የሙርሌ ጎሳ አባላት የጋምቤላ ሕፃናትን የሚሠርቁት ለሽያጭ ለማቅረብ ነው ተባለ

0
831

ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል ድንበር ጥሰው በመግባት ሕፃናትን አፍነው የሚወስዱት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ወንጀሉን የሚፈጽሙት በሱዳን ለሚገኙና ልጅ ለሚፈልጉ ግለሰቦች ለሽያጭ ለማቅረብ መሆኑን ክልሉ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሠሞኑን ወደ ጋምቤላ ክልል ድንበር ጥሰው በመግባት ሕፃናትን አፍነው የወሰዱት በባህላቸው መሠረት ትዳር ለመመስርት ብዙ ሀብት ሊኖራቸው እንደሚገባ ስለሚታመን፣ ሕፃናቱን በሀብት ለመለወጥ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽሕፈት ቤት ኡገቱ አዲንግ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ የገቡት የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎቹ የካቲት 2/2014 ቀን ሰባት እና አስር ሰዓት፣ እንዲሁም ሌሊት ዐሥር ሰዓት ላይ ወደ ጋምቤላ ክልል ድንበር ጥሰው በመግባት ሦስት ሕፃናትን አፍነው መውሰዳቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ ድንበር ጥሰው ወደ ጋምቤላ ክልል በገቡት ታጣቂዎች ታፍነው የተወሠዱት ሦስቱ ሕፃናት፣ በዲማ ወረዳ በስደተኞች የመጠለያ ካምፕ ይኖሩ እንደነበርም ተናግረዋል። ሕፃናቱ ታፍነው በመወሰዳቸው ከተፈጠረው ችግር በተጨማሪ፣ ታጣቂዎቹ በዲማ ወረዳ በነበሩ ኹለት ንጹኃን ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ማድረሳቸውንም ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ ሕፃናቱን አፍነው የሚወስዱት ለምን ዓላማ ነው ስትል አዲስ ማለዳ ላቀረበችው ጥያቄ ኃላፊው ሲመልሱ፣ “ታጣቂዎቹ ሕፃናቱን የሚወስዱት ለገበያ ለማቅረብ ነው” ብለዋል። “በሙርሌ ባህል የስርቆት ልምድ የሌለውና በሌብነት ያልሠራ ወጣት ጎረመሰ ተብሎ አይቆጠርም። ጎረመሰ ተብሎ የሚቆጠረው ሰው ሲገድልና ንብረት ሲዘርፍ ነው” ያሉት ኃላፊው፣ “ከብት ከዘረፉ ሚስት ለማግባትና ትዳር ለመምራት ብቃት እንዳላቸው ማረጋገጫ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

ኡገቱ አክለውም፣ ልጅ የሌላቸውና የሚፈልጉ በሱዳን አካባቢ ያሉ ባለሀብቶች “ሀብታቸውን በልጅ ስለሚቀይሯቸው አንድ ሕፃንን በመውሰድ ብዙ ከብት ማግኘት እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ ነው” ሕፃናቱን የሚወስዱት ሲሉ ገልጸዋል። ኃላፊው አያይዘውም፣ ታጣቂዎቹ ሕፃናቱን የሚወስዱት ብዙ ከብት መንዳት ለስርቆት የማይመች በመሆኑና ከዚህ ይልቅ አንድ ሕፃን ሰርቆ በቀላሉ ብዙ ገንዘብ ማግኘትን እንደ ቀላል አጋጣሚ ስለሚጠቀሙበት ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶችን ፈጽመዋል የሚሉት ኡገቱ፣ ለስርቆቱ ከላይ ከተዘረዘረው ምክንያት በተጨማሪ አግተው የሚወስዷቸውን ሕፃናት እንደ መያዣ በማድረግ ከቤተሰቦቻቸው ብዙ ሀብት ለመቀበል ስለሚያስቡ ነውም ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ከኃላፊው ያገኘቸው መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ፣ ታግተው ከተወሰዱት ሦስት ሕፃናት በተጨማሪ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የሞት አደጋ መድረሱን ነው። እስከሁን ማንነታቸው ያልታወቁ ሠዎች ሠሞኑን ከጋምቤላ ከተማ በመነሳት መዳረሻውን ወደ ኑዌር ዞን አድርጎ ሲጓዝ በነበረ የጭነት መኪና ላይ ጥቃት በመሠንዘራቸው ሹፌርና ረዳቱ ሕይወታቸው አልፏል።

በአገሪቱ ሕገ-መንግሠት ሠው መስረቅና መግደል ሕግን ከመተላላፍ በዘለለ ኢ-ሠብዓዊ ድርጊት ነው የሚሉት ኃላፊው፣ የክልሉ ልዩ ኃይል ታጣቂዎቹ የገቡበትን ቦታ የመከታተል ተግባር እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ በሒደት የሚያገኙትን መረጃም ለሕዝቡ እንደሚያሳውቁ አመላክተዋል።

ታጣቂዎቹ ጉዟቸው በጫካ በመሆኑ ጫካውን ከጣሱ በኋላ ነው ሾልከው በመግባት ጥቃቱን የሚያደርሱት የሚሉት ኃላፊው፣ ከዚህ ውጭ እስካሁን የተገኘ ተጨባጭ መረጃ ስለሌለ መርቶ ያስገባቸው አካል መኖሩና አለመኖሩን ገና ማወቅ እንዳልተቻለም አብራርተዋል።
የክልሉ መንግሥት የመደባቸው የጸጥታ ኃይሎች ጥቃቱን እየመከቱና በተከሠተው ችግር ላይ ዕርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ይህን ጥቃት ከማድረሳቸው በፊት በቅርቡ በኑዌር እና አኙዋ ዞኖች በመግባት ለ11 ሰዎች ሞት ምክንያት እንደሆኑና አራት ሕፃናትን አፍነው እንደወሰዱ፣ እንዲሁም ከብቶችን እንደዘረፉ የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት መግለጹ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here