ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመድኃኒት አቅራቢ ኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን ዝግጁ መሆኗን ተገለጸ።
በህክምና መገልገያዎች እና የመድኃኒት አቅርቦት እንዲሁም የጤና ክብካቤ አገልግሎት ቴክኖሎጂ እና ግብአቶች ላይ ትኩረት የሚያደርገው ኢትዮ ኸልዝ ዓለም ዓቀፍ ዓውደ ርዕይና ጉባኤ ለ6ኛጊዜ ከየካቲት 24 እስከ 26/2014 ድረስ በኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል እንደሚካሄድ የኹነቱ አዘጋጅ ፕራና ኤቨንትስ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡
በመድረኩ ተገኝተው ገለፃ ያደረጉት፤ የኢትዮጵያ መድኃኒትና ህክምና መገልገያ አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንት ዳንኤል ዋክቶሌ እስከዛሬ ከውጭ ከሚመጡት መድኃኒቶች በጥቅም ላይ የሚውለው 0.9 በመቶው ብቻ እንደሆነና ቀሪው ግን የማይጠቅም ፈሳሽ ውሃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዳንኤል አክለውም መድኃኒቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲመረት ይህን አላስፈላጊ የሆነ ወጭ ለመቅረፍ እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡
የማህበሩ የኮንፈንስ ዳይሬክተር አሰፋ አለም (ዶ/ር) በበኩላቸው የፊታችን መጋቢት 3 እና 4/ 2014 500 የሚሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚወስዱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
አሰፋ አክለውም ከሰልጣኞቹ መካከል አንዳንዶቹ በአንድ ቀን ቆይታ ሌላኛዎቹ ደግሞ በኹለትና ሦስት ቀናቶች ስልጠናውን እንዲወስዱ መታቀዱን አብራርተዋል፡፡
የፕራና ኤቨንትስ መስራችና ማኔጅንግ ዳይሬክተር ነብዩ ለማ በበኩላቸው መድኃኒቱ በአገር ውስጥ መመረት ሲጀምር በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን የመድኃኒት እጥረት ችግር ይቀርፋል የሚል ትልቅ ተስፋ እንደተጣለበት ገልፀዋል፡፡
መድኃኒትን በተመለከተ በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከሚባሉት ችግሮች በፊት የተመዘገበ መድኃኒቶች ብቻ ማምጣት ነው ያሉት ነብዩ፤ ይህን ተከትሎም ኩባንያዎች አዳድስ መድኃኒት እያስመዘገቡ አለመሆኑን ገልጸው፤ የጉዳዩን ማነቆ ነቅሶ በማውጣት ያልተመዘገቡ መድኃኒቶችን ለማጣትም እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
ኢትዮ ኸልዝ ዓለም ዓቀፍ ዓውደ ርዕይና ጉባኤ ከባንግላዴሽ፣ ህንድ፣ ጆርዳን፤ ሱዳን፤ ደቡብአፍሪካ፤ ታይላንድ፣ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ እና አሜሪካ መሰረታቸውን ያደረጉ ስምንት ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ሲሆን እንዲሁም ከ3 ሺሕ በላይ ሰዎች እንደሚጎበኙት ይጠበቃል፡፡
የዘንድሮው ኹነት ለመጀምሪያ ጊዜ የህንድና የባንግላዲሽ ብሄራዊ ተሳትፎን በማረጋገጥ እድገቱን ማሳየት ችሏል ተብሏል፡፡
ኹነቱ በዘርፉ የተሰማሩ የህክምናና የንግድ ባለሙያዎች በአንድ ላይ በማሰባሰብ በዘርፉ ለተጋረጡ ፈተናዎች የመፍትሄ አቅጣጫዎች ውይይት ለማድረግ ያስችላልም ነው የተባለው፡፡
በአሁኑ ጊዜ 16 ሺሕ 600 የጤና ኬላዎች፤ 3 ሺሕ 778 የጤና ጣቢያዎች እና አራት ሺሕ 110 የመንግስት ሆስፒታሎች በአገልግሎት ላይ እንደሆኑና፤ ባለሙያዎችን በየዓመቱ በማስመረቅ የባለሙያ ከሰው ጋር ያለው ምጣኔ ወደ 2 ነጥብ 1/ 1000 ሰዎች ማሳደግ እንደተቻለም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
______________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




