ሌብነት፣ ዝርፊያና አጭበርባሪነት ግለሰብን ብቻ ሳይሆን አገርንም ሆነ ትውልድን የሚቀጭ የሠው ልጆች ጠላት ነው። መሥረቅ እንደማይገባ ኹሉም የሚያውቀው ቢሆንም፣ አሁን አሁን የማይሠርቅና የማያጭበረብር እንደጅል የሚቆጠርበት ወቅት ላይ ደርሰናል። አትሥረቅ የሚለው ክልከላን የማያውቅ ባይኖርም፣ መንፈሳዊ ትዕዛዝ ብቻ አለመሆኑን የሚያውቀው ኃይማኖተኛ የሚባለውም ጭምር መሥረቅን ዘመናዊነት ወይም ፋሽን አድርጎታል።
በፊት በፊት እጅ መንሻ ይባል የነበረውና አሁን በተለያየ ሥም የሚጠራው ጉቦ፣ እያደር አገራችንን እንድትማቅቅና ሌላውም በዚሁ ምግባር እንዲያውቀን እያደረገ ነው። ሙሥና የሚባልና የተለያየ የማሽሞንሞኒያ ሥም እየተሠጠው የሠሪዎቹን ሠብዕና ለመጠበቅና ላለመስደብ እየተባለ ክብራቸው ሲጠበቅላቸውም ይታያል። ሌባ ሌባ ነው ካልተባለ፣ ወንበዴም ፣ ዘራፊም እንዲሁ በሥሙ ካልተጠራ ችግሩን መቅረፍ እንደማይቻል አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ከሕግ አንጻር ሲታይ ተደብቆ የሚሠርቅ፣ በማንዓለብኝነት ዕምነትን አጉድሎ የሚመዘብር፤ በጠራራ ፀሐይ የሚዘርፍ፣ ተደራጅቶም ሆነ አሳቻ ቦታ መርጦ አስፈራርቶ የሚቀማ ወንበዴ፣ እንዲሁም አጭበርብሮ በዘመኑ ቋንቋ የሚያጎድልም ሆነ በዘመድ አዝማድ ተጠላልፎ የሚጠቃቀም እንደአጠራሩ የተለያየ ቅጣት ይኖረዋል። ነገር ግን፣ በወንጀሉ ግለሰቡ የሚያገኘው ጥቅምና ቅጣቱ ስለማይነጻጸር፣ አንዳንዱ ዘርፎ ተይዞ ዘብጥያም ቢወርድ የማይቆጭበት ጊዜ ላይ ደርሠናል።
በዝርፊያ የተገኘ ሃብት ለባለቤቱ እንዲመለስ ቢደነገግም፣ ይህ ሲሆን ግን ዕየታየ አይደለም። በርካታ ባለሥልጣናትን ጨምሮ ግለሰቦች በሙሥና ተከሠው ዕሥር ቤት ሲገቡ እንጂ የዘረፉት ተመለሰ ሲባል አይሰማም። እንደውም፣ ሃብቱን ቤተ-ዘመዶቻቸው ሲጠቀሙበትና ከዕሥር ወጥተው ሲረከቡት ይታያል። በዝርፊያ የተገኘ ሃብት ከሙሠኞች ላይ ሲወረስ ባይታይም፣ በሽብር እየተባለ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሃብት ሲነጠቅና ለሌላው ማስፈራሪያ ሲሆን ይስተዋላል። ይህ አሠራር ላለፉት 30 ዓመታት ሲተገበር የነበረና አሁንም ልምዱ ባላቸው ባለሥልጣናት የቀጠለ እንደሆነ ይታወቃል።
የቀደመውን መንግሥት ለውድቀት የዳረገ ሌብነት አሁን እያንሠራራ ነው ማለት ብቻ ሳይሆን የቀደመውንም እያስናቀ ነው። ፀረ-ሙሥናም ሆነ ኦዲት ቢሮ ያሉ ከጉዳዩ ጋር ተቀራራቢ ሥራን የሚሠሩ ተቋማት ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ይናገራሉ። ለመቀነስና ለማጥፋት ከመሥራት ይልቅ፣ ጦርነትን የመሳሰሉ ችግሮችን ሠበብ በማድረግ ለከት በሌለው መንገድ መዝረፋቸውን ይናገራሉ። ይህ ሒደት በዚሁ ከቀጠለ አገር የማትከፍለው ዕዳ ውስጥ በጥቂት ስግብግቦች አማካኝነት መግባቷ አይቀርም።
