የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በአፍሪካ ላይ የሚያስከተለው መዘዝ

0
1121

በርካታ ሩሲያዊያን የዩክሬንን ነጻ አገር መሆን የማይቀበሉ ሲሆን፣ እ.አ.አ. በ1991 ከታላቋ ሩሲያ ተገንጥላ ነጻ አገር እንድትሆን መደረጉን እንደ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት እንደሚቆጥሩት ይነገራል። “ዘ ጋርዲያን” የተሰኘው ጋዜጣ በአንድ ወቅት እንዳስነበበውም ከ10 ሰዎች ዘጠኙ ፕሬዝዳንት ፑቲን በዩክሬን ላይ ያላቸውን አቋም የሚደግፉና የሩስያን ታላቅነት ዳግም ለማየት የሚናፍቁ ሆነው ተገኝተዋል።

በተጨማሪም፣ ከስድስት ዩክሬናውያን ቢያንስ አንዱ ሩሲያዊ ማንነት እንዳለው ይነገራል። ከሦስት ሰዎች አንዱም የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪ እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።

ሩስያ በታሪክም ይሁን በሌላ ከዩክሬን ጋር አንድ ሕዝብ ነን ብትልም፣ 70 በመቶ ዩክሬናውያን ግን ይህን የማይቀበሉ ናቸው። 72 በመቶ የሚሆነው የዩክሬን ሕዝብ ደግሞ ሩስያን እንደ ጠላት የሚያይ እንደሆነ ይነገርለታል። ታሪካዊ መረጃዎች እንደሚሉት ሩስያን እንደቅኝ ገዢ አገር አድርጎ የሚመለከታት ዩክሬናዊ ቁጥር ከሕዝቡ ግማሽ የሚልቀው ነው።

ተመሳሳይ ታሪክ፣ ባህል፣ ወግ እና ቋንቋ ያላቸው ዩክሬናውያንም በሥነ-ልቦና ልዩነት የተነሳ ኹለት ጽንፍ በመያዛቸው፣ አንዳቸው የምዕራባውያን ሌላቸው ደግሞ የሩስያ አፍቃሪ ሆነው እንደዘለቁ ማሳያዎች አሉ። በተለይም ምዕራብና ምሥራቅ ተብለው ከሚታወቁት ዩክሬናውያን፣ በምሥራቅ ያሉት ከሩስያ ጋር የዘር ግንድ እንዳላቸው የሚያምኑ መሆናቸው ይጠቀሳል። በምዕራብ ዩክሬን በኩል ያሉት በአንጻሩ ሩስያን በጥርጥሬ ከሚያዩትና ከሚጠሏት ወገን መሆናቸው ነው የሚነገረው።
ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ፣ የ44 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ የሆነችው ምሥራቅ አውሮፓዊቷ አገር ዩክሬን፣ በተለይ በፑቲን አስተዳደር ጥርስ ከተነከሰባት ቆየት እንዳለ የሚነገረው በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው።

ዋነኛው እና የመጀመሪያው፣ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ የሩስያን ሥጋት ለመከላከል ተብሎ በ1941 የተመሠረተውን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (NATO) ለመግታት የሚል ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በቅርቡ የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ምዕራባውያን በቀድሞ የሶቪዬት ሕብረት አገራት ውስጥ የጦር ሠፈር እንዳይገነቡ ማስጠንቀቂያ ሠጥተዋል።

ኹለተኛው እ.አ.አ. በ1991 የፈረሰችውን ሶቪዬት ሕብረትን (ሩስያ) ለመመለስ ነው የሚል ሲሆን፣ ሦስተኛው በተለይ በምሥራቅና በደቡብ ዩክሬን ግዛቶች የሚኖሩ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን በደል ለማስቀረት የሚሉ መረጃዎች ከሩስያ በኩል ይወጣሉ። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም፣ የዩክሬን አስተዳደር በሩስያና ተገንጣዮቹ ዶኔስክ እና ሉሃንስክ ውስጥ ባሉ ሩሲያኛ ተናጋሪዎች ላይ ባለፉት ስምንት ዓመታት ጦርነት አውጆ ቆይቷል ይላሉ።

ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን አባል ከሆነች ሩስያን ያሠጋት የመጀመሪያው ምክንያት ዕውን ይሆንና ጥቁር ባህርን እንዳልጠቀም ያደርገኛል ከሚለው ሥጋቷ በተጨማሪ፣ ታላቋን ሩስያ የመገንባት ዕቅዴ ተረት ሆኖ ይቀራል በሚል ለዓመታት ዩክሬን የአውሮፓና የኔቶ አባል አገር እንዳትሆን ስታስጠነቅቃት መቆየቷ የሚታወቅ ነው።

ሩስያ በ2007 ክሪሚያን ከዩክሬን በመገንጠል ወደ ግዛቷ ከጠቀለለች ጊዜ ጀምሮ፣ ኹለቱ የምሥራቅ አውሮፓ አገራት በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ አልፈው ሀሙስ የካቲት 17/2014 (February 24/2022) ሩስያ በይፋ ዩክሬንን ወራለች።
ከዚያ ቀን ጀምሮ እስካሁን ባለው ሒደት ውስጥ ጦርነቱ የዓለምን ትኩረት በከፍተኛ ኹኔታ የሳበ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም በአጭር ቀናት ውስጥ ብዙ ዓለም ዓቀፍ ለውጦች ተስተናግደዋል። ጦርነቱ ወደፊት በአገራት የኃይል አሰላለፍ፣ በዲፕሎማሲ እና በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ለውጥ እንደተጠበቀ ሆኖ፣መጠኑ ይለያይ እንጂ በኹለቱ አገሮች መካከል በሚደረገው ጦርነት ምክንያት በሚመጣው ተጽዕኖ የማይነካ አገር እንደሌለ ምሁራን ይገልጻሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፒኤችዲ ተማሪ እና የዩኒቨርስቲው የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም ተመራማሪ ኡርጌሳ ኢሬሳ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የኹለቱ አገሮች ጦርነት ከራሳቸው አልፎ በሌሎች አገራት ላይም የሚያስከትለው ጫና የላቀ ስለሚሆን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ትኩረትና ጥንቃቄ የሚሻ ሥራ መሠራት እንዳለበት አመላክተዋል።

ተመራማሪው፣ በተለይ ለአፍሪካ እና ለሌሎች ታዳጊ አገራት በዲፕሎማሲው ላይ ያለው ጫና የጎላ መሆኑን አንስተው፣ ኢትዮጵያም አሁን ላይ ተቻኩላ አቋም መያዝ የለባትም ባይ ናቸው።
ኢትዮጵያ ከኹለቱም አገራት ጋር ጥሩ ግንኙነት ሊኖራት ይገባል ያሉት ኡርጌሳ፣ የምታበረክተው ነገር ስለሌለም በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት አቋም መያዟ አይጠቅማትም ብለዋል።

ሩስያን መደገፍ ዩክሬንን ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያንን ጭምር ያስቆጣል፣ ዩክሬንን መደገፍም እንዲሁ ሩስያን እና ከእሷ ጋር የተሰለፉትን ሊያስቆጣ ስለሚችል ከወገንተኝነት ርቆ ጉዳዩን መከታተል ይሻላል ነው የሚሉት።
ስለዚህም፣ ለኢትዮጵያ ቶሎ አቋም መያዙ አያዋጣትም፣“wait and see strategy”ብትከተል ይበጃል የሚል ሐሳባቸውን ሠንዝረዋል።

የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት በተለይ በታዳጊ አገራት የዲፕሎማሲ ዘርፍ ላይ ያለውን ተጽዕኖ አንስተው የተናገሩት ተመራማሪው፣ ኢትዮጵያም የሚደርስባትን ጫና ለመቀነስ አስፈላጊ ከሆኑ ዕርምጃዎች ውስጥ አንዱ፣ ከተቻለ ከኹለቱም አገሮች ጋር የተለዬ አቋም(exclusive) መያዝ እንዳለባት ነው ያስገነዘቡት። ከኹለቱ አንዷን መምረጥ የግድ ከሆነም ብሔራዊ ሥጋት በማይፈጥር መልኩ ጥናት ተደርጎበት ከሚያዋጣት ጋር መወገን እንደሚኖርባት አንስተዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከኹለቱም አገራት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላት ጠቁመው፣ በኢኮኖሚ ከዩክሬን ጋር መልካም ትስስር እንዳላት እና ሩስያም በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ያላት አገር በመሆኗ ጥሩ ወዳጅ ልትሆን የምትችል ናት ብለዋል። ቀደም ብሎም ከሕወሓት ጋር በነበረው ጦርነት ኢትዮጵያ በአሜሪካና በምዕራባውያን ይደርስባት ከነበረው ወከባ ጋር በተያያዘ ያደረገችው እንደ ውለታ የሚቆጠር ነው ሲሉ አክለዋል።

ኾኖም ኢትዮጵያ ከሩስያ ጋር ካላት ግንኙነት አንጻር ከዩክሬን ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ አይደለም ቢባል እንኳን፣ አሁን ላይ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጓት አሜሪካና አውሮፓውያን ከዩክሬን ጀርባ ናቸው የሚል ዕይታቸውን አስቀምጠዋል።
በዚሁ ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኹለቱ አገሮች ጉዳይ ላይ ተሰብስቦ የመቃወም፣ የመደገፍ እንዲሁም የድምጸ ታቅቦ ውሳኔን ሲያስተናግድ፣ ኢትዮጵያ ድምጽ አለመስጠቷ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉዳዩን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክትም፣ ኹሉም ወገኖች ቀውስን ከሚያባብሱ ኹኔታዎች ታቅበው ግጭቱን ለመፍታት ኹለንተናዊ የሠላም መንገዶችን እንዲጠቀሙ ነው የጠየቁት።

ጦርነቱ በዓለም ጸጥታ ላይ ሥጋት መፍጠሩ የሚነሳ ሲሆን፣ ታዳጊ አገራት ደግሞ የበለጠ ነገም በእኔ ብለው እንዲያስቡ እና ሥጋት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ነውም ይባላል። አንድ ጠንካራ አገር በፈለገው ጊዜ ተነስቶ ጎረቤቱን በመውረር የሚያጠቃ ከሆነ፣ ለብዙ ደካማ አገሮች ነገም በእነሱ ላይ ጠንካራ በሆኑ አገራት ለሚፈጸምባቸው ጥቃት ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ይጠቀሳል።

የኹለቱ አገራት ጦርነት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ እንዲሁ የሚያሳድረው ጫና የላቀ ነው ሲሉ ምሁራን ይገልጹታል። አገራቱ ከፍተኛ የስንዴ አምራች ከመሆናቸውም በላይ፣ ሩስያ በተለይ ለአውሮፓ ዋነኛ የተፈጥሮ ጋዝ አቅራቢ ናት።
በሰላሌ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አዲስ አበባው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ዓለም በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብት፣ በቴክኖሎጅ እና በሌሎች ጉዳዮች የተሳሰረ በመሆኑ አንዱ አገር ሲጎዳ ሌላውም መጎዳቱ አይቀሬ ነው ብለዋል።

በዚህም ኹለቱ አገራት አሁን ላይ ጦርነት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተከትሎ በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚያደርሰውን ጫና ሲያብራሩ፣ ሩስያና ዩክሬን ለዓለም ገበያ ነዳጅ በማቅረብ የሚታወቁ በመሆናቸው የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ይገኛል፤ ወደፊትም መጨመሩ አይቀሬ ነው፤ ይህም የኑሮ ውድነት በዓለም ላይ ያባብሳል ባይ ናቸው።

የነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያም በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ መድረሱ እየተገለጸ ነው። ይህም ከ2007 ወዲህ ከፍተኛው የዋጋ ጭማሪ ነው ተብሏል። በዓለም የነዳጅ ምርት 10 በመቶ ድርሻ እንዳላት የሚነገርላት ሩስያ፣ በዓለም ሦስተኛ ደረጃ ላይ ያለች የነዳጅ ዘይት አምራችና ኹለተኛዋ ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ላኪ አገር መሆኗም ይጠቀሳል።

