የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ(ኦፌኮ) ፓርቲ ሊቀመንበር
መረራ ጉዲና(ፕሮፌሰር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለረዥም ዓመታት የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህር ሲሆኑ፣ ከወጣትነታቸው ጀምሮ በፖለቲካው ውስጥ በንቃት መሳተፍ ከጀመሩ አንስቶ በርካታ ዓመታትን የመንግስት ተቃዋሚ ሆነው አሳልፈዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ፓርቲን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች እና ከኦፌኮ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ መረራ ከአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
አዲስ ማለዳ፡- በኢትዮጵያ አሁን ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት እና ጦርነት እንዴት ይረዱታል?
ፕሮፌሰር መረራ፡- ዞሮ ዞሮ አጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ከንጉሱ መጨረሻ ዓመታት ጀምሮ ተመሳሳይ ነው፤ ብዙ የተለወጠ ነገር የለውም። ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ ሲሸጋገር ነው የኖረው። አሁንም ቢሆን ከዛ ቀውስ ወደ ባሰ ቀውስ እየገባን እንጂ ነገሮች ሊለወጡ አልቻሉም። እኛም እንግዲህ ቁጭ ብሎ ኹሉም ጉዳዩ የሚያገባቸውን ኃይሎች ችግሮችን ለመፍታት በሚቻልበት ኹኔታ ሳይሆን ያው ዞሮ ዞሮ የሥልጣን ጉጉትም ይሁን ብቻ ከዛ የበለጡ ችግሮች አሁንም እያስቸገሩን ነው። ስለዚህ ከዛ ቁርጠኝነት መውጣት ስላልተቻለ ቀውሱ ከእኛ ጋር እየኖረ ነው።
በኢትዮጵያ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ጊዜያዊ መንግሥት ወይም የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት እና ኹሉንም አካላት ያካተተ ውይይት እንዲደረግ ኦፌኮ እንደመፍትሔ አቅርቧል። የሽግግር መንግሥት ኢትዮጵያን ያፈርሳታል የሚሉ ሐሳቦች ይነሳሉ ከዚህ አንጻር እንዴት ያዩታል?
ዞሮ ዞሮ ሕወሓት ብቻውን የኢትዮጵያ ችግር አይደለም፤ የኢትዮጵያ ችግር ከሕወሓት ይሠፋል። ሕወሓት የፈጠራቸው ችግሮች ትላንትም ዛሬም ሊኖሩ ይችላሉ። ዋናው ጉዳይ ግን ሕወሓትንም የሚከሱ ወገኖች የተሻለ ሥራ መሥራት ስላቃታቸው ቀውስ ውስጥ እየዳከርን ነው። ስለዚህ ዞሮ ዞሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ደጋግሜ እኔ እንደምናገረው “ቡዳው ማን ነው“ የሚለውን በሥነ ሥርዓት ካልለየን በስተቀር አንዱ ሌላውን እየከሰሰ መኖሩ ብዙ ለውጥ አያመጣም።
