ፍርድ ቤቱ ጄኔራል ታደሰ ወረደ እና ሌ/ጄ ጻድቃን ገ/ተንሳኤን ጨምሮ በ74 ተከሳሾች ላይ የተመሰረተውን ክስ ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

0
1149

ዕረቡ የካቲት 9 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ-ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት፣ ጄኔራል ታደሰ ወረደ እና ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤን ጨምሮ በ74 ተከሳሾች ላይ የተመሰረተውን የዐቃቢ ሕግ ክስ ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ፡፡

በእነ ጄኔራል ታደሰ ወረደ የክስ መዝገብ የተከሰሱት የህውሃት ወታደራዊ ቡድን አመራርና አባላት ናቸው የተባሉ አጠቃላይ 74 ተከሳሾች ሲሆኑ፣ ከነዚህ ውስጥ 20 ተከሳሾች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።

ተከሳሾቹ ከህውሃት ቡድን ተልዕኮን ተቀብለው ወታደራዊ ቡድን በማደራጀት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ በፌደራል ፖሊስ እንዲሁም በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ ጥቃት ማድረስ ወንጀል በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ክስ አንደተመሰረተባቸው ይታወቃል ።

ትናንት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ-ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የቀረቡት ኮ/ል ገ/መስቀል ገ/ኪዳን እና ኮ/ል ዶ/ር አለምብርሃንን ጨምሮ 19 ተከሳሾች ሲሆኑ፣ አንድ ተከሳሽ በህመም ምክንያት ከማረሚያ ቤት አለመቅረቡ ተገልጧል።

ፍርድ ቤቱ በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ ከ1ኛ እሰከ 47ኛ ፣ 49ኛ፣ 50ኛ እና ከ52ኛ እስከ 56ኛ ያሉ በአጠቃላይ 54 ተከሳሾችን ፖሊስ ከመከላከያ ጋር በመተባበር እንዲያቀርባቸው በተሰጠው ተደጋጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮ አለመቅረባቸውን ተከትሎ ፖሊስ ያላቀረበበትን ምክንያት እንዲያስረዳ ታዞ ነበር።

ይህን ትዕዛዝ ተከትሎ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተከሳሾቹ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንደነበሩ በመጥቀስ የትግራይ ልዩ ሀይል አባል በመሆን በጦርነቱ በመሳተፍ እና በመምራት ላይ የነበሩ መሆናቸውን ማብራራቱ ይታወሳል።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሾቹ የተከሰሱበት የወንጀል ህግ ድንጋጌ ከ12 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ መሆኑን አብራርቶ፣ በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ተደርጎ የማይቀርቡ ከሆነ ያልቀረቡ ተከሳሾች ጉዳይ በሌሉበት እንዲቀጥል እንዲታዘዝ ፍርድ ቤቱን በመጠየቁ፤ ፍርድ ቤቱ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ህጉ መሰረት ያልተያዙ 54 ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል። የኢትዮጲያ ፕሬስ ድርጅትን የጋዜጣ ጥሪ ውጤት ለመጠባበቅም ለትናንት የካቲት 8 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በትላንቱ የካቲት 08/2014 በያዘው ቀጠሮ በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ 54 ተከሳሾች በጥር 16 /2014 በታተመው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገፅ 21 ላይ የጋዜጣ ጥሪ የተደረገላቸው መሆኑን ማረጋገጡን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በቁጥጥር ሥር ያልዋሉት 54ቱ ተከሳሾች በችሎት ባለመቅረባቸው መዝገቡ በሌሉበት እንዲታይ በመወሰን የዐቃቤ ሕግን ክስ ለመስማት ለየካቲት 22 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here