ይሁን እንጂ፣ ከፍተኛ የነዳጅ ዕጥረት ይኖራል ተብሎ በሚታሰብበት በዚህ ወቅት ትላልቅ የሚባሉ የነዳጅ አምራች አገራት የነዳጅ ምርት መጠናቸውን በዝቅተኛ መጠን ብቻ እንደሚጨምሩ ገልጸዋል። የነዳጅ ላኪ አገራት ድርጅት ኦፔክና አጋሮቹ ከድንበራቸው የሚወጣን ነዳጅ በተለየ መልኩ ከፍ እንደማያደርጉ መግለጻቸው፣ በዓለም ላይ በነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ውድነት ሊከሠት እንደሚችል ይነገራል።

የምጣኔ ሀብት መምህሩ አዲስ አበባው እንደሚሉት፣ ከነዳጅ ባለፈ ኹለቱም አገራት መሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦችንና የግብርና ምርቶችን ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ እንደመሆናቸው፣ ከእነሱ ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸው አገራት ተጽዕኖ ውስጥ መውደቃቸው አይቀርም።
በብዙ አገራት የኢንቨስትመንት መቀዛቀዝ ሊኖር ይችላል ያሉት መምህሩ፣ በተለይ የአፍሪካ አገራት ደግሞ በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉ በመሆናቸው ስንዴን ጨምሮ፣ እንደ ዶሮ ሥጋና እንቁላል ከወደ አገራቱ የሚያስገቡ በመሆናቸው፣ ጦርነቱ የሚጓተት ከሆነ የምግብ ዕጥረት ሊከሠት ይችላል የሚል ዕይታቸውን ሠንዝረዋል።

አንዳንድ የአፍሪካ አገራትም ከሩስያና ዩክሬን ድጋፍ፣ ብድር እና ዕርዳታ የሚያገኙ በመሆናቸው በጦርነቱ ተጎጅ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ከኹለቱም ጋር ያላት ግንኙነት መልካም የሚባል መሆኑን አስታውሰው፣ በተለይ ከሩስያ ጋር ጥሩ አጋር መሆኗን ነው ያነሱት። ከዩክሬን ጋርም ቢሆን በተለይ ቡና ስለምንልክ ጥሩ ግንኙነት አለን ሲሉ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ከሩስያም ይሁን ከዩክሬን ከፍ ያለ መጠን ያለው ስንዴ የምትሸምት በመሆኑ፣ የስንዴ ዕጥረት ሊያጋጥማት እንደሚችል ካነሱ በኋላም፣ ከዚህ ባሻገርም የቆዳ ውጤቶችንና ቡናን ወደነዚህ አገራት ትልክ ስለነበር፣ በዚህ ረገድም ችግር ሊያጋጥም ይችላል የሚል ሐሳብ አላቸው።

ጦርነቱ ሳይታሰብ ነው የተከሰተው፤ በዚህም በርካታ አገራት ጫና ውስጥ ይወድቃሉ ያሉት መምህሩ፣ ኢትዮጵያም የምግብ ዋስትናዋን በራሷ አቅም ያላረጋገጠች አገር እስከሆነች ድረስ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደምትሆን አስምረውበታል።
እንዲህ ዓይነት ችግሮች በሚከሠቱ ቁጥር ጫና ውስጥ ከመግባት የአገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው፣ ለአብነት የሚወራላቸው የበጋ መስኖ ሥራዎች በትኩረት ቢሠሩ፣ ኢትዮጵያ ቢያንስ ምግብ ነክ የሆኑ ፍላጎቶቿን በራሷ አቅም የማረጋገጥ ዕድል ይኖራት ነበር ሲሉ አብራርተዋል።