ከቻልን “ቡዳው” ማን ነው የሚለውን ለይቶ ማውጣት ነው። ካልቻልን ደግሞ ሌላው ቢቀር ሁላችንም ቡዳ ልንሆን እንችላለን ብለን ቁጭ ብሎ መሠረታዊ በሆኑ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ በመቀበል ድርድር መፈጠር መቻል አለበት። እስከ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላለፉት 50 ዓመታት ከንጉሱ መጨረሻ ዓመት ጀምሮ ከመገዳደል ፖለቲካ ወደ መደራደር ፖለቲካ መለወጥ አልቻለም።
ንጉሡም ያንን ሳይችሉ ቀርተው ኤርትራን ጥያቄ በተለይ እና በተወሰነ ደረጃ የትግራይና የኦሮሞን ጥያቄ ትተው ነው የሔዱት። ደርግ ደግሞ የበለጠ አበላሽቶ ኤርትራን ያለደረሰኝ አስረክቦ ነው የሄደው። ሕወሓትም ብዙ የተሻሉ ሥራዎችን መሥራት አቅቶት በቀውስ ውስጥ ለ27 ዓመታት ስንዳክር ኖርን። የሕወሓትን አመራር የተካውም ብልጽግና የተሻለ ነገር ይዞ ይመጣል ብለን ብዙ ጠብቀን ነበር። ማሰሪያ የሌለው ውይይቶች፣ ጉንጭ አልፋ ክርክሮችና ውይይቶች እንጂ የተጨበጠ የታሰረ፣ አገሪቷን ወደፊት ሊያራምድ የሚችል በተለይም የጋራ ፍኖተ ካርታ የአንድ ቡድን ፍኖተ ካርታ ሳይሆን፣ የጋራ ፍኖተ ካርታ መሬት ላይ ማስቀመጥ አልተቻለም። ስለዚህ ያው ሁልጊዜ እንደሚደረገው ቤተ መንግሥት የያዘ እዛ ለመቆየት የሚያደርገው ጥረት እና ሕልም፣ ከዛ ውጪ ያለው ደግሞ ያንን ለማስለቀቅ በሚያደርገው ትችት እና ግጭት ውስጥ ገብተን ብዙ መሔድ አልተቻለም።
ስለዚህ፣ እነዚህን ነገሮች ቁጭ ብሎ ማሰቡ ነው፤ “ቡዳው“ ካልታየ በስተቀር ቢያንስ ቢያንስ ኹላችንም እንግዲያውስ “ቡዳ“ መሆን እንችላለን ብለን መነጋገር ውስጥ ካልገባን ያስቸግራል።
እርስዎ ብዙ ጊዜ ከመገዳድል ፖለቲካ መደራደር ይሻላል ይላሉ። ኢትዮጵያ አሁን ለገጠማት ችግር መነሻ ነው የሚባለው ሕወሓት ጋር መደራደር እና ሕወሓትን ወደ ሥልጣን መመለስ አገሪቱን ወደ ኋላ ይመልሳታል የሚሉ ሐሳቦች ይሰማሉ፤ ምን ይላሉ?
ሕወሓት እኮ የያዘው አንድ አካባቢ ነው። ምን አልባት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ስድስት በመቶ ሰባት በመቶ አካባቢ ነው የያዘው። ኦሮሚያ ውስጥ ምን እየተደረገ ነው፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ ሱማሊያ፣ አማራም አካባቢ ቢሆን ምን እየተደረገ ነው? ቅድም እኮ ብያለሁ የ“ቡዳ“ ጉዳይ ሕወሓትን እኮ አንዱ ትልቁ ችግር ብለን ለ27 ታግለናል፤ ይሄ አዲስ ነገር አይደለም።
ዋና ጉዳይ እኔ በተለይም የዚህ የአሁኑ ዙር ጦርነት መፍትሔው፤ ይሄ ለውጥ የምንለው፣ ሽግግር የምንለው (Transition) ያልተሳካ በመሆኑ ነው። ዋናው ጉዳይ አሁን ያ ሽግግር (Transition) የምንለው ከሕወሓት ውጪ ተሳክቷል ወይ ነው? ለምሳሌ፣ ኦሮሚያ አካባቢ ብትመለከት ብዙ ከኤርትራ የመጡ ሠላማዊ ትግል ውስጥ እንሳተፋለን ያሉ የኦነግ መሪዎች እስር ቤት ናቸው። ዋና ሊቀመንበሩን ጨምሮ ማለት ነው። አንዳንዴ የሚያስቀው ደግሞ ፍርድ ቤት ኹለት፣ ሦስት አራት ጊዜ ሁሉ የፈታው አመራር አሁንም ፖሊስ አለቅም ብሎ ከአንድ ፍርድ ቤት ወይንም ጣቢያ ወደ ሌላ ይወስዳል።