ሌባ የሚያመልጥበት ወይም የሚያስጥለው ስለመኖሩ ሳይተማመን እንዲህ በግላጭ እንደማይዘርፍ ይታወቃል። ትንሹ ጉቦኛ የትልቁን እየደበቀና ለውለታው ከለላ እያገኘ እንደሚዘርፍም ሕዝብ ያውቀዋል። ማንም ሳያውቀው የሚዘርፍ ቢኖርም፣ ባለው ቢሮክራሲ ብቻውን “የሚበላ” እንደሌለ በግልፅ ይነገራል። ጉቦ የሚቀበል የመኖሩን ያህል ሠጪ መኖሩንም መገመት አይከብድም። አይታወቅብኝም ብሎ እርግጠኛ ኹኖ የሚዘርፍ እንደሌለ ግን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ሙሠኞች እርስ በርስ ስለሚደጋገፉና ስለሚተማመኑ ሠንሰለታቸውን በጥሶ ለማጋለጥም ሆነ ለመበታተን አስቸጋሪ መሆኑን የሚናገሩ አሉ። እነሱ እንደሚተጋገዙ እነሱን ለማጋለጥ የሚሠሩ ግን ሲተባበሩ አይታይም። ይህ የሆነው ስለሙሠኛም ሆነ ስለሌባ ያለው ጥላቻ እንዲሸረሸር በዘዴ ሲሠራበት ስለኖረ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
“ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለውን ብሒል አለልክ አጉነው ሕብረተሠቡ እንዲያዝንላቸው፣ እሱም ተረኛ ቢሆን ሊያደርገው እንደሚችል በማሳሰብ የነበረ ጥላቻ ቀስ በቀስ እንዲወገድ ተደርጓል። ይህ ብቻ ሳይሆን ሌቦች ሲካፈሉ እንዳይጣሉ አስቀድመው ስምምነት ስለሚገቡ፣ ክፍተት አግኝቶ ለማወቅ አሊያም ጥቆማ ለማግኘት አዳጋች እንዳደረገው ይታመናል።
መንግሥት ለራሱ ሲል ሌባ ከሌባ እንዳይተማመን፣ ሙሥና ሠሪዎች መካከል መጠራጠር እንዲፈጠር ሊያደርግ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ላጋለጠ ሠው ከጠቆመው መጠን የተወሠነውን ማካፈሉ እንዳለ ሁኖ፣ እንዳይሠረቅ የሚያደርግም ከልካይ መንገድ ሊመቻች ይገባል። ሙሠኞች የሚበዙበትን የሥራ መስክ በመለየት ልዩ ክትትል በማድረግ ጉዳይ ኖሮት የሚመጣን ኹሉ እንዲጠራጠሩት ማድረግ ይገባል።
ፀረ-ሙሥናን የመሳሰሉ ተቋማት በፊት በፊት የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጉዳይ ብቻ ይከታተሉ ነበረ ሲሆን፣ ከጊዜ በኋላ ሌሎችንም እንዲያካትቱ መደረጉ ይታወቃል። ይህ ቢሆንም ግን የደረሳቸውን ጥቆማ ብቻ መነሻ በማድረግ መርምረው ለሚመለከተው ከሳሽ አካል ያስተላልፋሉ እንጂ፣ ራሳቸው ለሙሥና የሚጋለጡት ጋር እየተገኙ ፍተሻ ሲያደርጉ አይስተዋልም። ይህም እስከአሁን ሥር ሠዶ ለቀጠለው ማስገደጃ መንገድ በር እንዲከፍት አድርጓል።
ባለሥልጣናትም ሆኑ ባለሃብቶች የዘረፉትንም ሆነ ያደረጉትን ያልተገባ ነገር በማስረጃ እያሰባሰቡ አከማችተው ከፖለቲካው “ከተዛነፉ” ከፋይል እየመዘዙ ፀረ-ሙሥና ጠረጴዛ ላይ ማስቀመጥ ተለምዷል። በዚህ መንገድ የተከሰሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ የክልል ፕሬዝዳንት ጥፋተኛ ተብለው የታሠሩበት ተመዘበረ የተባለው ሀብት ግን ከቤተሰቦቻቸው እጅ እንዳልወጣ ይነገራል። ይህ የሆነበት ምክንያትም፣ “የድርጅት ምስጢር” እንዳያባክኑ በሚል ሠንካላ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል።
