በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚታየው ግጭት እና አለመረጋጋት የሠብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሠሩ አድርጓል ሲል የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በሚስተዋለው ግጭት ምክንያት የዜጎች መብት እየተጣሰ እና አገሪቱ የሠብዓዊ መብት ቀውስ ውስጥ እየገባች መሆኑን ያነሱት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ያሬድ ኃይለማርያም፣ ለሠብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጥበቃ የሚያደርግ አካል ባለመኖሩ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰትና ቀውስ ለመመርመር መቸገራቸውን ጠቁመዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የፖለቲካ አውድ ሲበላሽ የሠብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጫና ውስጥ እንደሚገቡ ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ አገሪቱ በኮማንድ ፖስት ውስጥ በነበረችበት ወቅት በርካታ መገናኛ ብዙኃን እና ሠብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ለመንቀሳቀስ ተቸግረው እንደነበረ አንስተዋል። በዚሁ ጊዜ በርካታ ጋዜጠኞች ከሕግ ወጪ ለዕሥር መዳረጋቸውን ጠቁመው፣ እንደ ታምራት ነጋራ ያሉ ጋዜጠኞች ዛሬም በዕሥር ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
መንግሥት የሠብዓዊ መብት ተሟጋቾች ለሚያቀርቡት ጥያቄ የሚሠጠው ምላሽ በቂ አለመሆኑን ያነሱት ያሬድ፣ አንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች ተሟጋቾቹ የሚያነሱትን ጥያቄ እንደ መደፈር እና ፖለቲካዊ አድርገው እንደሚቆጥሩት ጠቁመዋል። በዚህም ለሚቀርብላቸው ጥያቄ በጎ ምላሽ እየሠጡ አለመሆኑን አመላክተዋል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት በሥራቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን ትችት ለመቀበል ልባቸው ሠፊ መሆን እንዳለበት ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ አንድ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ተቸኝ ብሎ የፍትሕ ሥርዓቱን የመበቀያ መንገድ ማድረግ አደገኛ አካሄድ መሆኑን አንስተዋል።
የሠብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በሚሠሯቸው ሥራዎች አማካኝነት ለችግር እየተጋለጡ መሆኑን ያነሱት ያሬድ፣ ማዕከሉ የሠብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ጋዜጠኞች በሚደርስባቸው ጫና ምክንያት ሥራቸው እንዳይዳከም የማገዝ እና ለተቋማቱ መብት መከበር አበክሮ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሠብዓዊ መብት አያያዝ ኹለት ገፅታ እንዳለው የሚያነሱት የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ መንግሥት ከዚህ ቀደም ለሲቪል ተቋማት አሳሪ የሆኑባቸውን ሕጎች በማሻሻል አንድ በጎ ዕርምጃ መራመድ ቢችልም፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታየውን ግጭት እና መፈናቀል ማስቆም ባለመቻሉ የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፤ አካል ጎድሏል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል። በዚህም አገሪቱ የሠብዓዊ መብት ቀውስ ውስጥ ገብታለች ብለዋል።
በመንግሥት በኩል በጎ ያልሆኑ ዕርምጃዎችን እየተመለከትን ነው ያሉት ከሚሽነሩ፣ በርካታ ሰዎች ከሕግ ወጪ ዕየታሠሩ እንደሚገኙና ፍርድ ቤት የዋስትና መብት የፈቀደላቸው ግለሰቦች ጭምር በዕሥር የሚቆዩበት ኹኔታ መኖሩን አመላክተዋል።
ኮሚሽኑ የሠብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ያነሱት ዳንኤል፣ የመብት ጥሰት ተፈፅሞ ሲገኝ መግለጫዎችን ከማውጣት ባሻገር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት ክትትል እናደርጋለን ብለዋል።
የሠብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጭምር እንግልት፣ ማስፈራሪያ እና ዕሥር እየፈጸሙ እንደሚገኙ ያነሱት ኮሚሽነሩ፣ ይህም አሳሳቢ እንደሆነ አንስተዋል።
አሁን ላይ በሲቪክ ተቋማት እና በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ የሚፈጸመው ዕሥር እና እንግልት ቀድሞ ከነበረው አስተዳደር አንፃር መሻሻሎች ቢያሳይም፣ በግለሰቦች ላይ የሚደርሰው እንግልት ሙሉ በሙሉ እንዳልተቀረፈ አንስተዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014


