሚናገረው።
ጥቅምት ወር ላይ ወደ ወለጋ በሔደበት ጊዜ አብረውት የዋኙና በቆሎ ጠብሰው የበሉት እነዚያ ጓደኞቹም ግማሾች በሕይወት የሉም፤ ሌሎቹም የዘመዶቹና የጎረቤቶቻቸው ገዳይ ሆነዋል።

ወለጋ ላይ የተፈጠረው ለማመን የሚከብድና የኢትዮጵያውያንን ማንነት የማይወክል እንደሆነ የሚገልጸው ሰይድ፣ የሞቱና ከሞት አምልጠው ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱ ዘመዶቹን ሀብትም ሌላው ማኅበረሠብ ሽሚያ እንደገጠመበት ይገልጻል። በርበሬውን፣ ማንጎውን እና ሌላ የደረሰውን እህል ለቅመው የወሰዱባቸው ሲሆን፣ ከብቶቻቸውን በሚከፋፈሉበት ወቅትም ለጸብ እንደተገባበዙ ሳይናገር አያልፍም።

ይህን ድርጊት ለማስቆምና ንጹኃንን በግፍ ከመገደል ለመታደግ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ይሁን የፌደራል መንግሥቱ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ቢኖራቸው ኖሮ የትኛውም ኃይል ከአቅማቸው በላይ እንዳልሆነም ሰይድ ይናገራል። እንዲህም ይላል ሰይድ፣ ከተጠቂዎች መካከል የተወሠኑት ራሳቸውን ለመከላከል ብለው ገዳዮቻቸው ላይ መተኮስ ከጀመሩ፣ የክልሉ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከየት መጡ ሳይባል በንጹኃን ላይ መዓት ያወርዳሉ።

በተለይ ሕወሓት አማራና ኦሮሞን ለመለያየት ያለውን አቅም አማጦ እየተጠቀመ እንደሆነ የማይደብቀው ሰይድ፣ ከተጠቂ ንጹኃን ውስጥ የተወሠኑት መሞታችን ካልቀረ እኛም ገድለን እንሙት ብለው በመተኮስ ገዳዮቻቸውን ከገደሉ በኋላመታ ወቂያቸውን ሲፈትሹ፣ የትግራይ ልዩ ኃይል የሚል መታወቂያ እንደሚያገኙ አረጋግጫለሁም ይላል። በተጨማሪም፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል የሚል መታወቂያ ይዘው ንጹኃንን የሚወጉ አካላት መኖራቸውንም ሳይጠቅስ አላለፈም።

በወለጋ በተለይም ማንነትን መሠረት አድርጎ የሚሠነዘረው ጥቃት ከዓመት በላይ አስቆጥሯል። መንግሥትም አንዳንዴ የጥቃቱን መኖር አላውቅም ሲል፣ ሌላ ጊዜም ገዳዮቹን ማረኩና ደመስሱኩ ሲል፣ በመሀል ንጹኃን የደረሰባቸውን በደል ለመናገር በሚከብድ ኹኔታ ይጨፈጨፋሉ።

ነገሩ እያደር መሻሻል ያመጣል ተብሎ ቢታሰብም፣ በእንዲህ ዓይነት አካባቢዎች የመንግሥት ኮቴ እየራቀ የታጣቂዎች ኃይል በመብዛቱ፣ በተለይ የአማራ ተወላጅ ኹነው በአካባቢው ካሉት ይልቅ የሞቱት እና አካባቢውን ለቀው የተሠደዱት እንደሚበልጥ ብዙ ማስረጃዎች ይቀርባሉ።

በዚህም በአዲስ አበባ በየዕምነት ተቋማት፣ በዘመድ ቤት፣ እንዲሁም መንገድ ላይ ልጆቻቸውን ይዘው የሚለምኑ በርካታ ሰዎችን ማየት በቂ ነው። ደብረ ብርሃን ከተማም ከ50 ሺሕ ያላነሱ ተፈናቃዮች ቤት ንብረታቸውን እና ከቤተሰቦቻቸው ውስጥ አብዛኛውን አጥተው በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሰው እጅ እየጠበቁ እንደሚኖሩ የሚታወቅ ነው።

