የአገር ውስጥ የውኃ ትራንስፖርት የደኅንነት ረቂቅ መመሪያ (Safety Regulations) መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የአገር ውስጥ የውኃ ትራንስፖርትን ለመቆጣጠር፣ እንዲሁም የውኃ ትራንስፖርት አካላትን የብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት በዐዋጅ የተሠጠውን ኃላፊነት ተጠቅሞ ረቂቅ መመሪያውን እንዳዘጋጀም ነው የገለጸው።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር የሺ ፈቃደ እንደገለጹት፣ ረቂቅ መመሪያው የአገር ውስጥ የውኃ ትራንስፖርትን ተመሳሳይ በሆነ መመሪያ ለመቆጣጠር ዋና ዋና ነገሮችን አካቶ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
በዋናነትም፣ በእያንዳንዱ የውኃ አካላት ላይ ምን ዓይነት ጀልባዎች ይንቀሳቀሳሉ የሚለውን ለይቶ ብቃታቸውን ያረጋግጣል ነው ያሉት። እንዲሁም፣ በየውኃ አካላቱ ላይ የተሠማሩ የትራንስፖርት ባለቤቶችና ሠራተኞች እንዴት ፈቃድ ይሠጣሉ እና ምንድን ነው የሚሠሩት የሚለውንም እንደሚቆጣጠር አስገንዝበዋል።
የብቃት ማረጋገጫውንም ለመስሥጠት ወጥ የሆነ መሥፈርት መዘጋጀት አለበት ያሉት ዳይሬክተሯ፣ በየክልሎች የተለያዬ እንዳይሆን እና ወጥነት እንዲኖረው ታስቦ ረቂቅ መመሪያው መዘጋጀቱን አመላክተዋል። በኹሉም ክልሎች በሚገኙ የውኃ አካላት ላይ ላሉ ጀልባዎች ተመሳሳይ የብቃት ማረጋገጫ መስጠት ስለሚያስፈልግም የረቂቅ መመሪያውን አስፈላጊነት አንስተዋል።
እንዲሁም፣ በየክልሎች ያሉ የውኃ አካላት መጠን ከመለያየቱም በላይ፣ አንዱ የውኃ አካል ከሌላኛው የውኃ አካል በመጠን፣ በጥልቀና ሥፋት የሚለያይ በመሆኑም፣ በእያንዳንዱ የውኃ አካላት ላይ የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ምን ዓይነት መሆን እንዳለባቸው እና ለምን ሥራ እንደሚውሉ ለማካተትም ታቅዶ እንደተዘጋጀ ተናግረዋል።
በረቂቅ መመሪያው የተካተተው ሌላኛው ቁልፍ ነገር ደግሞ፣ የውኃ ላይ መጓጓዣዎች አደጋ እንዳይፈጠር ምን ዓይነት የመከላከል ሥራ ሊሠሩ እንደሚችሉ፣ እንዲሁም አደጋ ከተፈጠረም እንዴት እንደሚታገዙ እና አደጋውን አስመልክቶ እንዴት ምርመራ እንደሚካሄድ በግልጽ ያስቀምጣል ነው ያሉት።
አገሪቱ ያሏት የውኃ አካላት በክልሎች እንደመገኘታቸው መጠን፣ ክልሎችም ለዘርፉ የራሳቸውን ዐዋጅ፣ መመሪያ እና ደንብ የማዘጋጀት ሥልጣን ያላቸው በመሆኑ፣ ረቂቅ መመሪያው በአንድ ዓይነትና ወጥነት ባለው አሠራር ዘርፉን በተመሳሳይ መልኩ ለመምራትና ለመቆጣጠር ያስችላል ነው የተባለው።
ዓለም አቀፍ ልምድን በማካተት፣ በየአካባቢው ያለውን የአገር ውስጥ ልምድም በመቀመር ዘርፉን በሚገባ ለመምራት እና ኢትዮጵያም ከዚህ ዘርፍ ማግኘት ያለባትን እንድታገኝ ለማስቻል የተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ትልቅ ዕገዛ እንዳለው ተገልጿል።
የአገር ውስጥ የውኃ ትራንስፖርት ትኩረት ሳይሰጠው የኖረ በመሆኑ፣ ለዘርፉ ትኩረት ሠጥቶ ለመሥራት ከታሰበው የቆዬ ሐሳብ በመነሳት፣ ረቂቅ መመሪያው የተዘጋጀውም በዚህ ዓመት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በውኃ አካላት ላይ ከሚንቀሳቀሱ መጓጓዣዎች እና ባለቤቶች ፈቃድ አሰጣጥ፣ ቁጥጥርና አመራር ጋር በዋናነት የተያያዘው ይህ ረቂቅ መመሪያ፣ ሕዳሴ ግድቡን ጨምሮ ከአገር በሚወጡ ወንዞችና ሌሎች ኹሉም የውኃ አካላት ላይ ያለውን የውኃ ትራንስፖርት ደኅንነት በተመሳሳይ አሠራር ይቆጣጠራል ተብሏል።
ረቂቅ መመሪያው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ገና ውይይት ያልተደረገበት በመሆኑ፣ የሚጨመሩ፣ የሚቀነሱ ወይም የሚሻሻሉ ሐሳቦች ሊኖሩት እንደሚችል ተመላክቷል። ከዚያ በኋላ ወደሚመለከተው የሕግ አካል ሔዶ ሲጸድቅ ሥራ ላይ እንደሚውል ነው የተጠቆመው።
ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014