በአቶ ስብሓት ነጋ ቁጥጥር ሥር እንደነበረ የሚነገረው የሹማምንቱን ቅሌት፣ ተረኛው ግለሰብ ይዞ ለቀጣዩ ዘመን እንደፈለገ ባለሥልጣናቱን እያሾረ በዚህ አገር ገዳይ መንገድ እንዳይቀጥል ባለሥልጣናቱ ጭምር ኹሉም ሊተባበር እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ስለማንኛውም ዓይነት ወንጀል መረጃው በእጁ ላይ ያለ ሠው ወዲያው ለሕዝብ እንዲደርስ ካላደረገ የወንጀሉ ተባባሪ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። ሕጉ ወንጀል ስለመሠራቱ የሚቀርብ ማስረጃ ማስገደጃ ሆኖ እንዳያገለግል ለፍርድ ቤት ሊቀርብ የሚችልበትን ጊዜ ሲያስቀምጥ፣ ያ ሠው ማስረጃው እጁ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሆን እንደሚገባ ቢያስቀምጥም ይህ ግን ሲጣራ አይስተዋልም።
ከሠሞኑ በአማራ ክልል የፓርቲ ብር በባለሥልጣናት ተመዘበረ ተብሎ የሕዝብ መነጋገሪያ መሆኑ ይታወቃል። በጦርነት ብዙ ሀብት ወድሞበት የለጋሾችን እጅ ለሚጠብቅ ግዛት 60 ሚሊዮን ብር ምን ያህል ትልቅ ብር እንደሆነ ግልጽ ነው። ገንዘቡ የፓርቲ ነው ቢባልም፣ በሕዝብ ሥም የተሰበሰበ እንደመሆኑ ተጠያቂነት ሊያመጣ ይገባል። ይህ በአንድ ከፍተኛ አባላቸው የቀረበ ቅሬታ እውነት ነው ብሎ ማኅበረሠቡ የተቀበለውን ያህል፣ አጣርቶ ወደክስ ሊገባ የሚገባው አካል እስካሁን ምንም አለማለቱ ተገቢ አይደለም። በክፉ ወቅት እንዲህ ዓይነት ለሕዝብ ጥቅም ተብለው የሚሰበሰቡ ሀብቶች ሲባክኑም ሆነ ለግል ጥቅም ሲውሉ ዕያየ ዝም ያለ ኹሉ ተባባሪ ሁኖ ሊጠየቅ እንደሚገባ የአዲስ ማለዳ ዕምነት ነው።
አንድ ሠው አንድን ዶሮ ከግለሰብ ላይ ሠረቀ ተብሎ ዓመት ከኹለት ወር ዕሥራት በሚፈረድባት አገር፣ ከሕዝብ ላይ ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ገንዘብ የዘረፉትን ለፓርቲም ሆነ ለአገር በሚል ማደናገሪያ ቅሌታቸውን ደብቆ ማቆየት፣ ርቦት ምግብ ያጣ ረሃብተኛ ላይ የሚበላውን ደብቆ እስኪበላሽ ከማቆየት የማይተናነስ አሳፋሪ ተግባር ነው።
አዲስ ማለዳ ከሕዝብ ሀብት ላይም ሆነ ከግለሰቦች ላይ እየመዘበሩ አላግባብ የሚበለጽጉ ወዲያውኑ ሊጋለጡ እንደሚገባ ታስገነዝባለች። ይህ እንዲደረግም የየመሥሪያ ቤቱ ሪፖርትም ሆነ የኦዲት ምርመራ፣ ሕዝብም ሆነ ውስጡን የሚያውቀው ሠራተኛ በቀላሉ እንዲያገኘው ይፋ እንዲደረግ ትጠይቃለች። ለኮሚቴ ብቻ ቀርቦ ተዳፍኖ የሚቀር ወንጀል እንዳይኖር እንደነጋሪት ጋዜጣ ኹሉም ሊያገኘው የሚችለው መረጃ እንዲሠራጭ መሠራት ይኖርበታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014