ይህ ዘመናትን የሚሻገር አባባል የተገኘው ከ112 ዓመት በፊት አፄ ምኒልክ ለጅማው ገዢ አባ ጅፋር የላኩት ደብዳቤ በስተመጨረሻ ላይ እንደማሳረጊያ ሠፍሮ ነው። ድሃ በወደደበት ይቀመጥ፤ አትከልክሉት የሚል ይዘት ያለው ይህ መልዕክት፣ ከተላከበት ጊዜ አኳያ የላኪውንም ሆነ የተቀባዩን ሰብዕና የሚስተካከል አስተሳሰብ አሁን እንደሌለ የሚያመላክቱ በርካታ ጉዳዮችን እየታዘብን እንገኛለን።
አትሂዱብን ብሎ ዜጎችን በግዛቱ ለማስቀረት ባደረገው ተግባር ደንብ ተጽፎለት የሚገሠጽ ገዢ እንዳልነበረ፣ አሁን ከእዛው አካባቢ ውጡልን አትቀመጡ እያለ ድሃን የሚያፈናቅል ትውልድ መታየት ከጀመረ ከራረመ። በእንግዳ ተቀባይነት እንታወቃለን የምንለው እኛ ኢትዮጵያውያን፣ ወንድሞቻችንን በጉርብትና ለማሳደር የሚቀፈን ዘመን ላይ እንገኛለን።
ይህ የመጠላላት መንፈስ የመጣው በዘር ወይም ኃይማኖታዊ አስተምህሮን መሠረት አድርጎ ሳይሆን፣ የዘመኑ ፍልስፍና ባሠራጨው ክፉ አስተምህሮ ሳቢያ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ጠላትህን እንደወዳጅህ እይ እየተባለ የሚሰበክ፣ አልያም ኹሉም ሠው እኩል ነው ተብሎ የሚማር ኢትዮጵያዊ፣ እኛና እነሱ በሚል ሠው ሠራሽ መሥፈርት ራሱንና ወገኑን ከፋፍሎ፣ በዘመናዊነት ካባ ተሸፍኖና አዋቂ ተብሎ በኩራት ተጀቡኖ የገዛ ወገኑን ፍዳ ያሳያል።
በዘርም ሆነ በኃይማኖት ሽፋን ጥላቻን መሠረት ያደረገ ማንኛውንም ዓይነት ጥቃትም ሆነ ጭፍጨፋ አልያም ማሳደድ፣ መነሻው ኢኮኖሚያዊ ምኞት ወይም ከሌላው ቀምቶ ለመበልጸግ በመፈለግ እንደሆነ ይታመናል። እንዲህ ዓይነት አጸያፊ ተግባራት ውስጥ ኅብረተሠቡን ለማስገባት እኩይ አስተሳሰብ ያላቸው የኹላችንም ጠላቶች የተለያዩ ዘዴዎችን ይቀይሳሉ። በቅድሚያ በማኅበረሠብ ከፋፍለው ሕዝቡን መለያየት ስለሚያስፈልጋቸው ልዩነት የሚፈጥርን ዕምነት፣ ባህል ወይም ዘርን መሠረት አድርገው ያገኙትን ቀዳዳ እያሠፉ ይለያያሉ።
ይህንንም ተጠቅመው፣ “እነሱ እንዲህ አደረጓችሁ” ብለው በቀላሉ ጥላቻን ለመፍጠር የተጎዱ የሚመስላቸውን ትርክትንም ሆነ ነባራዊ ድህነታቸውን እያነሱ በስስ ጎናቸው ተጠቅመው ይቀሰቅሷቸዋል። ይህንንም ካደረጉ በኋላ ‹እነዛ!› እያሉ ጭራቅ ያደረጓቸውን ወገኖች በማጥላላት “እነሱ እስካሉ ድረስ ጭቆና መኖሩ አይቀርም፤ ድህነታችሁም ይቀጥላል፤ መፅደቅ አትችሉም” የሚል ተመሳሳይ ውትወታ በማድረግ፣ መዳረሻው ጥፋት የሆነ ተግባር ላይ እንዲውሉ ክፋትን ሞልተው ይልኳቸዋል።
በዚህ ዓይነት የጥላቻ መንገድ የሔዱና ሕዝባቸውን የጨፈጨፉ በርካቶች ሲሆኑ፣ የጀርመኑ ናዚ፣ እንዲሁም የሩዋንዳው ኢንተርሀምዌይ የፈጸሙት የዘር ጭፍጨፋ እኛ አገር እየሆነው ካለው ጋር በአጀማመር እጅግ ይመሳሰላል። የአበራሽን ጠባሳ እያዩ በእሳት መጫወትን እንደጀግንነት የሚያዩ በርካቶች የተፈለፈሉበት ዘመን ላይ እንደመገኘታችን፣ ከቀደሙት አስከፊ ታሪኮች በቶሎ ተምረን አካሔዱን ማስተካከል ካልቻልን ከእነሱም የከፋ ኹኔታ ውስጥ እንደምንወድቅ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች።
