በአገር ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ ትኩረቱን በሴቶች እና ሕጻናት ሰብዓዊ መብቶች ጥሠት ላይ ያደረገ ብሔራዊ ምርመራ (National Inquiry) ሊካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሠዎች መብቶችን በተመለከተ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ብሔራዊ ምርመራ ለማድረግ ለሦስት ዓመት የሚዘልቅ መርሃ-ግብር ማዘጋጀቱን ይፋ ባደረገበት ወቀት፣ በዘንድሮው ዓመት ሴቶች እና ሕጻናት መብት ጥሠት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሥራውን እንደሚጀምር ገልጿል።
ምርመራው ግልጽና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንደሚካሄድና በኹሉም ዓይነት የመብት ጥሠቶች ላይ ሳይሆን ውስብስብና ሥልታዊ በሆነ መንገድ በተፈጸሙ የመብት ጥሠቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ነው የተመላከተው። በዚህም በጦርነት ምክንያት፣ በማረሚያ ቤቶች ፣ እንዲሁም ጾታን መሠረት አድርጎ በተፈጸሙ ጥቃቶች ላይ መነሻ ያደረገ ምርመራ እንደሚካሄድ ነው የተመላከተው።
አብዛኛው የምርመራ፣ እንዲሁም የማስረጃ ማሰባሰብ ሒደት የሚካሄደውም በሕዝባዊ መድረክ መሆኑ ተነግሯል። ሴቶችና ሕጻናትም በምርመራው ወቅት ስልት ተነድፎ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳትፎ ያደርጋሉ ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት በተለይም ሕጻናት በከባድ ወንጀል ድርጊት ላይ በሠፊው ተሳታፊ መሆናቸውን ተከትሎ፣ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት በሚያልፉበት ጊዜ ለሚደርስባቸው የመብት ጥሠት ካሳ የሚያገኙበትን መንገድ እንደሚሠራም ኮሚሽኑ ጨምሮ አሳውቋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ሕጻናት ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ እንደገለጹትም፣ ሕጻናትን በተመለከተ ሕጉ በቀላሉ ለዕሥር ስለሚዳርጋቸው የመዋቅር ችግር እንዳለበት የባለሙያ ጥቆማዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም፣ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ሕጻናት ከአዋቂዎች ጋር ስለሚታሠሩ መጠነ ሠፊ የመብት ጥሠት እንደሚደረግባቸው ተመላክቷል። ሴቶችም ከወንዶች በማይለይ መልኩ በአንድ ግቢ ውስጥ ከወንዶች ጋር መታሠራቸው ለመብት ጥሠት ምክንያት መሆኑ ነው ኮሚሽኑ የጠቆመው።
በተጨማሪም፣ የሕጻናት ማገገሚያ ማዕከሎች አለመኖር፣ ለሴቶች እና ሕጻናትም ራሳቸውን የቻሉ ማረሚያ ቤቶች አለመኖራቸው፣ በእነዚህ ወገኖች ዙሪያ ያለውን የመብት ጥሠት ሠፊ እንዳደረገው ነው የተገለጸው።
በመሆኑም፣ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን በደንብ በመመርመር መፍትሔ ለማምጣት እንደሚሠራ ነው ኮሚሽኑ የገለጸው።
ይሁን እንጂ፣ የዜጎች መብት በተደጋጋሚ በመንግሥት አካላት በሚጣስበት ወቅት መንግሥትን ተጠያቂ ለማድረግ አሠራር አለመኖሩ ምርመራው የመብት ጥሰት ክፍተቱን ለመሙላት እንቅፋት እንደሚፈጥር ተመላክቷል።
እንዲሁም፣ በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተም የሚደርስባቸውን ሠፊ የመብት ጥሠት የሚመረምርና መፍትሔ እንዲያገኙ የሚያደርግ ተቋም አለመኖሩ ተጠቅሷል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም በገንዘብ ውሱንነት የተነሳ በተለይ በገጠር ያሉ አካል ጉዳተኛ ሴቶችና ሕጻናት ላይ ምርመራውን ለማድረግ እንደሚቸገር አስገንዝቧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከሴቶችና ሕጻናት በተጨማሪ ነፃነታቸውን የተነፈጉ የኹሉም ሠዎች መብቶችን በተመለከተ ብሔራዊ ምርመራ እንደሚያካሒድ ገልጿል። በዚህም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለማስፈጸምና ሠብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ እንደሚያገዝ ነው ያመላከተው።
ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ይህ አገራዊ ምርመራ ፕሮጀክት፣ 15 ሚሊዮን ዩሮ በጀት የተያዘለት ሲሆን፣ በዜጎች ላይ ውስብስብና ስልታዊ በሆነ መንገድ የተፈጸሙ የመብት ጥሠቶችን ከመመርመር ባሻገር፣ ተዳፍነው የቆዩ የመብት ጥሠቶችን ለመመርመር የሚያሥችል ነው ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014


