ከሠሞኑ በጣም የታዝብኩትንና የገረመኝን ሐሳብ ላካፍላችሁ ወደድኩ። እኔ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቴአትር ትምህርት ተመርቄ ሥራ እያፈላለኩኝ ሳለ፣ ወደ ተለያዩ የአገራችን ፊልም ሠሪዎች ሔጄ ነበር። ኹሉም ነገር አልጋ ባልጋ ሆኖ አላገኘሁትም። የለፋሁለት እና ዋጋ የከፈልኩለት ትምህርቴ እንደጠበቅኩት አልሆነልኝም። በምወደው እና በተመረቅኩበት ሙያ ለመሥራት ብዙ ተፈተንኩኝ። አብዛኛው ቦታ የታዘብኩት ነገር፣ ፊልም ላይ እንዲተውኑ የሚመለመሉት በቁንጅና የተመረጡና ፊልም የመሥራት ፍላጎቱ ብቻ ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን ነው። ይህን ያስባለኝ ቀጣሪዎቹ የሚመዝኑባቸውን መሥፈርቶች ካስተዋልኩ በኋላ ነው።
ውበት፣ ፍላጎትና መሥራት መቻል የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ፊልም ለመሥራት ውበት መሥፈርት መሆን ነበረበት? ለምን ብቃትና ትምህርት አይታይም? የሴትን ልጅ መልክ መገምገሚያና መጠቀሚያ ማድረግስ መቼ ነው የሚያበቃው? የሴትን ክብር እና ማንነት የሚነካ በርካታ ዘርፍ ቢኖርም፣ የአገራችን የፊልም ሙያ ግን በግላጭ መሆኑ አስገራሚ ነው።
የመሥራት ፍላጎትና ብቃት ያላት ሴት ተገቢ ባልሆኑ መሥፈርቶችና መድሎዎች ከምትወደው ሙያ ስትርቅ ማየት እየተለመደ ነው። ይህ ችግር በአገራችን ፊልም ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። አንድ ሴት በተሻለ መልኩ መተወን እየቻለች ጾታን መሠረት ባደረገ ጥያቄ መሠረት የምትፈልገውን ሳትሠራው ትቀራለች፣ አሊያም የማትፈልገውን ነገር እንድታደርግ ትገደዳለች።
ሙያዊ ብቃትን ማዕከል ያላደረገ አሠራር የባለሙያውን ሥነ-ልቦና መጉዳት ብቻ ሳይሆን፣ የፊልሙ ዘርፍም እንዲጎዳና በቀላሉ ወደ ዕድገት እንዳያመራ ማነቆ ይሆንበታል። በእንዲህ ዓይነት ያልተገባ መንገድ ለሕዝብ የሚቀርቡ ፊልሞች የተሠለቹና ተቀባይነት ያጡ ይሆናሉ።
ሴት ልጅ ዉድ ናት። የዓለም ብርሃን ናት። ዓለም ላይ ያለ ኹሉንም ነገር በዕኩልነት የማግኘት መብት አላት። ሕልሟን ልትኖር ይገባል። በዓለማችን አሁን ድረስ የሴቶች መብት በአግባቡ እየተከበረ አይደለም። አሁን ድረስ ቤት እንድትውል እና የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ እንዳትሳተፍ እየተደረገ ነዉ።
በዚህ ዙሪያ የአገራችን የሴቶች መብት ተሟጋቾች ምን ያህል እየሠሩ ነው? ብሎ መጠየቅ ይገባል። በኪነ-ጥበቡ ዙሪያ ያለዉን ችግር የሴቶች መብት ተሟጋቾች ምን ያክል ያውቁታል? መፍትሔስ እየፈለጉለት ነው ወይ? የሚለው ሊታወቅ ይገባል። ስለሴቶች ጉዳይ ኹሉም ስለሚያገባው የተሻለ እና በራስ መተማመን ያለው ንቁ ዜጋ እንዲፈጠር ኹሉም በትብብር ሊሠራ ይገባል።
የሴቶችን ዕኩልነት ለማምጣት የወንዶች ሚና ላቅ ያለ ነው። ሴቶች ብቻቸውን ተጽዕኖ ማምጣት ስለሚያስቸግራቸው ወንዶችም ዕኩል በተግባሩ ላይ መሳተፍ እና ድምጽ መሆን አለባቸው ። ይሄን ችግር ተባብረን በመቅረፍ ወደ ሠለጠነ እና ወደተሻለ ዓለም መሔድ ይኖርብናል። ዘመኑ የሠለጠነ እንደመሆኑ መጠን እጅ ለእጅ ተያይዞ አብሮ በመሥራት የሴቶችን መብት እና ተሳትፎ አጉልቶ በማውጣት ጥሩ ጊዜ እንዲመጣ ልንሠራ ይገባናል።
ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014