የሕግ የበላይነት እየተባለ መንግሥት ሕግን ካላከበረ ፍርድ ቤት የሚወስናቸውን ውሳኔዎች ካላከበረ ያስቸግራል። ስለዚህ “ቡዳ“ ሕወሓት ብቻ አይደለም። እንግዲህ ኹሉም አስተዋጽዖ ለማድረግ እኔ ቅድም እንዳልኩት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከታሪክ ጣጣዎቻችን የመጡ ችግሮች አሉ። ለ27 ዓመታት ሕወሓት የፈጣራቸው ችግሮች አሉ። ያለፉት አራት ዓመታት ደግሞ ብልጽግና ሆኖ የወጣው ኃይል የፈጠራቸው ችግሮች አሉ። በዚህ ኹሉ ሌሎችም የፖለቲካ ኃይሎች እንደየቁመታቸው የፈጠሯቸውን ችግሮች ቁጭ ብሎ መለየትና መነጋገር፣ ሐቀኛ ገለልተኛ አካልም አስቀምጠንም ለመፍታት መጣር ነው። ለዘላለም ሕወሓትን ብቻ ብትከስ የምታመጣው ብዙ ነገር የለውም። ከሕወሓት ጋርም እንተዋወቃለን፤ አሁን ያለውም ገዢው ፓርቲም ከሕወሓት ጋር ይተዋወቃል። ኹላችንም እናውቃለን ማለት ነው። ስለዚህ ሕወሓት ስልጣን ላይ ይመጣል የሚለው ብዙ የሚያስኬድ አይደለም። ከሕወሓት ውጪ ያሉም ችግሮቻችን እየሰፉ፣ እየገዘፉ በጥልቀትም እየተበላሹ ሔዱ እንጂ እየፈታናቸው አይደለንም ማለት ነው። ስለዚህ አንድ ቡድንን ብቻ ዘላለም መውቀሱ ትክክል አይደለም። ለምሳሌ ወደ ንጉሱ ብንሄድ በአገር አንድነት ጥያቄ ምንም ቅርቃር የሌለባቸውን ሰዎችን ገደለ፤ እነ ጅራ ተፈሪን በአገር ክህደት ገደለ፤ ደርግ እነ ሐይሌ ፊዳንም፣ ብርሀነ መስቀል ረዳንም ገደለ። ገዥው ፓርቲ ሌሎችን የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገር አንድነት ብቻ እየከሰሰ መኖሩ ተለመደ።
ሕወሓትም ለምሳሌ እነ ኦነግን፣ ኦብነግን ሲከስ ነው የኖረው። ስለዚህ የመካሰስ ፖለቲካ አላዋጣም። መፍትሔው የጋራ ነው። የአንድ ቡድን መንግሥት ከሠማያት የለም እኮ! ፖለቲካ ውስጥ ያ መንግሥት በሕዝብ ይሁንታና ቅቡልነት ካልሆነ በስተቀር ከሠማያት አይመጣም። እኔ ግጭት ላይ እየሠራሁ ነው፣ ወርቅ ላነጥፍ ነው፣ የሚባለውን ነገር ሌላውም ወገን ማመን መቀበል አለበት።
እስካልተቀበለ ድረስ የትም አይደርስም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሕወሓትን ብቻ በመክሰስ የምንወጣው አይደለም። ሕወሓትን ተገቢ ክሶችን ስንከስ ነበር፤ የኛ ሆነ ሌሎች ድርጅቶችም ጭምር ውድ ዋጋ ከፍለናል፤ ተንገላተናል።
አሁን ላይ ለውጡን ያመጡ አካላት ጭምር ተመልሰው እየታሠሩ ነው። ለምሳሌ፣ የኦሮሞ ቄሮዎች የሚባሉት ለውጡን በደማቸው ነው ያመጡት፤ ከ ሰባት ሺሕ ያላነሱ የኦሮሞ ወጣቶች ተገለዋል። ጩልሌዎች ግን ወደ አራት ኪሎ ጠጋ ብለው ሥልጣን ይዘው ብዙ ነገር እየሠሩ ነው።
ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ከሚፈለገው በላይ ይዘውት ገደል እንዳይገቡ ሥጋት አለኝ። በተፈለገው ብቻ አይደለም፣ መሬት ላይ ያለው ፖለቲካ ካልተለወጠ በስተቀር ዝም ብሎ የሚለወጡ ብዙ ነገሮች የሉም።
እዛ ላይ ማተኮሩ ይሻላል። ሕወሓት ተገቢ ነው የሚለውን ጥያቄ ያነሳል፤ ለፈጠራቸው ችግሮችም ችግሩን ይሸከማል፤ 90 በመቶ በላይ የሆነው የኢትዮጵያ አከባቢ አሁን በቀውስ እየተቃወሰ ያለው እኮ በሕወሓት ብቻ አይደለም።
ይልቁንስ ፖለቲካችንን ለማስተካከል ከቻልን ችግሩን መለየት፣ ካልቻልን ደግሞ የራሳችንን አስተዋፅኦ ለማድረግ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ከሁሉም በላይ የጋራ ፍኖተ ካርታ አስቀምጠን፣ በጋራ ደግሞ ያን ፍኖተ ካርታ ላይ መሥራት አለብን። ይህንን ካላደረግን በስተቀር ጠመንጃ ያዥ መሆን አይጠቅምም።
እንደምንሰማው ብዙ ወጣቶች ወደ ጫካ መግባታቸውን የሚጠቁም ማስረጃዎች አሉ። ለምሳሌ፣ በኦሮሚያ ክልል የምክር ቤት አባል የነበሩ፣ የፓርላማ አባላት የነበሩ፣ በኛ ፖለቲካ ተስፋ ቆርጠው ጫካ እንደገቡ እናውቃለን፤ የአደባባይ ምስጢር ነው።
ዋናው ጉዳይ ተስፋ የሚሰጥ ፖለቲካ ሕዝቡ የኔ ነው የሚለው መንግሥትና ሁላችንም ደግሞ ችግራችን ለመፍታት የጋራ የሆነ ፍኖተ ካርታ ፈጥሮ አስተዋፅኦና መዋጮ ይዞ ወደ መፍትሔው ካልመጣን እኔ ብቻ መንግሥተ ሰማያት አደርሳለሁ የሚለውን ማንም ሊመኝ ይችላል፤ ሊያምን ይችላል። እኔ በዚያ ችግር የለብኝም። ግን ሌሎችም ኃይሎች እንዲቀበሉት፣ ሌሎችም ኃይሎች ጠመንጃ አስቀምጠው ወደ ድርድር እንዲመጡ መምከሩ ይሻላል።
በኦሮሚያ ክልል የዜጎች ሞትና መፈናቀል ተባብሶ ቀጥሏል። ለዚህ ተጠያቂው ማነው ? የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለማስቆም ፍላጎት የለውም የሚሉ ሐሳቦች ይነሳሉ፤ እርስዎ ምን ይላሉ?
እኔ የክልል መንግሥት ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ መንግሥት ችግር አለበት። እኛ በችግሮቹ ላይ የመፍትሔ ሐሳቦችን አቅርበናል፤ ተወያይተናል፤ ችግሮችን አሳይተናል። አንድ ቡድንን ብቻ በራሱ ፍላጎት መፍትሔ አያመጣም ብለን መፍትሔ አቅርበናል፤ ግን የሚሰማን አላገኘንም። አሁን ለምሳሌ ስለ አገራዊ ምክክሩ በተገባበት መንገድ ብዙ ችገር አይፈታም ብለን ደብዳቤ ኹሉ ጽፈናል፤ የሚሰማን አላገኘንም።
አለመደማመጥ የሚያመጣውን እያየነው ነው። በመገዳደል ፖለቲካ መቀጠል ነው፤ የመገዳደል ፖለቲካ አንዱ ሌላውን “ቡዳ” እያለ መቀጠል ነው። እና መጨረሻችንን እንይ ከማለት ውጭ ቸግሮናል ማለት ነው።
በኦሮሚያ ክልል ለዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆነው “ሽኔ” የሚባለው ታጣቂ ኃይል እንደሆነ መንግሥት ይገልጻል፤ “ሸኔ” የኦሮሞን ሕዝብ ይወክላል ብለው ያስባሉ?
