የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ ተደረገ

0
1753

ዕረቡ የካቲት 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የ2013 12ኛ ክፍል የኢትዮጵያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ መደረጉን የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።

በ2013 የትምህርት ዘመን ሊሰጥ የነበረው የ12ኛ ክፍል ፈተና በተለያዩ ሀገራዊ ምክንያቶች ወደ 2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተሸጋግሮ በሁለት ዙር መሰጠቱ ይታወቃል።

የመጀመሪያው ዙር ከቅምት 29 እስከ ህዳር 02/2014 ለወንድ 293 ሺህ 865 ሴት 250 ሺህ 703 ድምር 544 ሺህ 568 ተማሪዎች የተሰጠ ሲሆን ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በመጀመሪያው ዙር ሳይፈተኑ ለቀሩ ለወንድ 27 ሺህ 979 ሴት 26 ሺህ 456 ድምር 54 ሺህ 435 ተማሪዎች ደግሞ ከጥር 24-27/2014 በሁለተኛው ዙር ፈተናው ተሰጥቷል።

በአጠቃላይ በሁለቱም ዙር ከተመዘገቡት 617 ሺህ 991 ተማሪዎች ውስጥ ወንድ 321 ሺህ 844 ሴት 277 ሺህ 159 ድምር 599 ሺህ 003 (96.9%) ተማሪዎች ፈተናውን መውሰድ ችለዋል።

የፈተና እርማቱ ደህንነታቸው አስተማማኝ በሆኑና ከንክኪ ነጻ በሆኑ የማረሚያ ማሽኖች አስፈላጊው የደህንነት ጥበቃ በፌደራል ፖሊስና በሴኩሪቲ ካሜራዎች ታግዞ በጥንቃቄ ተከናውኗል። ከዚህ በተጨማሪም የፈተናዎች ውጤት በትምህርት ዓይነት፣ በትምህርት ቤትና በተማሪ ደረጃ ሰፊ የውጤት ትንተና በማካሄድ የእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት ውጤት ተገምግሟል።

በዚሁ መሰረት የመጀመሪያው ዙር የሲቪክስ ፈተና በሁሉም ትምህርት ቤቶች በሚባል ደረጃ የውጤት መመሳሰልና ግሽበት ታይቶበታል። ስለሆነም የሲቪክስ የፈተና ውጤት ለዩኒቨርስቲ መግቢያ መወዳደሪያነት እንዳያገለግል ተወስኗል።

በሌሎቹ የትምህርት ዓይነቶች የተገኘው የውጤት ትንተና ሲታይ ምንም ዓይነት ችግር የሌለበት በመሆኑ እንዲመዘገብ ተደርጓል። ነገር ግን በተናጠል የፈተና ደንብ ጥሰት የፈጸሙ 141 ተማሪዎች ላይ ከውጤት መሰረዝ ጀምሮ በየደረጃው የተለያየ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል።

ለከፍተኛ ትምህርት ገብተው ለመማር ብቁ የሚሆኑ ሁሉም ተማሪዎች ለመግቢያነት የሚያገለግሉ የትምህርት ዓይነቶችን አጠቃላይ አማካይ ነጥብ 50% እና በላይ ያመጡ ተማሪዎች ይሆናሉ። ለምሳሌ በሰባት የትምህርት ዓይነት ተፈትነው ከ600 ለሚያዝላቸው ተማሪዎች አማካይ ውጤት 300 እና በላይ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ገብተው ለሚማሩ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲዎችን የመቀበል አቅም በማገናዘብ ዝርዝር የመግቢያ ነጥብ ወደፊት የሚገለጽ ይሆናል ተብሏል።

ስለሆነም ተማሪዎች የሚከተሉትን አማራጮች በመጠቀም ውጤታቸውን ማወቅ ይችላሉ።

1) በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዌብሳይት፡- result.neaea.gov.et

2) በትምህርት ሚኒስቴር ዌብሳይት፡- result.ethernet.edu.et

3) በቴሌግራም ቦት (Telegram Bot):- @moestudentbot – በዚህ ማስፈንጠሪያ በመግባትና Exam Result የሚለውን በመጫን በመልክት መጻፊያው ላይ የመለያ ቁጥራቸውን በማስገባት እና የ ምልክት በመጫን መላክና ውጤታቸው ማየት ይችላሉ።

4) በ9444 የ ኤስ ኤም ኤስ (9444 SMS) ፡- በመልክት ማስተላለፊያ መጻፊያ ላይ የመለያ ቁጥራቸውን በማስገባት ወደ 9444 በመላክ ውጤታቸውን ማየት ይችላሉ።

የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ፈተናው ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ተግባሩን በቁርጠኝነት ለፈጸሙ በየደረጃው ላሉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና የጸጥታ አካላት ምስጋናውን አቅርቧል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here