ስደተኞቹም ዕርዳታ ይደረግልን ብለው ወደ መንግሥት አካል ሲሄዱም ጆሮ የሚሠጣቸው ካለመኖሩ በላይ፣ የሚደርስባቸው ወከባና እንግልት ቀላል እንዳልሆነ በየጊዜው ይናገራሉ።
ይህም ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝብ ያግዘን እንደሆን ስቃያችንን አሳውቁልን ብለው ወደ መገናኛ ብዙኃን ሲቀርቡም ማንም ጉዳይ እንደማይላቸው በሐዘን ይገልጻሉ።

ለአብነትም በርካታ ተፈናቃዮች ጋር ተሰባስበን ወደ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሔደን እውነታውን በሚገባ እንዲዘግቡ ብናናግራቸውም ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው እጅግ ያሳዘነኝ ነገር ነው ሲል ሰይድ ይደመጣል። የፌደራል መንግሥት የብዙኃን መገናኛዎችም እንዲሁ ከችግሩ ስፋት እና ጥልቀት አንጻር በሚገባ ዘገባ ሠርተዋል ብሎ ለመናገር እንደማይቻል የብዙዎች ቅሬታ ነው።

የአንድ አገር መንግሥት ዜጎቹን ከጥቃት ካልጠበቀና ሠላምን ካላሠፈነ ራሱም ወንጀለኛና የወንጀለኞች ተባባሪ ነው የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውም አሸባሪ የተባሉ አካላት ንጹኃንን ሲገድሉና ሲያፈናቅሉ፣ መንግሥትም እነዚህ አካላት በዜጎች ላይ የሚያደርሱትን ሰቆቃ ከማሳነስ ባሻገር፣ የማያዳግም ቆራጥ ዕርምጃ የማይወስድባቸው ከሆነ፣ በጋራ ሆነው ነው ንጹኃን ላይ ግፍና በደል የሚፈጽሙት ብሎ መናገር እንደሚቻል ብዙዎች ከሚሠነዝሩት ሐሳብ መረዳት ይቻላል።

በበርካታ የአገሪቱ ቦታዎችም ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ያድነናል ብለው የማያምኑ በርካታ የማኅበረሠብ ከፍሎች መኖራቸው ይነገራል። ይህም በመሆኑ ነገሩን ማድበስበስና ማለሳለስ አያስፈልግም። መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት የማያስጠብቅ ከሆነ ሕዝቡ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ከፍሎ ሠላምና ደኅንነቱን ማስጠበቅ አለበት ሲባል መስማትም እየተለመደ ነው።

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በመግለጫቸው በተለይም በወለጋ በመንግሥት ቸልተኝነት በንጹኃን ላይ እየደረሠ ያለውን ጥቃት አትተዋል።

ከእነዚህም ውስጥ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ‹‹በኦሮሚያ ክልል በተለይ በምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈፀመው ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ፣ ማፈናቀል እና ንብረት ማውደም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል። አሸባሪው የሸኔ ቡድን በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ ከሰሞኑ በፈፀማቸው ጭፍጨፋዎች በወረዳው በተለያዩ አካባቢዎች 81 ወገኖቻችን ተግድለዋል። እንዲሁም በጅምላ ተገድለው አስከሬናቸው አንድ ቦታ የተገኙ 87 ሰዎች በድምሩ168 ወገኖች መገደላቸው ተረጋግጧል። ወገኖቻችን አገራችን ብለው እየሠሩና ወልደው ከብደው በሚኖሩበት ቀዬ በተፈፀመ የዘር ተኮር ጥቃት ውድ ሕይወታቸውን በግፍ ተነጥቀዋል›› ሲል አካቷል።

