ማክሰኞ የካቲት 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና ካቢኔያቸው ዛሬ የካቲት 8 ቀን 2014 በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ የቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ህዝብ ግንኙነት ገልጿል።
ቋሚ ሲኖዶሰሰ የካቲት 4 ቀን 2014 በመስቀል አደባባይ፣ በወይብላ ማርያም ጉዳይ፣ በጃንሜዳ ባህረ ጥምቀት እና በሌሎች የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች ዙሪያ ተወያይቶ አሉ የሚባሉ ችግሮችን በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ለመፍታት ይዞት የነበረው ቀጠሮ በወቅቱ የከተማ አስተዳደሩ ም/ቤት ሥብሰባ ስለነበረውና ከንቲባዋም በዚያ መገኘታቸው የግድ ስለሆነ ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር የነበረው ቀጠሮ ለዛሬ እንዲተላለፍ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና ከአስተዳደሩ የተወከሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በአካል ተገኝተው ለቋሚ ሲኖዶስ በገለጹት መሰረት የውይይቱ ጊዜ ለዛሬ እንዲተላለፍ መደረጉ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት ከንቲባዋና የካቢኔ አባላቶቻቸው ዛሬ በሰዓቱ በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ የተገኙ ሲሆን ከቋሚ ሲኖዶስ አባላት በተጨማሪ ሌሎች ብፁአን ከባቶች ፣ የህግ ባለሙያዎች ፣ ከመምሪያ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ያደርጋሉ።
በውይይቱ አሉ የሚባሉና ቤተክርስቲያን የምታቀርባቸው ጥያቄዎች ሁሉ ፍጹም ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ የሚያገኝበትን ሁኔታ ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚገመት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገልፃለች።
ከዚህ ቀደም በቋሚ ሲኖዶስ አባላትና በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ መካከል ሊደረግ የታሰበው ውይይት በተለያዩ ምክንያቶች እንቅፋት እየገጠመው መቆየቱ ይታወሳል።
——————————
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n









