በአውሮፓ ኅብረት የ4 ነጥብ 8 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ለ3 ዓመት የሚተገበር በማኅበራዊ ተግዳሮቶች፣ በጤና እና በሥርዓተ-ጾታና ኩልነት ላይ የሚሠራ ፕሮጀክት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይፋ ተደርጓል።
ፕሮጀክቱ እንደ አገር ጤናማ ማኅበረሰብ በመፍጠር ምርታማነት እንዲኖር በጤናው ዘርፍ የሚተገበሩ ሥራዎችን በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ተብሏል፡
ፕሮጀክቱም በክልሉ በጤና ላይ እና በሥርዓተ-ጾታ ላይ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በሚቀርፍ መልኩ ተፈጻሚ እንዲሆን፣ የፕሮጀክቱ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት እና የክልሉ ሴክተሮች ከወቅታዊ ኹኔታው ጋር በማገናዘብ ለውጤታማ ሥራ በኃላፊነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ነው የተገለጸው።
ፕሮጀክቱ በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ፣ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውል ሠጭነት በ4 ነጥብ 8 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲገባ መደረጉ በመንግሥት አቅም ሊሽፈኑ ያልቻሉ የጤና ፕሮግራሞችን በማዳረስ የክልሉን ጤና ሽፋን የሚያግዝ መሆኑም ተመላክቷል።
በተለይ ፕሮጀክቱ በሴቶች ላይ፣ በታዳጊ ልጃገረዶች፣ እንዲሁም ከ5 ዓመት በታች ያሉ ሕጻናትን ጤና እና አመጋገብ ለማሻሻል በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ለማወቅ ተችሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014


