ስድስት ባርኔጣዎች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስብሰባዎች የሠራተኛውን ጊዜ የበለጠ እየወሠዱ ይገኛል፡፡ አጨቃጫቂ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ሥርዓትም ስለሌላቸው ብዙ ጊዜን እንደሚወስዱ፣ ሀብትንም እንደሚያባክኑ ይነገራል፡፡ “በሌላ ሠው ጫማ ውስጥ ሆነን ዕንመልከት” እንደሚባለው የውይይቶችንም ሆኑ የኮሚቴ አሠራሮችን ለማሻሻል ይጠቅማል ያሉትን ሐሳብ ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) እንዲህ አጋርተውናል፡፡

በአንድ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ከመስጠት በፊት በኹሉም አቅጣጫዎች የመመልከት ጥበብ
1. አጠቃላይ
በስድስት ባርኔጣዎች የማሰብ ጥበብን ያስተዋወቀው ኤድዋርድ ዴ ቦኖ እ.አ.አ. በ1985 በጻፈው “Six Thinking Hats” በተባለው መጽሐፉ ነው። ብዙውን ጊዜ በግልም ሆነ በቡድን አንድ ውሳኔ የሚያሻው ጉዳይ ላይ ስናስብ በጥቅሙ ወይም በጉዳቱ ላይ እናተኩራለን። የውሳኔያችንን ጥቅምና ጉዳት እኩል ጊዜ ሠጥተን ኹለቱን በእኩል አትኩሮት ካልመረመርናቸው የውሳኔያችንን ጉዳት አሊያም ጥቅም አጋነን የመመልከት ስህተት ልንፈጽም እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ከጥቅምና ጉዳት ባሻገር መታየት ያለባቸው ስሜት እና ፈጠራን የመሰሉ መታለፍ የሌለባቸው ነገሮችን ዋጋ ላንሰጣቸው እንችላለን።

ስድስቱ ባርኔጣዎች የተዘጋጁት ይህንን ችግር ለመቅረፍ ነው። ስድስቱ ባርኔጣዎች ዘይቤዓዊ ምሳሌዎች (metaphoric) ናቸው። እነዚህ ባርኔጣዎች የተለያዩ ስድስት ቀለማት አሏቸው፤ ነጭ፣ ቀይ፣ ጥቁር፣ ቢጫ፣ አረንጓዴና ሠማያዊ ናቸው። ውሳኔ በሚያሻው አቢይ ጉዳይ ላይ በምናሰላስልበት ጊዜ ወይም በኮሚቴ ውይይት በምናደርገበት ወቅት በሐሳባችን እያንዳንዱን ባርኔጣ በየተራ እናጠልቃለን። ለምሳሌ፣ ለእያንዳንዱ ባርኔጣ 3 ደቂቃ ወሰንን እንበል። ነጩን ባርኔጣ በምናጠልቅበት ጊዜ ኹላችንም የምናስበው ነጩ ባርኔጣ አድርገን እንድናስብ በተወሰነበት መንገድ ነው። ውሳኔ ሰጪው አንድ ግለሰብ ከሆነ ግለሰቡ ለ 3 ደቂቃዎች በአንድ ጉዳይ ትኩረት ሠጥቶ እንዲያስብ ያደርገዋል። ውሳኔ ሰጪዎቹ ብዙ ከሆኑም ኹሉም ለ 3 ደቂቃ በአንድ አቅጣጫ እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። ከዚያ ያ ባርኔጣ ወርዶ ሌላው ሲጠለቅ ደግሞ አሁንም ኹሉም ተሰብሳቢ በሌላ አንድ የጋራ አቅጣጫ እንዲያስቡ ይደረጋል።