ሁለም የኢትዮጵያ ችግር የሚጀመረው እኮ ወኪል መጥፋቱ ነው። ሕዝቡ የሚወክለኝ ብሎ እንደዚህ ነው የሚባል ድርጅት ወይም ግለሰብ አልመረጠም። ሁሉም ተነስቶ ሐጢያቱን ይዞ ጉልበቱን ይዞ አኔ ነኝ ተወካይ ይላል። በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት ለምን ዝም እንዳለ አላውቅም፤ ሸኔ የሚባለው ለሠው በሚገባው ቋንቋ ኦነግ ነው። ኦነግን በስም መጥራቱ ወይም የኦነግ ታጣቂ ነው ብሎ መጥራቱን መንግሥት ለምን ዝም እንዳለ አላውቅም።
ዞሮ ዞሮ ግን አሁን ፖለቲካ አልተመቸኝም ብለው ጫካ የገቡ፣ ጠመንጃ የያዙ የኦሮሞ ልጆች አሉ። በምንም ሥም ይጠሩ፣ መንግሥት ሸኔ ሊል ይችላል፣ የኦሮሞ ሕዝብ ደግሞ የኦሮሞ ታጣቂዎች ናቸው ሊል ይችላል። ነፃ አውጪ አባላት ናቸው ሊል ይችላል። በዓለም ደረጃወም የአንዱ ነፃ አውጪ የሌላው ሽብርተኛ ሊሆን ይችላል። ዋናው ጉዳይ ግን አሰያየሙ ማንም ሰየመ ማን የኦሮሞ ሕዝብ እንዴት ያይሃል ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ዞሮ ዞሮ እኛም እዚሁ አካባቢ እንቀሳቀሳለን ቀላል ድጋፍ የላቸውም።
የኦሮሞ ታጣቂዎች ናቸው የሚሆኑት፣ እስከምናውቀው ድረስ ባሉን መረጃዎች ቀላል የሕዝብ ድጋፍ የላቸውም። የላቸውም ብሎ ማረጋገጥ የሚቻለው ደግሞ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ፈተና በሀቅ መሬት ላይ አምጥቶ፣ ከዚያ በኋላ ማን እንደሚመረጥ ማን እንደሚያሸንፍ፣ ሕዝቡ ማንን እንደሚደግፍ ጠመንጃውን ከጨዋታ አውጥቶ ማለቴ ነው። በጠመንጃ ሳይሆን ውድድሩ በምርጫ ሳጥን ሆኖ የዚያን ጊዜ ማን እንደሚያሸንፍ ሌሎችም የፖለቲካ ኃይሎች አሉ እኛ ጭምር ማለቴ ነው፤ ያን ፈተና መንግስት እስካላለፈ ድረስ ንጉሱም እኮ እነ ማሞ መዘምርን አገር በታኝ ነው የአገር አንድነት ብሎ ሰቅሏል።
በጠመንጃ ፖለቲካ ለመፍታት የሚሞክሩ ብዙ አገሮች ብዙ አልተሳካላቸውም። ተደራድረው ደሞ ብዙ የተሳካላቸው አሉ። እንደገናም ደሞ በተለይም በዚህ የአገር አንድነት ጥያቄ ዩጎዝላዚያ እንደ ቀልድ እኮ ነው የፈረሰችው። የሰርብ ብሔርተኝነት ምናልባት ዩጎዝላቪያን የበለጠ ሊወድ ይችላል። ዩጎዝላቪያን በትኖ ያን የጋራ የነበረውን መሪም ራሱን ገሎ ነው የተገኘው።
ስለዚህ ኢትዮጵያ አትፈርስም ብቻ ማለታችን፣ እኛ ሐቀኛ ነን ሌሎቹ ወንጀለኛ ናቸው፣ ሌሎቹ ሽብርተኞች ናቸው፣ ብሎ ማለት ብቻ የኢትዮጵያን ችግር አልፈታም። እኔ እስገሚገባኝ ድረስ አሁንም የሚፈታ አይመስለኝም።
ኦፌኮ ቀጣይ በሚካሄደው አገራዊ የውይይት መድረክ ላይ እንደማይሳተፍ ከአንድ ሳምንት በፊት መግለጹ አይዘነጋም። ፓርቲው የሐሳብ ለውጥ አድርጎል? ወይስ ባቋሙ እንደፀና ነው?