ፓርቲው በግድያው የመንግሥት አመራር እጅ አለበት ብሎ የሚያምን ሲሆን፣ በዚህም ‹‹ወንጀሉ የሚፈፀመው በከፊሉ የመንግሥት አመራር ደንታ ቢስነት እና በከፊሉ ቀጥተኛ ተሳትፎ የመሆኑ ጉዳይ ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል። በአሁኑ ወቅት ሕዝባችን የሚያስፈልገው በሕይወት የመኖር መብቱን የሚያስከብርለት ዝቅተኛ መንግሥት (minimal state) እንጂ ነባራዊ ተጨባጭነት የሌለው መዋቅር እንዳልሆነ መገንዘብ ይገባል›› ነው ያለው።

ባልደራስ ለእውነተኛ ፓርቲም ጉዳዩን በመኮነን ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የንጹኃን አማሮች ደም በወለጋ፣ በቤኔሻንጉል ጉሙዝ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በአርሲ፣ በባሌ እና በሐረርጌ ያለማንም ተከላካይ እየፈሰሰ ይገኛል። ይህ ብሔርና ኃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ጭፍጨፋ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ፣ ከ180 በላይ ሰዎች በአንድ ጀምበር ተጨፍጭፈው 87 የሚደርሱ ንጹኃን ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸው በአንድ ሥፍራ ተገድለው ተገኝተዋል። ይህ በአማሮች ላይ እየደረሰ ያለውን ጭፍጨፋና ግድያ የፌደራል መንግሥቱ በተደጋጋሚ እንዲያስቆም ሲጠየቅ፣ የሽንገላ ምፀት መግለጫዎችን ከመስጠት በዘለለ፣ አሸባሪው ኦነግ/ሸኔንና በመንግሥት ውስጥ ያሉ ተባባሪዎቹን ተጠያቂ አድርጎ ግድያውን ለማስቆም የሚያስችል በቂ ዕርምጃ ሳይወስድ ቀርቷል›› በማለት ወቀሳውን አሠምቷል።

ፓርቲው ከወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን የተቀመጡ ዜጎችን በጎበኘበትም ወቅት፣ ተፈናቃዮቹ በቤተሰባቸው፣ በዘመዶቻቸውና፣ በንብረታቸው ላይ የደረሰውን ዘር ተኮር ጭፍጨፋና ጥቃት እንባቸውን ወደሰማይ እየረጩ አስረድተውኛል ሲል ገልጿል።
አክሎም፣ በጥቃቱ የኦሮሚያ መስተዳድር ባለሥልጣናት እጅ እንዳለበትም አስረግጠው ነግረውኛል ነው ያለው። እንዲሁም በአሁኑ ሰዓት ወደ 60ሺ የሚጠጉ የአማራ ተወላጆች በኦነግ/ ሸኔና ተባባሪዎቻቸው ተከበው የሞት ጥላ ተጋርዶባቸው እንደሚገኙ በመግለፅ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና የፌደራል መንግሥቱ ከሞት እንዲታደጋቸው የድረሱላቸው ጥሪ ማቅረባቸውን አስገንዝቧል።

በየቦታው በማንነቱ ምክንያት ብቻ የሚገደለውን የአማራ ሕዝብ ለመታደግ መጀመሪያ የክልሉ ሕዝብ መብቱን ከማያስከብሩለት አመራሮች መላቀቅ አለበት በማለት ቁጭታቸውን የሚገልጹ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይነገራል። በርካታ የክልሉ አመራር የፌደራል መንግሥቱን ላለማስከፋት በሚል፣ በፍርሀትም ተሸብቦ፣ በሾመው ሕዘብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ካለማስቆሙም በላይ ዕውቅና ሲሰጥ እንኳን አይታይም እየተባለ መታማቱ በተደጋጋሚ ይሠማል።

አሁንም ቢሆን በተለያዩ የወለጋ አካባቢዎች ማምለጥ እንኳን ባለመቻላቸውና የሚደርስላቸው አካል ባለመኖሩ ሞታቸውን የሚጠባበቁ በርካታ ዜጎች እንዳሉ ይነገራል። ለዚህም በቦታው በየቀኑ ስለሚገደሉ ሰዎች መስማት በቂ መሆኑ እንደማስረጃ ይቀርባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here