ይህ አሠራር ከተለመደ የሚገኘው ጥቅም በአጭሩ የሚከተለው ነው። ዘዴው በግለሰብ ደረጃ በተግባር ላይ ሲውል ግለሰቡ በአንድ ጊዜ በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ በማትኮር በጥልቀት ያስባል፤ ቀጥሎ ያንኑ ጉዳይ ከሌላ አቅጣጫ ይመለከታል፤ ከሌላ አቅጣጫ እያልን ጉዳዩን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለማየት ያስችለናል። ይህ ዘዴ አንዱ አቅጣጫ ብቻ የግለሰቡን አዕምሮ ይዞ እንዳያቆይና የሌላውን አቅጣጫ ዕይታ እንዳይጋርድ ይረዳዋል። ይህ ዘዴ በቡድን ሲሠራ ደግሞ ጠቀሜታው ከዚህም የላቀ ነው። ከላይ ከተገለጸው በግለሰብ ደረጃ ካለው ጠቀሜታ በተጨማሪ ተደጋጋፊ ማሰቦችን (collaborative thinking) ይፈጥራል። ለምሳሌ፣ በኮሚቴ ውይይት ወቅት ተሰብሳቢዎች ኹሉ በአንድ ጊዜ በአንድ አቅጣጫ እንዲያስቡ ስለሚረዳ የኮሚቴዎችን ጊዜ የሚገድለውን አላስፈላጊ አተካራ ይቀንስልናል። ይህ ዘዴ የኮሚቴዎች የውሳኔ አሰጣጥ ውጤታማነትን ከ5 ዕጥፍ ጊዜ በላይ እንደሚያሻሽል ይነገራል።

2. የባርኔጣዎቹ ትርጓሜ
እያንዳንዱን ባርኔጣ ስናጠልቅ ትኩረታችን ምን ላይ መሆን እንደሚኖርበት ከዚህ በታች በአጭሩ ቀርቧል።

2.1. ነጭ ባርኔጣ
ነጩ ባርኔጣ የመረጃ ባርኔጣ ነው። ለማስታወስ እንዲረዳን ነጭ ወረቀትን ማሰብ እንችላለን። ነጭ ወረቀት መረጃ መሰብሰቢያ ነው። ነጭ ባርኔጣ ስናደርግ የሐሳባችን ወይም በቡድን ከሆነ የውይይታችን ትኩረት መረጃዎች ላይ ነው። ምንድነው ያለን መረጃ? ያለን መረጃ ምን ያህል ተዓማኒ ነው? ያለን መረጃ በቂ ነው ወይ? በምን ጉዳይ ላይ መረጃ ይጎድለናል? የሚጎድለንን መረጃ የምናገኝበት መንገድ አለን? በነጩ ባርኔጣ የውይይት ወቅት መረጃዎችና ከመረጃ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ብቻ ነው የሚነሱት።

2.2. ቀይ ባርኔጣ
ቀዩ ባርኔጣ ስለጉዳዩ ስሜታችን (“መንፈሳችን”) የሚነግረንን የምናዳምጥበት ነው። ለማስታወስ እንዲረዳን ልባችንና በውስጡ የሚፈሰውን ደም ማሰብ ይቻላል። ቀዩን ባርኔጣ ስናደርግ በተቻለ መጠን መንፈሳችንን በጥሞና ለማዳመጥ እንሞክር፤ ውሳኔው ወይም ዕቅዳችን ምን ዓይነት ስሜት ፈጥሮብናል? በራስ መተማመን፣ ብርታት፣ እልህ፣ ቁርጠኝነት፣ ተስፋ … ወይስ ፍርሃት፣ ሥጋት፣ ጭንቀት፣ ሐዘን፣ መሸማቀቅ … ? ለማንኛውም ውሳኔ መረጃዎች ብቻ ሳይሆን መንፈሳችን የሚነግረንንም ማዳመጥ ተገቢ ነው።

2.3. ጥቁር ባርኔጣ
ጥቁሩ ባርኔጣ ውሳኔያችን ሊያመጣቸው የሚችሉትን አደጋዎች መመልከቻ ነው። ለማስታወስ እንዲረዳ ውሳኔያችን ሊያመጣ የሚችለውን ጥፋትና ሐዘን ይታየን። ጥቁሩ ባርኔጣ እንደተጠለቀ መጠየቅ ያለባቸው የሚከተሉትን የመሰሉ ጥያቄዎችን ነው። ዕቅዳችን ተግባራዊ ከመሆን የሚያግዱት ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? ተግባራዊ ቢሆንስ የሚያመጣቸው ጉዳቶች ምንድን ናቸው? ይህንን ውሳኔ የሚቃወሙ ኃይሎች እነማን ናቸው? መቃወሚያ ምክንያታቸው ምን ሊሆን ይችላል? የውሳኔያችን ተቃዋሚዎች አቅም ምን ያህል ነው? … ጥቁሩ ባርኔጣ እንደተጠለቀ ስለ ውሳኔው ወይም ዕቅዱ ክፉ የተባሉ ነገሮች ኹሉ ይዘርዘሩ።