ኾኖም ያ ሳይሆን በመቅረቱና ጦርነቱም ይሆናል ተብሎ ሳይታሰብ በመከሠቱ፣ አሁን የሚያዋጣው የአጭር ጊዜ መፍትሔ ነው በማለት ገልጸዋል። ለዚህም እንደመፍትሔ ያቀረቡት በተለይ ኢትዮጵያ ከምትፈልገው የስንዴ መጠን አንጻር የግዥ ሒደቱ ጊዜና ንግግር የሚጠይቅ ከመሆኑ፣ በኋላ ችግር ውስጥ ከመግባት ከአሁኑ ወደ ሌሎች አገሮች በማየት አማራጭ ገበያዎችን መፈለግ ግድ ይላታል ነው ያሉት።

ከባለፈው ዓመት በፊት (እአአ 2020) የአፍሪካ አገራት 4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የግብርና ምርቶችን ከሩስያ ያስገቡ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 90 በመቶው የስንዴ ምርት መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ። በተመሳሳይ መልኩም በዚሁ ዓመት ከዩክሬን ጋር 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የግብርና ምርቶችን እንዳስገቡና ከዚህም ውስጥ 48 በመቶ የሚሆነው ስንዴ መሆኑን ነው መረጃዎች ጨምረው የሚያሳዩት። ሩስያና ዩክሬን ከዓለም የስንዴ ምርት ሩብ ያህሉን የሚያቀርቡ መሆናቸው ይነገራል።
ግብጽ በዓለም ቀዳሚዋ የስንዴ ገዥ አገር በመሆኗም በሩስያና ዩክሬን መካከል የተከሠተውን ጦርነት ተከትሎ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደገባች ይነገራል።

በተጨማሪም የዓለምን የማዳበሪያ ምርት ድርሻ 60 በመቶ ገደማ የምትሸፍነው ሩስያ ለኹለት ወር ወደ ውጭ እንደማትልክ ማሳወቋ፣ በይበልጥ በታዳጊ አገራት የግብርና ሥራ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ነው የሚነገረው።

ኢትዮጵያም በነዳጅና ስንዴ ዋጋ መናር እና ዕጥረት የተነሳ ከሚደርስባት ተጽዕኖ ባለፈ፣ ሠብዓዊ ድጋፍ የሚሹ በርካታ ዜጎች በመኖራቸው፣ ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ፊታቸውን ወደ ጦርነቱ ስለሚያዞሩ ለኢትዮጵያ የሚሠጡትን ዕርዳታ ሊቀንሱ ስለሚችሉ ሌላ ጫና ይፈጠራል የሚል ሥጋት አለ።

የሩስያና የዩክሬን ጦርነት በኑክሌር የታገዘ ሊሆን እንደሚችልም ጥቆማዎች እየቀረቡ ይገኛል። የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭም፣ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት በኑክሌር የታገዘና አውዳሚ ይሆናል ነው ያሉት። ላቭሮቭ በገለጻቸው ዩክሬን ኑክሌር ከታጠቀችም እውነተኛ አደጋ ይጠብቃታል ሲሉ መዛታቸው የሚታወስ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ሩስያ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለደኅንነቴ ሥጋት ናቸው በምትላቸውና በዩክሬን ደጋፊ በሆኑ አገሮች ላይ ሳይቀር ጠንከር ያለ ማስፈራሪያ በመሠንዘር ላይ ነች።

‹‹አንዳንድ የውጭ መሪዎች በሩሲያ ላይ የተቀነባበረ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጁ መሆናቸውን እናውቃለን፤ እኛ ደግሞ በዩክሬን የጀመርነውን ወታደራዊ ዘመቻ እስከ መጨረሻው ድረስ እንቀጥልበታለን›› ሲሉም ሰርጌ ላቭሮቭ በዚሁ ሳምንት አስገንዝበዋል።
ይህም በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሠው ሠራሽ ችግሮች የተሞላችውን ዓለም፣ ጦርነቱ በኑክሌር የታገዘ በመሆን ወደባሰ አስከፊ እና ውስብስብ ወደ ሆነ ቀውስ ያመራታል ተብሎ ይታሰባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here