ኤጀንሲው የትራፊክ ደንብ ቅጣት ክፍያን በቴሌብር መክፈል የሚያስችል አሰራርን ተግባራዊ አደረገ

0
1322

ሐሙስ የካቲት 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የትራፊክ ደንብ ተላላፊ አሽከርካሪዎች የቅጣት ክፍያ ለአሽከርካሪዎች ቀላል፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ በሚያደርግ መልኩበቴሌብር መክፈል የሚያስችል አሰራርን ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ።

አዲስ ይፋ የተደረገው የትራፊክ ቅጣት ክፍያ ስርዓት፣ የቅጣት ክፍያን የሚያቀላጥፍ እና የሚያዘምን አዲስ አሰራር ሲሆን፤ ኤጀንሲው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በጋራ በመሆን ነው በዛሬው ዕለት ይፋ ያደረገው፡፡

የትራፊክ ህግ ተላላፊ አሽከርካሪዎች የትራፊክ ቅጣት ክፍያን ለመፈፀም የሚያጠፉትን ጊዜ በመቆጠብ ቀላል፣ ግልፅ እና ተደራሽ በማድረግ ክፍያውን ለመፈፀም የሚያስችል በኢትዮ-ቴሎኮም የተዘጋጀው 6050 አጭር ቁጥር በመጠቀም የትራፊክ ቅጣት መመዝገቢያ ቴክሎጂ የኤጀንሲውን የአገልግሎት አሰጣጥ የሚያዘምን ነው ተብሏል፡፡

የትራፊክ ቅጣት ክፍያ ስርዓቱ በ6050 አጭር ቁጥር በመጠቀም ትራፊክ ፖሊሶች እና የኤጀንሲው የቁጥጥር ባለሙያዎች በወረቀት ይደረግ የነበረውን አሰራር በማስቀረት፤ ቅጣቱን በሞባይል ስልክ ለተቀጪው በማድረስ መንጃ ፈቃዱ ሳይያዝበት ወይም ታርጋው ሳይፈታበት ጥፋቱን በፈፀመበት ቦታ ክፍያውን መፈፀም የሚያስችል መሆኑም ነው የተነገረው።

በ6050 አጭር ቁጥር የትራፊክ ቅጣትን እንዲፈፅሙ አስፈላጊው ስልጠና በኢትዮ ቴሌኮም ለትራፊክ ፖሊሶች እና የኤጀንሲው የትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎች መሰጠቱም ተነግሯል።

በዚህም መሰረት መንጃ ፈቃዳቸው በዳታ ቤዝ ተመዝግቦ የሚገኙ አሽከርካሪዎችን ሥም እና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን በማስገባት የቅጣት ማዘዣ ቁጥር ለአሽከርካሪው የሚሰጡ ሲሆን የተቀጣው አሽከርካሪም ቴሌ ብርን በመጠቀም ክፍያውን ሲፈፅም ለቀጪው ወዲያው የማረጋገጫ አጭር መልዕክት ስለሚደርሰው መንጃ ፈቃድም ሳይያዝ ታርጋም ሳይፈታ የቅጣት ክፍያውን መፈፀም ያስችላል ተብሏል።

ይህ አገልግሎት ወይም አሰራር ለዘመናት አድካሚ የነበረውን በወረቀት ላይ ያተኮረ የቅጣት ክፍያ አፈጻጸምን ያስቀራል የተባለለት ሲሆን፤ በተለይ አሽከርካሪዎች የቅጣት ክፍያውን ለመፈፀም የሚወስድባቸውን ጊዜ በመቆጠብ እና ድካምን የሚያስቀር ዘመናዊ አገልግሎት ከመሆኑም ባሻገር መንግስት ለመቅጫ ፓድ ህትመት የሚያወጣውን ወጪንም እንደሚያስቀር መገለፁን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የትራፊክ ቅጣት ክፍያ አከፋፈልን በማዘመን ቀላል፣ ቀልጠፋ እና ተደራሽ ለማድረግ እያደረገ ባለው ጥረት፤ ከአራት የግል ባንኮች(አዋሽ፣ አቢሲኒያ፣ ዳሽን እና የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ) እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ቅርንጫፎቻቸው እንዲከናወን ያደረገ ሲሆን፤ የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ከኢብር ጋር በመተባበር አሽከርካሪዎች የትራፊክ ቅጣት ክፍያቸውን በተቀጡበት ቦታ ሆነው በሞባይል ስልካቻው እንዲከፍሉ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱ ይታወቃል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here