2.4. ቢጫ ባርኔጣ
ቢጫ ባርኔጣ በሚጠለቅበት ጊዜ ውሳኔያችን ወይም ዕቅዳችን ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞች መተንተኛ ነው። ያሉትንም አማራጭ ውሳኔዎች ማወዳደሪያ ነው። ቢጫ ባርኔጣ ስናጠልቅ አዕምሯችን ውሳኔያችን በሚፈጥራቸው መልካም ነገሮች እንዲደሰትና ብርሃናዊ ዕይታ እንዲኖረው ማበረታት ይገባል። ምን ዓይነት አማራጭ ውሳኔዎች አሉን? የትኛው ነው የተሻለው? የተሻለው በምንድን ነው? ማነው ተጠቃሚ የሚሆነው? ምን ያህል ግለሰቦችን፣ ቡድኖችን፣ ማኅበረሠብን፣ አገርን ይጠቅማል? ምን ያህል ተስፋ ሰጭ ነው? ስኬታማነቱ ምን ያህል ነው? ምን ያህል አጓጊ ነው? … የሚሉና መሰል ጥያቄዎች መነሳት አለባቸው። ተሰብሳቢዎች ይህን መፈፀም አለብን፤ እኛ ካልፈፀምነው ማ የሚል የማድረግ እልህ ውስጥ እንዲገቡ መበረታታት አለባቸው።

2.5. አረንጓዴ ባርኔጣ
አረንጓዴ ባርኔጣ የፈጠራ ባርኔጣ ነው። በማደግ ላይ ያለ አትክልት ይታየን፤ አዳዲስ ቅርንጫፎችን ሲያወጣ፤ አበቦችና ፍሬዎችም ይታዩን። ይህ ባርኔጣ በተጠለቀበት ጊዜ ከተለመደው መንገድ ወጣ ብሎ ማሰብን ይጠይቃል። ውሳኔያችን የሚፈጥራቸው አዳዲስ ዕድሎች ወይም አዳዲስ ተግዳሮቶች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ውሳኔያችን ምን የጎንዮሽ ጥቅሞች ምንስ የጎንዮሽ ጉዳቶች ይኖሩታል? ከቀረቡት አማራጮች ኹሉ ውጭ የሆነ ውሳኔ የለምን? በዚህ ወቅት ጭንቅላታችን “ከሳጥኑ” ወጥቶ እንዲያስብ ይበረታታ።

2.6. ሠማያዊ ባርኔጣ
ሠማያዊ ባርኔጣ ዕሴት ላይ የሚያተኩር ነው። ሠማያዊ ባርኔጣ ስናጠልቅ እኛ ሠማይ ላይ ሆነን ችግሮችን ቁልቁል ስንመለከት ይታየን። ይህ ችግር ምን ያህል አስፈላጊ ስለሆነ ነው ይህን ያህል ያሳሰበኝ ወይም ያሳሰበን? ይህን ጉዳይ አሁን መወሰን ለምን አስፈለገን? በውሳኔው ምን እናገኝበታለን? ሠማያዊ ባርኔጣ ያደረገ አሳቢ ወይም አሳቢዎች ራሳቸው ከችግሮች በላይ ሆነው (አድርገው) እንዲያስቡ ይበረታታሉ።

3. አጠቃቀም
በተለይ በኮሚቴ ሥራ ወቅት
1. ሰብሳቢው የባርኔጣዎቹን ቅደም ተከተል ወስኖ ቢመጣ ይመረጣል። የባርኔጣዎች ቅደም ተከተል እንደጉዳዩ ሊለያይ ይችላል።

2. በእያንዳንዱ ባርኔጣ ላይ መቆየት ያለበት ጊዜ እኩል እንዲሆን ግዴታ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በቀዩ ባርኔጣ ላይ ብዙ አለመቆየት ይቻላል። አደጋቸው ከፍተኛ ለሆኑ ውሳኔዎች ጥቁር ባርኔጣ ላይ ዘለግ ያለ ጊዜ ለመቆየት መመደብ ይገባል። ማኅበራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በቢጫ ባርኔጣ ላይ ረዘም ያለ ጊዜ ማጥፋት ይገባል።

