ተቃውሞ የገጠመው አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መነሣት

0
651

ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ባለው ጦርነት እና በሌሎች አካባቢዎች በተከሠቱ ግጭቶች ውጥረት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ፣ በመላው ኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚደረግ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ባለፈው ጥቅምት 23/2014 መታወጁ የሚታወስ ነው። አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ የስድስት ወር ቆይታ የነበረው ሲሆን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዐዋጁ እንዲነሳ መወሠኑን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ማክሰኞ ዐዋጁን አንስቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 8/2014 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በኢትዮጵያ ተጥሎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንዲነሳ በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተወያይቶ በ63 ተቃውሞ፣ በ21 ድመጸ ተአቅቦ፣ በአብላጫ ድምጽ ዐዋጁን አንስቷል። በምክር ቤቱ አባላት ጠንካራ ተቃውሞ የገጠመው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ መነሳት፣ ወደ ምከር ቤቱ ከመምጣቱ በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲነሳ ውሳኔ ሀሳብ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ አካላት ተቋውሞ ሲቀርብበት ነበር።

ይህን ውሳኔ ተከትሎ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መርማሪ ቦርድ ከአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ያላጠናቀቃቸው ጅምር ሥራዎች ካሉ ይህ ውሳኔ ከተላለፈበት ከዛሬ ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሥራዎቹን አጠናቆ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እንዲያደርግ ተወስኗል።
የዐዋጁን መነሳት የደገፉ የምክር ቤቱ አባላት ለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ፣ ለሠብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለምጣኔ ሀብትና ቱሪዝም ዕድገት፤ እንዲሁም በውጭ ዲፕሎማሲ ላይ አወንታዊ ሚና ስለሚኖረው በአገር ደረጃ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መነሳቱ ጠቀሜታ እንደሚኖረው በመግለጽ ውሳኔውን ደግፈዋል።

የዐዋጁን መነሳት በጥብቅ የተቃወሙ የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር የዐዋጁን መነሳት ተቃውመዋል። ኢትዮጵያ ከገጠማት ችግር ዕልባት አለማግኘቷን በማንሳት የዐዋጁን መነሳት የተቃወሙ የተለያዩ የምክር ቤቱ አባላት፣ አሁንም ድረስ በአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች እየተገደሉ እና እየተፈናቀሉ በመሆኑ ዐዋጁ መራዘም እንደሚገባው ጥያቄ ቢያቀርቡም ዐዋጁ ከመነሳት አልቀረም።

ከአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አፈጻጸም ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በመደበኛ የፍትሕ ሥርዓት እንዲጠናቀቁ በምክር ቤቱ ውሳኔ ተላልፏል። ዐዋጁ መነሳቱን ተከትሎ ዐዋጁ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የታሠሩ ዜጎችን በአስቸኳይ ከዕሥር እንዲለቀቁ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ጠይቋል።

ከ15 ወር በፊት በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱንና በአገሪቱ ላይ የሕልውና አደጋ መደቀኑን ተከትሎ ነበር አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ የታወጀው። የጦርነቱ መሥፋፋት እና መባባስ የፈጠረውን ሥጋት ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት ችግሩ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን አምኖ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ማወጁ የሚታወስ ነው። ዐዋጁ ከታወጀበት ከጥቅምት 23/2014 ጀምሮ ለስድስት ወራት እንዲዘልቅ የተወሰነ ቢሆንም፣ ውሳኔው የተነሳው ግን ዐዋጁ በታወጀ በሦስት ወር ከ15 ቀኑ ነው።

የዐዋጁን መነሳት ከተቃወሙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ዕጩነት ተወዳድረው የምክር ቤት አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ(ዶ/ር)፣ የዐዋጁ መነሳት ከገጽታ አንጻር በጎ ጎን ቢኖረውም፣ ዜጎች እየሞቱና እየተፈናቀሉ ባሉበት ኹኔታ መነሳቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን አስረድተዋል። “የተወሰነ የገጽታ መሻሻል ለማምጣት ተብሎ፣ በመንግሥት የዜጎች የሕይወት፣ የሀብትና የንብረት ደኅንነትና ዋስትና ባልተሰጠበት ኹኔታ ለማንሳት መቸኮላችን ተገቢ ነው ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል።

መንግሥት ለዜጎች የሕይወትና የንብረት ዋስትና ይሠጣል ወይ ሲሉ ምክር ቤቱን የጠየቁት አባሉ፣ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ ንጹኃን ዜጎች በተደጋጋሚ የሚገደሉበት ኹኔታ በተባባሰበት እና ሕወሓት በአፋር ክልል ዳግም ጦርነት በጀመረበት ወቅት አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ማንሳት ተገቢ አለመሆኑን አብራርተዋል።