እኛ ብዙ ጊዜ አሳውቀናል። ክፍተቱንም አሳውቀናል። ቅድም እንዳልኩት ለጠ/ሚኒስትር ቢሮውም ለፓርላማውም በተሄደበት መንገድ የትም አንደርስም ብለን አሳውቀናል። ለምሳሌ ኹለት ቁልፍ ጉዳዮች አሉ ሌሎችም እንዳሉ ሆኖ። አንደኛው ያ ተቋም አካሂዳለሁ የሚለው ተቋም ገለልተኛ ሆኖ፣ ነጻ ሆኖ ለመንቀሳቀሱ ለሁሉም የማይወግን ተቋም ለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለንም።
አሁን እየተካሄደ ያለው አንድ ፓርቲ የራሱን ዳኛ ይዞ ወደ ሜዳ እየገባ ነው። ማለት እስከምናውቀው ድረስ ፓርላማው 98 በመቶ ከአንድ ፓርቲ ነው። የቀረችው ኹለት በመቶም ያን የሚደግፉ ናቸው። ስለዚህ መቶ በመቶ አካባቢ የአንድ ቡድን ፓርላማ ያን ኮሚሽን ሠይሞ ይሄ ኮሚሽን ደሞ ገለልተኛ ነጻና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይዳኛል የሚል እምነት የለኝም።
ሰዎቹም አንዳንዶቹ ጓደኞቼ ናቸው አውቃለሁ። ግን መሬት ላይ ያለው እውነታ ያን ለማስደረግ የሚችል አይደለም። ዞሮ ዞሮ ችግሮችን አይፈታም።
ኹለተኛ ትልቁ ነገር ደግሞ የአካታችነት ጥያቄ ነው። ስለዚህ ኹሉም ወገኖች ጠመንጃ የያዙም ጭምር በዚህ ጉዳይ ላይ ካልገቡና ተወካዮቻቸውን በዚህ ኮሚሽን መዋቅር አባላት ዝርዝር ላይና በዚህ ኮሚሽን ላይ እምነት የለንም ካሉ ጠመንጃ አያስቀምጡም ማለት ነው።
ጠመንጃ ያነሱትን ጠመንጃ እስከሚያስቀምጡ ድረስ ደሞ ስንት መቶ ሺሕ ኢትዮጵውያን ሊያልቁ ይችላሉ? የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየታዬ ነው። አገሪቷ ምናልባት እስካሁን ድረስ በጣም አስቸጋሪ ሊባል በሚቻል ሁኔታ ውስጥ እየገባች ነው።
ስለዚህ ይህን ሁሉ ቀውስ፣ በኢኮኖሚውም፣ በፖለቲካውም፣ በሠው ሕይወትም ረግድ ያለው ቀውሱ እንዲቀጥል መፍቀድ ማለት ነው። እኔ ለምሳሌ፣ አምቦ ሔጄ እነዚህ ጫካ የገቡ ተዋጊ ወጣቶች ጠመንጃ አስቀምጡ ለማለት ምን ብዬ ነው የምለው? እነሱ ይሰሙኛል ወይ? ስለዚህ ዋናው ጉዳይ፣ ድርድር የሚያስፈልገው ከወዲያ ያሉትን ኃይሎች ጠመንጃ አስቀምጣችሁ ተደራደሩ ለማለት ነው። እሱ ደግሞ መተማመን ያስፈልገዋል። አስቀምጥ ጠመንጃህን ለማለት ከማረክከው ትችላለህ። አለበለዚያ ግን ጠመንጃ አናስቀምጥም ይላሉ። ስለዚህ ችግር ይሆናል።
የገለልተኝነት ጥያቄ በዚህ በቀጠለበት መንገድ አልተፈታም፤ አይፈታም ነው የእኛ አቋም። እሱን ደግሞ ለፓርላማውም ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ፅፈናል። በነገራችን ላይ እኛ ብቻ እኮ አይደለንም። ባለፈው ጊዜ ለምሳሌ ወደ 50 አካባቢ የሚሆኑ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰብስበው አሁን በተኬደበት መንገድ ሠላም አያመጣም፤ ጦርነቱን አያቆምም፤ የአገራችን ዕጣ ፈንታ በእንደዚህ ዓይነት መንገድ መወሰን ያስቸግራል ብለው እኮ ሙሉ ድምጽ ሊባል በሚችል ደረጃ (ባለኝ መረጃ ከሦስት ፓርቲዎች በስተቀር) ወስነዋል። ሠሞኑንም በተሔደበት መንገድ እንደማያዋጣ መግለጫ እያወጣ ነው። መንግሥት ይህን ሒደት አቁሞ ማስተካከያ እንዲያደርግና እንዲያርም እኛ ብቻ አይደለንም እየጠየቅን ያለነው። ከ50 በላይ ከሆኑ መካካል እንደሰማሁት ወደ ሦስት ፓርቲዎች ብቻ ናቸው በመንግሥት ሐሳብ መግፋት የፈለጉት። ሌሎቹ በሙሉ ድምጽ የተገባበት መንገድ አያዋጣንም ብለዋል።
የእነ ጀዋር ኦፌኮን መቀላቀል ለፓርቲው እንቅስቃሴ እስካሁን ያመጣው ለውጥ ምንድን ነው?