ጦርነት በታጠቁና ለመሞት በፈቀዱ አካላት መካከል ሥርዓት ተበጅቶለት የሚካሔድ እንደመሆኑ፣ በወንድማማቾች መካከል ቢሆን እንኳን ለሠሚው ላይገርም ይችላል። ከጦርነት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው፣ ማንም አሸነፈ ማን ሠርተው መኖር የሚፈልጉ ድሃዎች ግን ዒላማ ሲሆኑ ማየት ለማንም ቢሆን ማሳዘን የነበረበት ግፍ ነው።
ነገር ግን፣ አሁን አገራችን እየሆነ ያለው “አህያውን ፈርተው ዳውላውን” እንደሚባለው ነው። ለዳውላውም ፈርተው ሌላ ራሳቸውን የተሸከማቸውን በቅሎ የሚገሉ ጉልበተኞች እጅ ላይ የወደቁ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች አሁንም ሞታቸውን እየተጠባበቁ ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆነው ቀን እየቆጠሩ ነው።
ጥቃት ያለባቸው አካባቢዎች የተሠማሩ ማን ጋር እንደሚጋጩ ለይቶ ማወቅ ሲገባቸው፣ ድሃ ንጹኃንን መጠቀሚያ ማድረግና እነሱን ዒላማ ማድረጋቸው የማይጠገን ቁስልን እንደሚፈጥር ሊያውቁ ይገባል። እያደር የሚያመረቅዝ፣ በትውልድ ቅብብሎሽ እየገዘፈ የሚሔድ ጥላቻንና ቂምን ሊፈጥር እንደሚችል ፈፃሚዎቹ እንዲያውቁት መደረግ ይኖርበታል። በማስረጃ የተያዘ ጥቃት ይቅርና ምንም መረጃ በሌለበት ከዘመናት በፊት ተፈፀመ ተብሎ የሚነገር ትርክት ምን እንደፈጠረ በማየት ለልጅ ልጆቻቸው ምን ዓይነት መከራን እንደሚያቆዩ ማስረዳት ያስፈልጋል።
“የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም” እየተባለ በይፋ በሚነገርበት አገር፣ አብሮት የማይዘልቅን ጉልበት አለኝ ብሎ ድሃን ማሰቃየት ቅጣቱ በምድር ብቻ እንደማይሆን ለማንም ግልጽ ነው። በማናለብኝነት ድሃ እንዲሠደድ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ወደፈለገበት ሒዶ እንዳይቀመጥ መጀመሪያውኑ ሊጠብቁት የሚገባቸው ባለሥልጣናት ሲያሳድዱት ማየት እጅግ ያሳዝናል። ድሃ የፈለገበት ማደር ይቅርና የፈለገበት ቦታ ለጊዜውም ማረፍ ተከልክሎ እየተሠቃየ ይገኛል። እንዲህ ዓይነት መድሏዊ አሠራር ለማንም የማይጠቅም ዘግናኝ ግፍ ተብሎ ሕዝብ እንዲያውቀው መደረግ እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ለጥቂቶች ዕይታም ሆነ ለፖለቲከኞች ቁማር ምቹ እንዲሆኑ ሲባል፣ ከሞት የሸሹን እያሳደዱ ከቦታ ቦታ እንደአፈናቃዩ በሕጋዊ መንገድ እየተከታተሉ ማሳደድና ማንቋሸሽ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል። ከኹሉም የሚብሰው፣ “በጀት የለም” እያለ ከየግዛቱ የሚያባርረው ባለሥልጣን ብቻ ሳይሆን፣ “መቀበልና መርዳት አንችልም” እያለ ሌላው እንዳይረዳቸው የሚሸሽገው ጉዳይ ነው። ሕዝብ እንዳያያቸው ወስዶ መደበቁ አሁን እየተለመደ የመጣ አሳፋሪ ድርጊት ቢሆንም፣ መጡ እንደተባለ ወንበዴ መጣ የተባለ ይመስል የፀጥታ ኃይልን እየላኩ ከበው ማስጠበቃቸው፣ ለእነሱ አስበው ሳይሆን በምስልም ተቀርፀው ዕርዳታ እንዳይጠየቅላቸው መሆኑን ደርሰው ስልክ እንዳያስገቡ የተከለከሉ ምስክር ናቸው።