ዐዋጁ ከመነሳቱ አስቀድሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ብዙዎች የተቃወሙት ሲሆን፣ በተለይ በአማራ እና በአፋር ክልል ጦርነቱ እልባት ሳያገኝ መነሳት የለበትም የሚል ሐሳብ በተለያዩ አካላት እየቀረበ ነበር።

የዐዋጁን መነሳት አስቀድመው ከተቃወሙት ውስጥ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ይገኝበታል። ፓርቲው ጥር 20/2014 ባወጣው መግለጫ “የፌዴራል መንግሥት ዐውጆት የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ለማንሳት ያቀረበው ሐሳብ የአገሪቱን ወቅታዊ ኹኔታ ያላገናዘበ በመሆኑም በተለይ በአፋር እና አማራ ክልሎች ላይ እንዲቆይ እናሳስባለን” ብሎ ነበር። ፓርቲው የዐዋጁ በአፋር እና አማራ ክልሎች ጸንቶ እንዲቆይ ከመጠየቁ በተጨማሪ፣ በአፋር ክልል ዳግም በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት የክልሉ መንግሥት የክልሉ ሕገ-መንግሥት በሚደነግገው መሠረት በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንዲያውጅ እና ጠንከር ያለ ኮማንድ ፖስት እንዲያደራጅ መጠየቁ የሚታወስ ነው።

ዐዋጁ እሰካሁን ተግባራዊ በሆነባቸው ሦስት ወራት፣ በተለይ በአዲስ አበባ በአሸባሪነት የተፈረጀው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት) አስቦት የነበረው የሽብር ተግባር መክሸፉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መግለጹ የሚታወስ ነው።

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ በተለይ ለሽብር ተግባር ሊውሉ የሚችሉ ሕግ ወጥ የጦር መሣሪያዎችን እና ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለመዋል ጉልህ አስተዋጽዖ ማድረጉ ሲገለጽ ነበር። በአንጻሩ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ፣ ዐዋጁን መሠረት በማድረግ ለሚፈጸሙ የሠብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት እየሆነ ነው የሚሉ ሐሳቦች ይንጸባረቁ ነበር። ኢሰመኮ በተደጋጋሚ ባወጣቸው መግለጫዎች አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ምንክያት ሠዎች ያለ አግባብ እየታሠሩ ነው የሚል ክስ ሲያቀርብ ነበር።

የዐዋጁ ድንጋጌዎች ምን ነበሩ?
የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ፣ “የአገር ሕልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣ ዐዋጅ ቁጥር 5/2014” የሚል ሥያሜ የተሠጠው ሲሆን፣ መንግሥት የአገርን ሕልውና፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላቶች የመጠበቅ የሕግም ሆነ የሞራል ኃላፊነት እና ግዴታ ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፣ ሕወሓት ኢትዮጵያን የማዳከም እና ብሎም የማፍረስ ምኞት ካላቸው የውጭ ኃይሎች ጋር በከፍተኛ ቅንጅት እየሠራ እንደሆነ በመገንዘብ፣ የአገር ሕልውና ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም አዳጋች በመሆኑ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መደንገግ እና ተግባራዊ ማድረግ አደጋውን ለመቀልበስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ መታወጁን እንደ ምክንያት አንስቶ ነበር።

አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ፣ የሠዓት ዕላፊ ገደብ ሊወሰን እንደሚችል፣ ማንኛውም የሕዝብ መገናኛ እና የሕዝብ መጓጓዥ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም እንዲቋረጥ ሊያዝ ይችላል ተብሏል። ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሠው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ ይህ ዐዋጅ ተፈጻሚ ሆኖ ባለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ይቻላል ተብሎ ተደንግጎ ነበር።

በተጨማሪም፣ ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሠው ወይም ድርጅት ንብረት የሆነን ማንኛውንም ቤት፣ ሕንፃ፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበርና እንዲሁም ማንኛውንም ሠው ለማስቆም፣ ማንነቱን ለመጠየቅ፣ ለመፈተሽ፣ በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ የጦር መሣሪያዎችን ለመውረስ፣ ለተወሰነ ጊዜ መንገዶችንና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመዝጋት፣ ሰዎች ለጊዜው በተወሠነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቁ ማዘዝ እና ከፍተኛ የጸጥታ ችግር እና ሥጋት በተፈጠረባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ያለ የአካባቢ አመራር መዋቅር በከፊልም ሆነ በሙሉ ማገድ፣ መለወጥ እና በሲቪልም ሆነ በወታደራዊ አመራር መተካት እንደሚችል ተደንግጎ ነበር።


ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here