3. በአንድ ባርኔጣ ላይ ቢያንስ አንድ ደቂቃ መቆየት አስፈላጊ ነው- ለይስሙላ ተጠርቶ እንዳያልፍ። በጣም ውስብስብ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ለእያንዳንዱ ባርኔጣ በአማካይ 4 ደቂቃዎች በመመደብ ስብሰባዎችን በግማሽ ሰዓት ለመጨረስ መሞከር።

4. ሰብሳቢው የተሰብሳቢዎቹን የሐሳብ አቅጣጫ የሚቀይሰው የባርኔጣውን ሥም በመጥራት እንዲሆንና ይህም ተሰብሳቢዎች እንዲለምዱት ማድረግ። ለምሳሌ ሰብሳቢው “አሁን ወደ ቢጫ ባርኔጣ እናመራለን” ሲል ኹሉም ተሰብሳቢ “የይቻላል” መንፈስ ውስጥ እንዲገባ ራሱን ማሰልጠን። አረንጓዴ ባርኔጣ ላይ ሲሆን ደግሞ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ባይመስሉም እንኳን ወጣ ያሉ ሐሳቦች ለማቅረብ መሞከር።
የሚከተለውን የ25 ደቂቃ ስብሰባ ሠንጠረዥን በምሳሌነት መጠቀም ይቻላል
ባርኔጣ ምሥል ትኩረት መነሳት ያለባቸው ጥያቄዎች
ሠማያዊ
ዕሴት
(መክፈቻ)
ለምንድነው የተሰበሰብነው? ለምን ይህ ጥያቄ አስፈላጊ ሆነ? የት መድረስ እንፈልጋለን? (3 ደቂቃ)
ነጭ
መረጃ በእጃችን ያለው መረጃ ምንድነው? ምን መረጃ ያስፈልገናል? የሚያስፈልጉን መረጃዎች ማግኘት እንችላለን?ባሉን መረጃዎች ተመስርተን መወሰን እንችላለን?(5 ደቂቃ)
ጥቁር
ጥንቃቄ ይህንን ውሳኔ ብንሰጥ የሚኖረው አደጋ ምንድነው? በቂ ግብዓቶች አሉን?ማነው ሊቃወመን የሚችል?ተቃዋሚያችን ሥራዎቻችንን ለማደናቀፍ ያለው ኃይል ምን ያህልነው?(3 ደቂቃ)
ቢጫ
ተስፋ ያሉን አማራጭ መፍሔዎች ምንድናቸው? የትኛው መፍትሔ የተሻለ ነው?ማንን እናስተባብር?የውሳኔያችንን ጥቅሞች እንዴት እናብዛ? ቅድም ያነሳቸውን ጉዳቶች እንዴት እንቀንስ?
(5 ደቂቃ)
ቀይ
ስሜት
ምን ይሰማናል? ልባችን፣ መንፈሳችን፣ “ውቃቤዓችን” ምን ይለናል?
(1 ደቂቃ)
አረንጓዴ
ፈጠራ ለየት ያለ ሐሳብ ያለው አለ? ይኸ ውሳኔ የሚያመጣቸው የጎንዮሽ ዕድሎች ወይም ጉዳቶች አሉን?
(3 ደቂቃ)
ሰማያዊ
ዕሴት
(ማጠቃለያ)
ውሳኔያች እንዴት ይተግበር? ስኬታማ ነን የምንለው ምን ተፈጥሮ ስናይ ነው?
(5 ደቂቃ)

በዚህ መንገድ በ25 ደቂቃ የሚጠቃለል ስብሰባ በመደበኛው አካሄድ ከ2 ሰዓት በላይ ሊወስድ ይችላል። በስብሰባዎች ውስጥ የሚነሱ አላስፈላጊ ንትርኮችን ስለሚቀንስም ይኸኛው መንገድ የተሻለ ውጤታማ ነው። ይህንን አሠራር የትላልቅ ድርጅቶች ማኔጅመንት ቦርዶች ይጠቀሙበታል። እኛም ተግባራዊ ብናደርገው፤ ብዙ እናተርፍበታለን።

የፅሑፉን አቅራቢ ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) በዚህ [email protected] ኢሜል አድራሻቸው ማግኘት ትችላላችሁ፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here