ጀዋር እንደአንድ ግለሰብ እኛ ፓርቲ ጋር መቀላቀሉ፣ እሱ ጠይቆ ነው እኛም ፈልገን ነው። የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ ነው። አንድ ድርጅት ይጠቅመኛል የሚለውን ኢትዮጵያዊ በሕጉ መሠረት አባል የማድረግ መብት አለው። አይጠቅመኝም ብሎ ደግሞ ከወሰነ የፓርቲው መብት ይመስለኛል። ብልፅግና ፓርቲም ይሁን ሌሎች ፓርቲዎች፣ እነጀዋር በተለይም የኦሮሞ ወጣቶች እንቅስቃሴ ውስጥ የተጫወቱትን ሚና የሚያውቁ ይመስለኛል። ምንአልባት ከቤታቸው ይልቅ ኮንግረስን ለምን መርጦ ገባ ነው እንጂ፣ እነጀዋር በቄሮ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበራቸውን ሚና የሚክዱ አይመስለኝም። ስለዚህ ዋናው ጉዳይ ፓርቲው ይጠቅመኛል አይጠቅመኝም የሚለውን ቢወስን ይሻለዋል። ጉዳዩ ለፓርቲው ቢተው ይሻላል። እኛ ይጠቅመናል ብለን አባል አድርገናል። ብዙ የፓርቲ አባላት ያንን ይደግፋሉ፤ ተቀብለውታል። በጣም ብዛት ባለው መንገድ ስለተቀበሉት በእኛ ዕይታና ሚዛን ፓርቲውም በጣም እየተጠቀመ ነው።
እነ ጀዋር ከእስር ከተለቀቁ በኋላ እንደ ፓርቲ ምን እየሠራችሁ ነው?
የድርጅቱን ሥራ ማጠናከሩን ቀጥሎበታል፤ በቅርብ ጊዜ ደግሞ ጠቅላላ ጉባኤያችንን እናካሒዳለን ብለን እየሠራን ነው። በፓርቲዎች ክርክር እና ውይይትም እንሳተፋለን፤ የአቅማችንን ያክል የአገሪቱን ፓለቲካ እንዲስተካከል መንገድ እንዲይዝ ኹላችንም በሚጠቅም መንገድ እንዲመራ የራሳችን አስተዋዖ ለማድረግ እየጣርን ነው። ገዥው ፓርቲ ጭምር ጋዲሳ ኦሮሞ ብለን ተፈራርመን ፖለቲካውን ለማስተካከል ሙከራወች ነበሩ፤ ከዛ በኋላ ገዥው ፓርቲ ከዛ ሲወጣ እና ሌሎች ወደ ገዥው ፓርቲ ያዳሉ ሲወጡ እኛ እና ኦነግ በኦሮሞ ብሔር ላይ እና ኦሮሚያ ውስጥ በሚደረጉ እንቅስቃሳሴወች ለመተጋገዝ ምርጫ ወስደን በጋራ ለመግባት ተፈራርመናል። የተደበቀ ነገር የለውም ተፈራርመን ስንቀሳቀስ ነበር፤ መንግሥትም ያውቃል። የተደበቀ ምስጢር የለውም ማለቴ ነው። የኦሮሞን ሕዝብ ፖለቲካ የመብት ትግል በጋራ ለመሥራት በምንተባበርባቸው በጋራ ምርጫ ውስጥም መግባትን ጨምሮ ተስማምተን ያንን ሥራ ለማዋል ያቅማችንን እንቅስቃሴ እየጀመርን ነው። መንግስት በመደናገጡ ይሁን በሌላ መንገድ ኦነጎች ላይም ዕርምጃ መውሰድ ጀመረ። እኛ ላይ መውሰድ ዕርምጃ መውሰድ ሲጀምር ከምርጫ በፊት አንድ አመት አካባቢ ቢያንስ ቢያንስ ስድስት ወር አካባቢ ወደ 206 ቢሮወች ነበሩን፣ አሁን ያለን ሦስት ቢሮዎች ብቻ ናቸው። 203 ቢሮዎች ተዘግተውብናል ማለት ነው።
