በአፋር ክልል በጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎች በሕክምናና በውኃ ዕጥረት እየተቸገሩ ነው

0
1090

እስካሁን ከ350 ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል

በአፋር ብሔራዊ ክልል ሕወሓት እንደ አዲስ በከፈተው ጦርነት ከ350 ሺሕ በላይ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ተከትሎ፣ በተለይም በውኃ ዕጥረት እና በሕክምና ዕጦት እየተቸገሩ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከተፈናቃዮች አረጋግጣለች፡፡

ለተፈናቃዮች ውኃ በቦቴ እየቀረበ ቢሆንም፣ አካባቢው በረሀማ ከመሆኑ የተነሳ ከፍተኛ የሆነ የውኃ ዕጥረት መኖሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተያያዘም በሕክምና ዕጦት የተነሳ በርካታ የጦርነቱ ተጎጅዎች እየተቸገሩ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡ ለአብነትም በዱብቲ ሆስፒታል በርካታ ቁስለኛ ታካሚዎች መኖራቸውንና የሕክምና ቁሳቁስ ዕጥረቱም የጎላ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የአፋር ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አሕመድ አሎይታ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ከከባድ መሣሪያ ጥቃት ሸሽተው የወጡ ነዋሪዎች በባዶ እግራቸው እና የለበሱትን ልብስ ብቻ ይዘው የወጡ በመሆናቸው ሠፊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡

አሁን ላይ መንግሥት በሚችለው አቅም ድጋፍ እያደረገ ነው ያሉት ኃላፊው፣ በየቦታው ተበታትነው የሚገኙ ሠዎችን ወደ መጠለያ ለማምጣት ያሰበ ሲሆን፣ በክልሉ መንግሥት በኩል የሚቀርበው ድጋፍ አናሳ በመሆኑ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ አካላት የሚችሉትን እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

በተለይም አብዛኛው ተፈናቃይ ከመጠለያ ጣቢያ ውጭ በዘመድ ቤት እና በግል ተከራይቶ የሚኖሩ በመሆኑ እና የሚቀርበው ድጋፍ ደግሞ ከመጠለያ ካምፕ ውጭ ላሉት እየቀረበ ባለመሆኑ የምግብና የውኃ ዕጥረት መኖሩን አመላክተዋል፡፡
ሕወሓት እንደ አዲስ ወረራ እየፈፀመ ባለበት በዚህ ወቅትም፣ በኪልበቲ ረሱ ዞን በርካታ ሕፃናት፣ ሴቶችና አዛውንቶችን በጅምላ ጨፍጭፏል፣ ከ350 ሺሕ በላይ ዜጎችም ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል ነው የተባለው፡፡

ተፈናቃዮች ከኪልበቲ ረሱ ዞን፣ ኮነባ፣ በራህሌ፣ አብአላ፣ መጋሌ እና ኢረቢቲ ከሚባሉ አምስት ወረዳዎች የተፈናቀሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ኹሉም ቦታዎች ከትግራይ ክልል የሚዋሰኑ መሆናቸውንም ተመላክቷል፡፡
አሁን ላይ ከሰርዶ 60 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ “ስድሳ” እና “አፍዴራ” በሚባሉ የተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ እና ሌሎችም በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው እንደሚገኙ ነው የተገለጸው፡፡

ብዙ ተፈናቃዮች ከሰመራ 110 እና 180 ኪሎ ሜትር ርቀው የሚገኙት ሲሆን፣ ሰመራ ከተማም ከዘመድ የተጠጉና ቤት ተከራይተው የሚኖሩ መኖራቸውን ተገልጿል፡፡

የአፋር ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እንደገለጸው ከሆነ፣ ሕወሓት ወረራ በካሄደባቸው በኪልበቲ ረሱ አካባቢዎች ማኅተምና ፊርማ ያለው ደብዳቤ በማስያዝ ጨዉ፣ በርበሬ፣ ስኳር፣ ዘይት፣ ፓስታ፣ ማኮረኒ እና ሌሎች ከአርብቶ አደሩ የዘረፏቸውን ቁሳቁሶች በጅምላና በችርቻሮ ይዘው እንዲመጡ ታጣቂዎችን መላኩን አመላክቷል፡፡

ሕወሓት ዛሬም በከባድ መሣሪያ በመታገዝ በጅምላ የጨፈጭፏቸውን እና ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀላቸውን ንጹኃን ዜጎችና ንብረት በመዝረፍ፣ የአፋርን ሀብትና ንብረት ከዚያም አልፎ የአፋርን መሬት ወደ ትግራይ በማካለል፣ ታላቋን ትግራይ ሪፐብሊክ የመመስረት ቅዠቱን ለማሳካት በአፋር ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል ሲሉ ኃላፊው ገልጸዋል።

“ቡድኑ ንጹኃን ዜጎችን በጅምላ መጨፍጨፉን እና ሀብት ንብረታቸውን መዝረፉን ተያይዞታል፡፡ የአፋር ሕዝብም ወራሪው ቡድን ወርሮ ከያዛቸው የአፋር አካባቢዎችን ለማስለቀቅ ብርቱ ተጋድሎ እያደረገ ነው” ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here