ባልጠፋ ምግብ እንዳይረዱ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ግፉ፣ ድጋፍ በቅርበት ሊያገኙ ከሚችሉበት አካባቢ እንዲርቁና ከዐይን እንዲሠወሩ ማድረጉ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያልታያቸው ባለሥልጣናት፣ ለተፈናቃዮች በማዘን ፈንታ ስለእነሱ ሲሰሙ ዐይናቸው ደም እንደሚለብስ ከሚናገሩት ንግግር መረዳት ይቻላል። ሰውን እንደቆሻሻ በማመላከት ለሚናገሩት ንግግር ቃላትን መምረጥ የተሳናቸው ባለሥልጣናት፣ ነገ እኛስ ብንሆን ለማለት አርቆ ማሰብ ተስኗቸው ይታያሉ።
ከምዕተ ዓመት በፊት ተማሩ የማይባሉ በሳል መሪዎቻችን የሚያስቡትን በጥቂቱ መገንዘብ ያቃታቸው የዘመናችን ባለሥልጣናት፣ ለድሃ በመቆም ፈንታ ሲገፏቸው እየተመለከትን ነው። ሀብታም ቢፈናቀልም፣ እንደ ድሃ የሚያርፍበት ስለማያጣ የችግሩ ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ አቅም የሌለው ድሃ እንደሚሆን ግልፅ ነው። ይህ የማኅበረሠቡ አብዛኛው ነዋሪ ስለሚሆን የሕዝብን ትኩረት እንደሚስብ ማሰብ ብልሀትን ቢጠይቅም የዘመኑ ሹሞች ግን መጠየፍን መርጠዋል።
ከሱማሌ የተፈናቀሉን ያለፍላጎታቸው “ይሻላቸዋል” ብሎ ከተማ አምጥቶ ቤት ሠርቶ ያሠፈረ መንግሥት፣ አማራጭ አጥተው ወደመዲናዋ ዕርዱን ብለው የመጡት ላይ የወሰደው ዕርምጃ ደግሞ በየትኛውም መለኪያ አሳፋሪ ነው። ሕጋዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ የማፈናቀል ተግባሩን በራሱ ወጪ ከከተማ ከተማ እያካሄደ ያለው የመንግሥት አካል፣ ከዋናዋ ከተማ ውጭ ሥልጣን እንደሌለው የሚያሳይ ተፈናቃዮቹን ለተደጋጋሚ እንግልት የሚዳርግ ማመላለስ ውስጥ መግባቱ እንደአገር ልናፍርበት የሚገባ መሆኑን አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች።
የሶሪያ ስደተኞችን ቤተ-መንግሥት ጭምር ተቀብሎ በውድ ወጪ ጋብዞ በመዲናዋ እንክብካቤ እያደረገ የሚገኘው መንግሥት፣ “ውስጡን ለቄስ” ብሎ የአገሩ ዜጋዎች አዲስ አበባ ውስጥ እንዳይታዩ ማድረግ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ማብቂያ ላይ ሆነ ሲባል እንደምንሰማው የወሎ ተፈናቃዮች የንጉሡን ልደት እንዳያበላሹ ተብሎ ከየመግቢያው ታግደው ነበር ይባላል። እውነት ይሁንም አይሁን በአስተዳደራቸው ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ እንዳለ ሆኖ፣ ታሪካቸው ላይ እስከዘላለም ያሳረፈው ጥቁር ቀለምን የሚያጥብ ድርጊት አይኖርም።
የምስልም ሆነ የተለያዩ ዘላቂ ማስረጃዎች በበረከቱበት በዚህ ዘመን፣ አንድ ወገንን ለይቶ የሚደረግ ጭፍጨፋም ሆነ ተጨፍጫፊን ዝም የማስባልና የማግለል ድርጊት እንደዋናው አባራሪ ሊያስኮንን ይችላል። ያም ብቻ ሳይሆን ሊያስጠይቅም ስለሚችል የዘመኑን ሕግ ብቻ ሳይሆን መጪንም ከግምት አስገብቶ በቀረ ጊዜ ማስተካከሉ ይበጃል። አዲስ ማለዳ ምዕተ ዓመት ባስቆጠረው ደብዳቤ ላይ ባረፈ ዓረፍተ ነገር ትቋጫለች። ‹እግዚአብሔር መርጦ፣ ከሠው አልቆ ሲያስገዛ (ገዢ ሲያደርግ) ጊዜ በሠው መጨከን አይገባም። ለሠው ቢያዝኑ ዕድሜ ይሰጣል።”
ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014