እነ ጀዋር ተፈቱ እንጅ ብዙ ቦታ አባሎቻችን አሉ፤ አሁንም ዕሥር ላይ ናቸው። ለምሳሌ፣ በነ ጀዋር ምክንያት የታሠረ ምስራቅ ሐረርጌ ላይ የኛ ድርጅት ቢሮ ኃላፊ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አንዋር ሳኒ የሚባል ልጅ፣ የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርስቲ አስተማሪ የሆነ አሁንም እስር ቤት ነው ያለው። እነ ጀዋር ተፈቱ እንጅ በነ ጀዋር ምክንያት የታሠሩ ሠዎች ደግሞ አልተፈቱም ። እኛ ሕጋዊ እና ሠላማዊ ትግላችንን እንቀጥላለን። ሕጋዊ እና ሠላማዊ ትግላችንን የምናደርገው ደግሞ የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ሁላችንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዲሞክራቲክ ኢትዮጲያ እንድትፈጠር እና ሠላም፣ መረጋጋት በአገራችን እንዲፈጠር፣ ከኹሉም በላይ ደግሞ ሦስት ትላልቅ የአገሪቱ ጥያቄዎች እንድፈቱ ነው።
አንደኛው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት በአገራችን አንዲሰፍን አንፈልጋልን። ለዚያም አንታገላለን። ኹለተኛው ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር በአገራችን አንዲመጣ አንፈልጋለን፤ ለዚያ ሕጋዊና ሠለማዊ ትግላችንን አንቀጥላለን። ሦስተኛው ደግሞ፣ ኹለቱንም ካገኘን ትርጉም ያለው የኢኮኖሚ ልማት እና ዕድገት እንዲፈጠር አንፈልጋለን። ሕዝባችን በልቶ እንዲያድር የተሻለ ዕድል እንዲገጥመው እንፈልጋለን፣ ለዚያም አንታገላለን። ሕጋዊና ሠላማዊ ትግላችንን እንቀጥል። ከመገዳድል ፖለቲካ ወደ መደራደር ፖለቲካ እንግባ።
“ቡዳ” ወይም “የቡዳ ፖለቲካ” ሲሉ በተደጋጋሚ ይደመጣሉ ምን ማለት ነው?
የቡዳ ፖለቲካ በባህላችን እኔ ያደኩበት የኦሮሞ ማኅበረሰብ ተረቱ አንድ ንጹሕ የሆነ ሰው የቡዶች ሠፈር ይሄድና አንዱን ቡዳ ያገኘዋል፣ ቡዳ ማነው ብሎ ያንን ቡዳውን ይጠይቀዋል። ቡዳው ደግሞ እኔ አንዱ ነኝ ማለት አፈረና እኛ እዚያ ማዶ ያሉ ሰዎች ቡዶች ናቸው እንላለን አነሱ ደግሞ እኛን ቡዳ ይሉናል ብሎ መለሠለት ይባላል።
ነገርየው ምንድን ነው? እራስህ በሆንካቸው እና በምታጠፋቸው ነገሮች ታፍርና እራስህ ነፍሰ ገዳይ ሆነህ ነፍሰ ገዳዮች ሌሎቹ ናቸው፤ እራስህ አጥፊ ሆነህ አጥፊዎች ሌሎቹ ናቸው፤ እራስህ የኢትዮጵያን ፖለቲካ አበላሽተህ አጨማልቀህ ሌሎቹ ናቸው ያጨማለቁት እኔ ንጹሕ ነኝ የሚለውን የአገራችን ባህልና ክርክር ለመግለጽ ብዬ ነው። የራስን ጥፋት ወደ ሌላው ማሸጋገር የአባዬን እከክ ወደ እምዬ የሚለው ማለት ነው፣ ይቀራረባል።
ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014



