ማክሰኞ የካቲት 22 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ በቀጠናዊ የሚኒስትሮች ፎረም ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ለሚቀጥሉት 2 ዓመታት የሚኒስትሮች ፎረምን የመምራት ኃላፊነትን ከኬኒያ መረከቧ ተገለጸ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል ከኬንያ የሰራተኛና ማህበራዊ ዋስትና ሚኒስትር ከሲሞን ቼሉጉዊ ጋር የሰራተኞች ፍልሰት አስተዳደርን በማሻሻል ቀጠናዊ ትስስርን ለማጠናከር ገንቢ ውይይት ማካሄዳቸው ገልፀዋል፡፡
ላለፉት ኹለት ዓመታት በኬንያ የተመራ የ11 የምስራቅ አፍሪካ አገራት የሚሳተፉበት ቀጠናዊ የሰራተኞች ፍልሰት መማክርት የሚኒስትሮች ፎረም በርካታ ተግባራትን ሲያካሄድ መቆየቱም ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህም የመሪነቱን ሚና ለተጫወተው የኬንያ መንግስትና ለፎረሙ አባል አገራት ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው ብለዋል ሙፈርያት፡፡
በአገራት የሥራ ገበያ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለገበያ ማቅረብ የአገራቱን ኢኮኖሚ ከመደገፉም ባሻገር ዜጎች የሚገባቸውን ክብርና ጥቅም እንዲያገኙ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡፡
በቀጠናዊ የሚኒስቴሮች ፎረም ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ለሚቀጥሉት ኹለት ዓመታት የሚኒስትሮች ፎረሙን የመምራት ሀላፊነት ኢትዮጵያ መቀበልዋን ገልፀው የአመራር ሽግግሩ በቅርቡ ይካሄዳል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ እንደሌሎች ጉዳዮች ሁሉ በዚህ ዘርፍም የተሰጣትን የመሪነት ሚና ቀጠናዊ ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከርና ፈጣን ለውጥ ለማምጣት ትሰራለች ሲሉም ገልፀዋል፡፡
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




