ባለፉት ሳምንታት መነጋገሪያ ከነበሩ አንኳር ጉዳዮች መካከል ከአዲስ አበባ-ባህርዳር-ጎንደር መስመር ጋር በተገናኘ መንገደኞች ላይ ሲፈፀም የቆየ ግድያ አንዱ ነው። የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያን ከመሀል አገር የሚያገናኘውን መስመር በተደጋጋሚ እንዲዘጋ ያደረገው የሠላም ዕጦት መንስዔ በአካባቢው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መግባት እንደሆነ ይታወቃል።
መንግሥት በአሸባሪነት ከፈረጃቸው ኹለት ቡድኖች አንዱ የሆነው ይህ በኦሮሚያ ክልል እንደሚንቀሳቀስ የሚታወቀው ታጣቂ ቡድን፣ ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑ ይነገራል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ጭምር ከ300 በላይ የክልሉን ከተሞች እንደተቆጣጠረ የተነገረለት ይህ ቡድን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን አንዲሞቱ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ ግድያውንና ስቃዩን ሽሽት በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ እንዲፈናቀሉ አድርጓል።
በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ሠሞን ብቻ በተለያዩ ቦታዎች በርካቶችን ገድሎ ቀሪዎችን ያፈናቀለ ሲሆን፣ ግድያውን አምልጠው 400 የሚሆኑ ተፈናቃዮች አዲስ አበባ መጥተው የሚጠለሉበት ፍለጋ ሲንከራተቱ ነበር። ሕፃናት የሚበዙበት ይህ የተፈናቃይ ቡድን፣ ማረፊያ አጥቶ የካ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሰኞ የካቲት ሰባት ተገኝቶ ነበር። ተፈናቃዮቹ ወዲያው በፀጥታ ኃይሎች ተከበው እየተዋከቡ ግቢው ውስጥ እንዲቆዩና ሠው እንዳይቀርባቸው ከተደረጉ በኋላ፣ ምሽት ተገን ተደርጎ ወደ ፈረንሳይ ጉራራ አካባቢ በመኪና ተጭነው ሕዝብ እንዳያያቸው ገለል እንደተደረጉ የሚናገሩ አሉ።
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በርካቶች እየመጡ ደብረብርሃንን ወደመሳሰሉ ቦታዎች ተጭነው እንደተወሰዱ ይሠማል። እነዚህ ከሞት የተረፉ ዜጎች እንደሚናገሩት ኹኔታዎች እያደር እየተባባሱ መምጣታቸውን ነው። በወለጋ አካባቢ ይዘወተር የነበረው ይህ ጥቃት አሁን አድማሱን አስፍቶ ጎጃም መስመር በሚባለው አካባቢም መበራከቱን እያጣቀሱ የሚናገሩ ሰዎች የኹኔታውን መባባስ ያስረዳሉ።
ለበርካታ ሹፌሮችና መንገደኞችም ሞት ምክንያት የሆነው በዚህ መንገድ ላይ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን፣ አሁን አሁን ከተማና የገጠር ቀበሌ በመግባት ነዋሪዎችን በመግደልና ቤታቸውን በማቃጠል መጠመዱ ይነገራል። አንዳንዶች የመንግሥትን ድክመት ለመሸፈን፣ ሌሎች ደግሞ ለታጣቂዎቹ በመወገንም ሆነ ኹኔታውን ለማሳነስ በመሞከራቸው እስከዛሬ ጉዳዩ ተድበስብሶ መቆየቱ ይነገራል።
የሠሞኑ ጥቃት መበራከቱና ብዙዎች ማለቃቸውን ተከትሎ ግን፣ መንግሥት አቅም ካጣ እኛ ወደቦታው እንዘምታለን የሚል አካል በመሠማቱ ጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት ተደርጎበታል። መንገዱ በተደጋጋሚ እየተዘጋ መልሶ ለተሸከርካሪ ክፍት ሲሆን ትኩረቱም እየደበዘዘ እዚህ መድረሱን የሚናገሩ አሉ። ታጣቂዎቹ ከመንግሥት ሹመኞች ጋር በትብብር የሚሠሩ ስለሆነ ነው እንዲህ እንደልብ የተለቀቁት በማለት ብዙዎች ቅሬታና ምሬታቸውን የሚያሰሙበት ይህ መስመር፣ አሁንም ለዕልቂት ምቹ ስለሆነላቸው ትኩረት እንዲደረግበት ተደጋጋሚ ጥያቄ ይቀርብበታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014



