-የሲትሪክ አሲድ ዋጋ ከኹለት ሺሕ ወደ ሰባት ሺሕ ብር ከፍ ብሏል
በደረቅና ፈሳሽ ሳሙና ምርት ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎች እንዲሁም በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች የኬሚካል አቅርቦት እጥረት ስለገጠማቸው ሥራ ማቆማቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ከሆነ፤ ፈሳሽና ደረቅ ሳሙና ለማምረት ከውጭ አገራት የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎች ዋጋቸው ከፍ ከማለቱም በተጨማሪ አቅርቦት አለመኖሩን ነው፡፡
ዕጥረቱ እንደገጠማቸው ቅሬታ ካቀረቡት መካከል ጥሬ ዕቃዎችን ከአከፋፋዮች ተረክበው በግላቸው ፈሳሽ ሳሙና የሚያመርቱት ኢሳይያስ ያለው፤ ሲትሪክ አሲድ ከነባሩ ዋጋ ከመጨመሩም በዘለለ ማግኘት እንዳልቻሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ኢሳይያስ አስከትለውም፣ ፈሳሽ ሳሙና ለማምረት ሲትሪክ አሲድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ “ሰሞኑን ለማምጣት ብሄድም የአንድ ኪሎ ሲትሪክ አሲድ ዋጋ ወደ 300 ብር ከፍ ከማለቱም በላይ ማግኘት ስላልቻልኩ በባዶው ተመልሻለሁ” ነው ያሉት፡፡
ካሁን በፊት አንድ ኪሎ ሲትሪክ አሲድ የሚገዙት 90 ብር እንደነበር ያስታወሱት ኢሳይያስ፤ ሰሞኑን ግን ዋጋው ተወዶም ማግኘት ባለመቻላቸው ፈሳሽ ሳሙና ለማምረት መቸገራቸውን ነው ያብራሩት፡፡
አያይዘውም፣ እስካሁን በኹለት ሺሕ 250 ብር ሲገዙት የነበረውን 25 ኪሎ ሲትሪክ አሲድ፣ በድጋሚ ሊገዙ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ማከፋፈያ ጎራ ባሉበት ወቅት ዋጋው ወደ ሰባት ሺሕ 500 ከፍ እንዳለና በቂ አቅርቦትም አለመኖሩን ነው የገለጹት፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ከሆነ፤ እጥረቱ የገጠማቸው በሲትሪክ አሲድ አቅርቦት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጥሬ ዕቃዎችና ኬሚካሎችም ጭምር መሆኑን ነው ማወቅ የተቻለው፡፡
ይህን በተመለከተም ሌላኛዋ ትዝታ እሸቱ በበኩላቸው፣ ከሲትሪክ አሲድ በተጨማሪ የፈሳሽ ሳሙናን ለማምረት የሚጠቀሙበት ሶዲየም ሲልኬትም የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን የጠቆሙ ሲሆን፤ እስካሁን ሲሸጥበት የነበረው ዋጋ 20 ብር እንደነበርና ሰሞኑን ግን ወደ 40 ብር ከፍ ማለቱን ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት፡፡
አክለውም፣ የኮሲቲክ ሶዳ ዋጋ ከ60 ወደ መቶ ብር፤ የላብሳ ኬሚካል ዋጋ ከ80 ብር ወደ 170 ብር ከፍ ማለቱንም በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ እጥረቱን ተከትሎ በየጊዜው የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፤ ለአብነትም 25 ብር ሲሸጥ የነበረው የአንድ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ዋጋ 30 ብር እንደሆነ ኢሳይያስ ያለው ተናግረዋል፡፡
ኬሚካሎችን የሚያከፋፍሉ የግል ድርጅቶች በበኩላቸው፣ የጥሬ ዕቃው እጥረት መከሰቱን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሜሪ ኬሚካል ማከፋፈያ ድርጅትን የሚያስተዳድሩት ለአገር ምንይዘለቅ፣ ከሁሉም በተለየ መልኩ ኤስ. ኤል. ኢ. ኤስ የተሰኘው ኬሚካል እጥረት እንዳለ ያመላከቱ ሲሆን፤ 10 ሺሕ ኮንቴይነር ብቻ እንደነበራቸውና በአራት ቀን ውስጥ እንዳለቀ ተናግረዋል፡፡
ለስምንት ሴክተሮች ጥሬ ዕቃ እንደሚያቀርቡ የጠቀሱት ለአገር፤ የሻምፖና ኮንዲሽር፤ የሳሙናና ዲተርጀንት፤ የለስላሳና የቢራ፤ የቴክስታይል ፋብሪካዎች እና ሌሎችም ፋብሪካዎች የኬሚካል ዕጥረት እንደገጠማቸው ነው የገለጹት፡፡
ለዕጥረቱ መከሰት ኹለት ምክንቶችን ያስቀመጡ ሲሆን፤ በመጀመሪያ ደረጃ የጠቀሱት በተለይም በራሺያ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ጥሬ ዕቃዎችን ለማስገባት እንዳልተቻለና የዶላር ምንዛሬ የመጨመር ችግርን ነው፡፡
ግለሰቡ አስከትለው ያቀረቡት ኹለተኛው መንስኤ፣ ብሔራዊ ባንክ በዕቃ አስገቢዎች ላይ የጣለው አዲስ ሕግ ያስከተለው አሉታዊ ተፅዕኖ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም፣ ከዚህ በፊት በመቶ ሺሕ ዶላር ዕቃ የላከ ሰው 70 ሺሕ ዶላሩን በነጻ ጥሬ ዕቃ እንዲያስገባበት ይፈቀድለት እንደነበር ጠቅሰው፤ ህጉ ከጸደቀ በኋላ ከመቶ ሺሕ ዶላር መካከል 80 ሺሕ የሚሆነው ለብሔራዊ ባንክ እንደሚገባና በ20 ሺሕ ዶላሩ ብቻ በነጻ እንደሚያስገቡ ነው ያብራሩት፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014



